በቤትዎ በቀላሉ ስለሚሠራ ጭምብል ማወቅ የሚገባዎት ነጥቦች

ማስክ

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በሮቻቸውን ዘግተው የነበሩ አገራት ዳግመኛ ወደ እንቅስቃሴ እየተመለሱ ነው። ዜጎቻቸው ሕዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ሲሆኑ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በመጓጓዣ እንዲሁም መገበያያ መደብር ውስጥ ጭምብል ማድረግን አስገዳጅ ሕግ ካደረጉ አገራት መካከል ፈረንሳይና ጀርመን ይገኙበታል።

የጤና ባለሙያዎች ከሚያዘወትሩት ጭምብል ወይም ማስክ ባሻገር ግለሰቦችም በቤታቸው ማዘጋጀት ይችላሉ። እርስዎም ‘ማስክ’ የሚሠሩበትን መንገድ እና በምን መንገድ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ልንነግርዎ ወደድን።

• እጅ ስፌት ላይ እንዴት ነዎት? ያረጀ ካናቴራ የመጠገን ልማድ አለዎት እንበል። ጭንብል ማዘጋጀትም እንደዚሁ ነው። ጨርቁ በርከት ሲል ማስኩ ጠንካራ ይሆናል። በፊትዎ ልክ መሆኑን እንዲሁም ለመተንፈስ አስቸጋሪ አለመሆኑን ማጣራት አይዘንጉ።

• ጭንብሉ አፍና አፍንጫዎን በአግባቡ መሸፈን አለበት። ፊትዎ ላይ እንዲቀመጥ ጆሮዎ ላይ የሚታሰር ገመድ ሊዘጋጅለትም ይገባል።

• ከጥጥ ወይም ከሐር የተሠሩ ጨርቆች ‘ማስክ’ ለመሥራት ተመራጭ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። እነዚህን ማግኘት ካልቻሉ ግን ቤት ውስጥ ባለ ጨርቅ ለማዘጋጀት ይሞክሩ።

• ጭንብል ከማጥለቅዎም ሆነ ከማውለቅዎ በፊት እጅዎን በሳሙና ሙልጭ አድርገው መታጠብ አለብዎት።

• ‘ማስክ’ በማይጠቀሙበት ወቅት ላስቲክ ውስጥ ያስቀምጡት፣ አዘውትረው ማጠብም ይጠበቅብዎታል።

• ኮረናቫይረስ ይዞዎት ነገር ግን ምልክቶቹን እያሳዩ ካልሆነ ጭንብል በማጥለቅ በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች ከማስተላለፍ ይታቀባሉ።

• የኮቪድ-19 ምልክቶች ካሳዩ ደግሞ በቤትዎ ራስዎን አግልለው መቆት ይገባዎታል። ከምልክቶቹ መካከል ትኩሳት እና ደረቅ ሳል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

• ‘ማስክ’ አጥልቀዋል ማለት ከበሽታው ራስን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸው ሌሎች ጥንቃቄዎችን መተው አለብዎ ማለት አይደለም። ጭምብል ቢያደርጉም እንኳን እጅዎን ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ የግድ ነው።

• አሁን ላይ የፋሽን ዲዛይነሮችን ምሳሌ በማድረግ ጭምብል የሚሠራባቸውን መንገዶች የሚጠቁሙ ብዙ ገፆች አሉ። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያገኟቸዋል።

• ከአንድ በላይ ‘ማስክ’ ማዘጋጀት አይዘንጉ! አንዱ እስኪታጠብ ሌላውን ማድረግ ይችላሉ።

• ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ወይም በትክክል የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማጥለቅ የማይችሉ ግለሰቦች ‘ማስክ’ እንዲጠቀሙ አይመከርም።