ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያን ሃሳብ አልቀበልም ማለቷ ተሰማ

ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የቀረበላትን ሃሳብ አልቀበልም ማለቷ ተሰማ።

በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ባለው አወዛጋቢ ግዙፍ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የስምምነት ሃሳብ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልተቀበሉት ተገልጿል።

በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ግብጽ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ባከለው ግድብ ዙሪያ አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቅርባ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሃሳብ ውድቅ ያደረጉት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለው ግድብን በተመለከተ ያለተፈቱ ቴክኒካዊና ሕጋዊ ጉዳዮች አሉ በማለት ነው።

ግብጽና ሱዳን በምዕራብ ኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድበን ከወንዙ የምናገኘውን የውሃ መጠን በከፍተኛ መጠን ይቀንስብናል የሚል ስጋት አላቸው።

በቢሊዮኖች ዶላር አውጥታ ግድቡን እየገነባችው ያለችው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችላትን ውሃ በመጪው ሐምሌ ወር ውሃ መሙላት እንደምትጀምር አስታውቃለች።

ሦስቱ አገራት ከወራት በፊት በአሜሪካና በዓለም ባንክ አማካይነት ዋሽንግተን ውስጥ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት ተከታታይ ድርድሮች ቢያደርጉም ከመቋጫ ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ በመጨረሻ ላይ የቀረበው የስምምነት ሰነድ ጥቅሟን የሚነካና ለግብጽ ያደላ ነው በሚል እራሷን ከፊርማው መራቋ ይታወሳል።

ለዘመናት ከፍተኛውን የወንዙን ውሃ በመጠቀም የምትታወቀው ግብጽ የግድቡ ግንባታና ውሃ አሞላልን በተመለከተ ከፍያለ ስጋት ስላደረባት አሜሪካንን ጨምሮ የአረብ አገራትን ድጋፍ ለማሰባሰብ ባለፉት ወራት ጥረት አድርጋለች።

የአረብ ሊግ አገራትም የግብጽን ፍላጎት የሚያስከብር የአቋም መግለጫ ባወጡበት ጊዜ ሱዳን መግለጫውን ተቃውማ እራሷን አግልላ ነበር።

ሱዳን ቀደም ባሉት ጊዜያት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን ሃሳብ የሚደግፉ አቋሞችን ስታንጸባርቅ ከመቆየቷ ባሻገር ከአረብ ሊግ ውሳኔ እራሷን በማግለሏ ከኢትዮጵያ ምስጋናን ከግብጽ በኩል ደግሞ ወቀሳ ቀርቦባት ነበር።

ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌትና ሥራን በተመለከተ የእራሷን የስምምነት ሃሳብ ማቅረቧም ተነግሯል።