ፌስቡክ በሥራ ምክንያት ጭንቀት ለያዛቸው 52 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፍል ነው

Facebook app

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

ፌስቡክ ይዘት የሚቆጣጠሩ ሰዎች ደረስብን ላሉት የጤና ቀውስ የ52 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማማ።

ፌስቡክ ላይ የሚለጠፉ መልዕክቶችን ይዘት የሚቆጣጠሩ ግሰለቦች ናቸው ድርጅቱን ከሰው ማሸነፍ የቻሉት።

ፌሰቡክ ላይ የሚለጠፉ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ሰዎችን እንዲሁም ሰው-ሠራሽ ልኅቀትን [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] እየተጠቀምኩ ነው ይላል።

ግዙፉ ማኅበራዊ ድር-አምባ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የሚሠራጩ ጎጂ መልዕክቶችን ለማስወገድ ነው ሰው-ሠራሽ ልኅቀት እየተጠቀመ ያለው።

ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ፌስቡክ ላይ የሚለጠፉ ጎጂ መልዕክቶችን እንዲቆጣጠሩ በሦስተኛ ወገን በኩል ሰዎች የተቀጠሩት።

ግለሰቦቹ ፌስቡክ ላይ የሚለጠፉ ለማየት የሚዘግንኑ እንደ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎችና ራስ ማጥፋት የመሳሰሉ አሰቃቂ ምስሎችን በማየታችን ለጭንቀት [ፖስት-ትሮማቲክ ስትረስ ዲስኦርደር] ተዳርገናል ሲሉ ነው ድርጅቱን የከሰሱት።

ከሳሽና ተከሳሽ በደረሱት ስምምነት መሠረት ፌስቡክ ለሰዎች 52 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

ከሳሾቹ ከአንድ ሺህ ዶላር ጀምሮ እንዳጋጠማቸው ጫና መጠን ካሳ እንደሚከፈላቸውና የአእምሮ ጭንቀት ካጋጠማቸው ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብ ድርጅቱ እንደሚጨምር ታውቋል።

በዚህም መሰረት 11 ሺህ 250 ሠራተኞች ለካሳው ብቁ እንደሆኑ ተነግሯል። ፌስቡክ ጎጂ የሆኑ ይዘቶችን የሰው ልጆች እንዳያዩ የሚያደርግ ቴክኖሎጂም አዘረጋለሁ ብሏል።

ለፌስቡክና ለዩቲዩብ ይዘቶች እንዲቆጣጠሩ ሰዎች የሚቀጥሩ ሦስተኛ ወገን ድርጅቶች ሥራው ፒቲኤስዲ ወይም ጭንቀት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳውቅ ደብዳቤ ሠራተኞቻቸውን ማስፈረም ጀምረዋል።

ፌስቡክ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ይዘት እንዲቆጣጠሩለት ቀጥሯል። ነገር ግን የሰው ልጅ ባያያቸው ተብሎ የሚመከሩ ይዘቶችን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እለያለሁ ብሏል።

ድርጀቱ ሰው-ሠራሽ ልኅቀት 90 በመቶ ያህል ሐሰተኛ መረጃዎችን እየለየና እየመነጠረ ነው ይላል። አልፎም ስለኮሮናቫይረስ የሚሠራጩ ከእውነት የራቁ መረጃዎችን በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካይነት እየተከታተልኩ ነው ባይ ነው።

ቢሆንም ቴክኖሎጂው እንደ ሰው ልጅ አይሆንም የሚል ክርክር ይነሳል።