ሪሃና ሦስተኛዋ ሃብታም ብሪታኒያዊት ሙዚቀኛ ሆነች

ሪሃና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሪሃና 'ዘ ሰንደይ ታይምስ ሪች ሊስት' በተሰኘው የቱጃሮችን ሃብት መዝጋቢ መፅሔት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሟ ሰፍሯል።

ነዋሪነቷን ለንደን ያደረገችው ሪሃና 468 ሚሊዮን ዶላር እንዳላት ይገመታል። ሰር ኤልተን ጆንና ሚክ ጃገርን በመብኀጥ ነው ሦስተኛ ሃብታም ብሪታኒያዊት ሙዚቀኛ መሆን የቻለችው።

አንድሩ ሎይድ ዌቤር እና ፖል ማካርትኒ እያንዳንዳቸው 800 ሚሊዮን ዶላር በማካባት አንደኛ ደረጃውን ለሁለት ተቆናጥተውታል።

ሪሃና 'ፌንቲ' በተሰኘ የቁንጅና ምርቶች ድርጅቷ አማካይነት ነው ዶላር ያጋበሰችው ተብሏል። በድርጅቱ ውስጥ ያላት የ15 በመቶ ድርሻ 351 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ይባላል።

የመፅሔቱ ሰዎች ሪሃና የቱጃሮች ዝርዝር ውስጥ የገባችው በአጭር ጊዜ መሆኑ አስገርሞናል ይላሉ። ለጥቆ ቢሊየነር የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለም ባይ ናቸው።

የኮሮናቫይረስ ትሩፋት

ባለፈው ታኅሣሥ 32 ዓመት የሞላት ሪሃና ከሌሎች ሃብታም ሙዚቀኞች ጋር ስትነፃፀር በጣም ወጣት ናት።

ከ40 ብሪታኒያዊ ሃብታም ሙዚቀኞች መካከል ባለ 200 ሚሊዮኑ ኤድ ሺረን እና ባለ 150 ሚሊዮኗ አዴል ከሪሃና በመቀጠል በዕድሜ ለጋዎቹ ናቸው።

ዱዋ ሊፓ እና ጆርጅ እዝራ የተሰኙት አዳጊ ሙዚቀኞች ምናልባት ወደፊት ሃብታቸው እያደገ እንደሚመጣ ይገመታል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በርካታ አርቲስቶች ኮንሰርት ማቅረብ አለመቻላቸው ገቢያቸውን እየጎዳው እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ለመጨረሻ ጊዜ አልበም ካወጣች 4 ዓመት ያለፋት ሪሃና ግን ፊቷን ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ ማዞሯ እንደጠቀማት እየተዘገበ ነው።

ፌንቲ የተሰኘው የቁንጅና ምርቶች አምራች ለተለያዩ የቆዳ ቀለሞች የሚሆኑ ምርቶች ወደ ገበያ ማምጣቱ ተቀናቃኞችን እንዲገዳደር አስችሎታል ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።

82 ሚሊዮን የኢንስታግራም ተከታዮች ያሏት ሪሃና ድርጅቱን ማስተዋወቅ ከጀመረች በኋላ የፌንቲ እውቅና ጫፍ ደርሷል። ድርጅቱ በመጀሪያዎቹ የሽያጭ ሳምንታት ብቻ 78 ሚሊዮን ዶላር አትርፏል።

የሪሃና 468 ዶላር በዩናይት ኪንግደም ብቻ ሳይሆን በዓለምም ሃብታሟ ሴት ሙዚቀኛ ያደርጋታል። ማዶና በ462 ሚሊዮን ዶላር፣ ሴሊን ዲዮን በ365 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ቢዮንሴ በ325 ሚሊዮን ዶላር ሪሃናን ይከተላሉ።