የአሜሪካ የኮሮናቫይረስ መቆጣጠሪያ ግብረ-ኃይል ከፍተኛ ኃላፊዎች ራሳቸውን አገለሉ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ዶክተር አንቶኒዮ ፋውቺ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኮሮናቫይረስ ከታመመ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው በሚል ሦስት የዋይት ሐውስ የኮሮናቫይረስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል አባላት ራሳቸውን ለሁለት ሳምንት አግልለዋል ተባለ።

የዋይት ሐውስ ከፍተኛ የሕክምና አማካሪና የአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ ከተጠቀሱት መካከል አንዱ ናቸው።

አሜሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በምታደርገው ጥረት ፊት ለፊት ሲጋፈጡ የሚታዩት ዶክተር አንቶኒዮ ፋውቺ በበሽታው ከተያዘው ሰው ጋር የነበራቸው ንክኪ "ብዙ ለበሽታውም እንደማያጋልጣቸው" የሚመሩት ድርጅት የአሜሪካው ብሔራዊ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የ79 አመቱ አንቶኒዮ ፋውቺ የኮቪድ 19 ምርመራ አድርገው ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም ለተወሰኑ ጊዜያት ከሰው ተገልልለው በቤታቸው ሆነው እንደሚሰሩና በተከታታይም ምርመራ እንደሚደረግላቸው ኢንስቲትዩቱ ጨምሮ ገልጿል።

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ፀሐፊ ኬቲ ሚለር፣ የቀዳማዊቷ እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ረዳት ስቴፈን ሚለርም ከሰሞኑ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መያዛቸው ተረጋግጧል።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልባሽም በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል።

ራሳቸውን ያገለሉት እነማን ናቸው ?

የአሜሪካ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ሮበርት ሬድፊልድና የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ኮሚሽነር ስቴፈን ሃንም በኮሮናቫይረስ ከታመመ ሰው ጋር ግንኙነት ነበራቸው በሚል ራሳቸውን አግልለው ይገኛሉ።

የአሜሪካ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ማዕከል ባወጣው መግለጫው የ68 አመቱ ዳይሬክተር የኮሮናቫይረስ ምልክቶች እንደማይታይባቸውና ጤንነታቸውም ጥሩ እንደሆነ አረጋግጦ በዋይት ሃውስ ውስጥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ፈጥረዋል በሚልም በቤታቸው ሆነው ይሰራሉ ተብሏል። ንክኪ ከማን ጋር እንደነበራቸው አልተገለፀም።

የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ለሮይተርስ እንደተናገረው የ60 አመቱ ኮሚሽነር ስቴፈን ሃንም በተደረገላቸው ምርመራ ነፃ ቢሆኑም ራሳቸውን ለሁለት ሳምንታት ያህል ለይተው እንደሚያቆዩ ቃለ አቀባዩ ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የአሜሪካ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ሮበርት ሬድፊልድና የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ኮሚሽነር ስቴፈን ሃንም ራሳቸውን አግልለዋል

ሦስቱ የሥራ ኃላፊዎች የምክር ቤቱን አባላትም በሚቀጥለው ሳምንት ምክር ቤቱን ለማናገር ቀጠሮ ይዘው ነበር ተብሏል።

የዶክተር አንቶኒዮ ፋውቺ ራሳቸውን የማግለል ዜና ይፋ ከመሆኑ በፊት፣ ከንቲባ ላማር አሌክሳንደር ሁለቱ የሥራ ኃላፊዎች በቪዲዮ ከምክር ቤቱ ጋር ይወያያሉ ብለው ነበር።

እስካሁን ባለው መረጃ በአሜሪካ ውስጥ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ 78 ሺህ 794 ሞቶች መከሰታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ይህም አሃዝ አሜሪካን ከአለም ቀዳሚ አድርጓታል።

በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥን ጨምሮ እንቅስቃሴ የሚገድቡ መመሪያዎችን ባለፈው ወር ቢያስተላልፉም ብዙዎቹ መመሪያዎቹን አላልተው ሰዎች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል።

ቫይረሱን ለመቆጣጠር እያደረገች ያለችውን እርምጃም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ "ቅጥ አምባሩ የጠፋው" ሲሉ ክፉኛ ተችተውታል።