በስፔን በእድሜ ትልቋ የ113 ዓመት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ አገገሙ

በስፔን በእድሜ ትልቋ የ113 ዓመት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ አገገሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማርያ ብራንያስ 113 ዓመታቸው ነው። ስፔን ውስጥ በእድሜ ትልቋ ሰው እንደሆኑ ይታመናል።

አዛውንቷ ኮቪድ-19 እንደያዛቸው የታወቀው አገራቸው ከሁለት ወራት በፊት እንቅስቃሴ መግታቷን ካወጀች በኋላ ነበር። ለሳምንታት በለይቶ ማቆያ ገብተውም ነበር።

ኮሮናቫይረስ በአረጋውያን ላይ እንደሚጸናባቸው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሆኖም ግን የ113 ዓመቷ ማርያ እጅ አልሰጡም።

የስፔን ባለሥልጣኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ አዛውንቷ ከኮሮናቫይረስ አገግመዋል። ለሳምንታት መለስተኛ የኮቪድ-19 ምልክቶች ያሳዩ የነበሩት ማርያ አሁን ላይ እንደተሻላቸውም ተገልጿል።

ማርያ በአንድ ወቅት ዓለምን አስጨንቆ የነበረውን ‘ፍሉ ፓንደሚክ’ አሳልፈዋል። እአአ ከ1936 እስከ 1939 የዘለቀውን የስፔን የእርስ በእርስ ጦርነትም አልፈውታል።

አዛውንቷ አሁን ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን አልፈዋል።

የማርያ ልጅ በትዊተር ላይ “አሁን ተሽሏታል። ወደቀድሞ እሷነቷ ተመልሳለች። ማውራት፣ መጫወት ትፈልጋለች” ስትል ጽፋለች።

አዛውንቷ የተወለዱት በ1907 ሜክሲኮ ውስጥ ነበር። ከዛም ከሁለት ዓመት በኋላ በሳንፍራንሲስኮ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ በጊሮና ግዛት ይኖሩ ነበር።

በግዛቲቱ አብረዋቸው የነበሩት አባታቸው ጋዜጠኛ ነበሩ።

ማሪያ ሦስት ልጆች አሏቸው። ከልጆቻቸው አንዱ በቅርቡ 86ኛ ዓመት ልደታቸውን አክብረዋል። አዛውንቷ 11 የልጅ ልጆች አፍርተዋል። ከ11ዱ የልጅ ልጆቻቸው ትልቁ 60 ዓመቱ ነው።

ማርያ 13 የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል።

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኦሎት ውስጥ በሚገኝ የአረጋውያን ማቆያ ውስጥ ኖረዋል።