የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 27 የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታወቀ

የምርጫ ቦርድ አርማ

የፎቶው ባለመብት, NEBE

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድጋሚ ለመመዝገብ የሚጠበቅባቸውን መመዘኛዎች አላሟሉም ያላቸውን 27 ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታወቀ።

ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ተመስርተው በአገሪቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መጋቢት ወር መጀመሪያ ድረስ በአዲሱ ህግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ተጠይቀው እንደነበር ቦርዱ አመልክቷል።

ቦርዱ እንዳለው በሕጉ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማቅረብ ያልቻሉና የሚያሟሉበት ጊዜ እንዲራዘም የጠየቁ የፓለቲካ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ ተወስኗል።

በተጨማሪም ሌሎች 14 ፓርቲዎች ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሰረት የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ያላቀረቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን በመግለጻቸው መሰረዛቸው ተነግሯል።

ከእነዚህ ባሻገር ከ106 የፖለቲካ ፓርቲዎች 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በሕጉ መሠረት ተሟልተው የቀረቡ ስለመሆናቸው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው ሰነዶችና ማስረጃዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ ሲጠናቀቅ የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው በእንቅስቃሴያቸው መቀጠል የሚችሉትን ቦርዱ ይፋ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ፓርቲዎች በውስጥ ችግር የተነሳ ሰነዶችን ማቅረብ አለመቻላቸው ስለታመነ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽን በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ወስኖ፤ ሌሎች ሰነዶቻቸው እየተገመገሙ እንደሆነ ተገልጿል።

የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች

1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

2. የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( የብዴን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - የመስራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ትወብዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

7. የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ

8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

9. የመላው አማራ ህዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ደቡብ ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) -ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ

13. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ (ነጻነትናሰላም) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

ሰነድ ባለማምጣታቸው እንዲሰረዙ የተሰወኑት ፓርቲዎች

1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ

2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ

4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት

5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት

6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ

7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት

8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ

10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ

11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ

12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት

13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት

14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ

በልዩ ሁኔታ ሰነድ ካስገቡ ፓርቲዎች ጋር ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች

1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ኢዴፓ)

2. ወለኔ ህዝቦች ፓርቲ

በኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ክልላዊና አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን በሕግ የተቀመጡትን መስፈርቶች ባለማሟላታቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዙት ፓርቲዎች ከዘርዝሩ ሲወጡ ቁጥሩን ዝቅ ቢያደርገውም፤ የቀሩት ፓርቲዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገውን አጠቃላይ ምርጫ በመጪው ነሐሴ ወር ለማድረግ አቅዳ የነበረ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ተደርጓል።