ኮሮናቫይረስ፡ ዝንጀሮዎች ላይ የተሞከረው ክትባት ተስፋ ሰጪ ነው ተብሏል

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስን ይከላከላል የተባለለት ክትባት በስድስት ሬሰስ ማኩዌ በተሰኙ የዝንጀሮ ዝርያዎች ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይቷል።

ክትባቱ በአሁኑ ወቅት በሰው ልጅ ላይ እየተሞከረ ይገኛል። ነገር ግን የሰው ልጅ ላይ ያለው ውጤታማነት ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም።

ስድስቱ ዝንጀሮዎቹ ሳርስ-ኮቭ-2 የተሰኘው ቫይረስ እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ ክትባቱን እንዲወጉ ተደርገዋል። ዝንጀሮዎቹ ክትባቱ ከተሰጣቸው በኋላ ሳንባቸውና በመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ እየቀነሰ መጥቷል።

ከአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት እና የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው ዝንጀሮዎቹ ላይ ሙከራ እያደረጉ ያሉት።

ክትባቱ እንስሳቱ የሳንባ ምች [ኒሞኒያ] በሽታ እንዳይዛቸው እንደተከላከለም ተዘግቧል።

ሬሰስ ማኩዌ የተሰኙት የዝንጀሮ ዝርያዎች ከሰው ልጅ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው እንስሳት ናቸው።

ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ እንስሳቱ በሽታን የመከላከል አቅማቸውን የሚያዳክም በሽታም አልያዛቸውም። ከዚህ በፊት በነበረው የሳርስ ወረርሽኝ ጊዜ መሰል ክትባት እንስሳት ላይ ተሞክሮ ጉዳት አምጭ ሆኖ ተገኝቶ ነበር። አሁን ግን ይህን ዓይነት ክስተት አልታየም ተብሏል።

ጥናቱ በሌሎች ሳይንቲስቶች ታይቶ ገና መታተም ቢጠበቅበትም የለንደን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ስቴፈን ኢቫንስ ግን "በጣም አበረታችና ጥራቱን የጠበቀ" ሲሉ ክትባቱን ገልፀውታል።

በሌላ በኩል የዩናይት ኪንግደሙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ክትባት እየሞከረ ነው።

የለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፔኒ ዋርድ ክትባቱ ጉዳት አምጭ አለመሆኑና ኒሞኒያን መከላከሉ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነው ይላሉ።

ክትባቱ የተሠራው ከኮሮናቫይረስ ቅንጣት ሲሆን፤ የሰው ልጅ ሰውነት ቫይረሱን እንዲያውቀውና በቫይረሱ በሚጠቃበት ጊዜ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው። ክትባቱ ሰውነት በቫይረሱ ሲጠቃ በቂ የሆነ መከላከለያ እንዲያዘጋጅ ያግዛል።

ዝንጀሮዎቹ ላይ የተሞከረው ክትባት ይህንን ማድረግ ችሏል። ማለትም ዝንጀሮዎቹ በቫይረሱ ሲጠቁ መከላከል የሚያስችል አቅምን አጎልብቷል።

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከ100 በላይ ኮሮናቫይረስን ይከላከላሉ የተባሉ ክትባቶች ሙከራ እየተደረገባቸው ነው።