የ64 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የኮንቴነር ውስጥ ሞት የተረፈው ደጀኔ

ደጀኔ ደገፋ
የምስሉ መግለጫ,

ደጀኔ ደገፋ

የአስራ ስምንት ዓመቱ ደጀኔ ደገፋ በያዝነው ዓመት መባቻ በሞያሌ በኩል ኢትዮጵያን ትቶ ወደደቡብ አፍሪካ ጉዞ ሲጀምር ኪሱ ውስጥ ሦስት ሺህ ብር ገደማ ነበረው።

በሚቀጥሉት ሰባት ወራት አራት የአፍሪካ አገራትን ካቆራረጠ በኋላ ግን ካሰበበት ከመድረስ ይልቅ ስድሳ አራት የጉዞ አጋሮቹን ለሞት ገብሮ በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እገዛ ወደገሩ ነብሱን ብቻ ይዞ ተመልሷል።

ትውልድ እና ዕድገቱ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔሮች እና ሕዝቦች ክልል ከሆሳዕና ከተማ አቅራቢያ በሻሸጎ ወረዳ በምትገኝ የገጠር ቀበሌ ነው።

የእናቱን ሞት ተከትሎ አባቱ እርሱን ጨምሮ አምስት ልጆቻቸውን በግብርና ለማስተዳደር ይታትሩ ነበር። ገበታቸው ላይ ግን ለልጆቻቸው የሚበቃ ነገር አቅርበው አያውቁም ነበር።

ኑሮ እንደቋጥኝ መክበዱ ነበር ደጀኔንም ትምህርቱን አምስተኛ ክፍልን ሳይሸገር እንዲተው እና ሥራ ፍለጋ እንዲባዝን ያስገደደው።

የ'ጆበርግ' ጥሪ

ቀየውን ለቅቆ ወደ ኦሮሚያዋ ቢሾፍቱ ከተማ በማቅናት ልዩ ልዩ የቀን ሥራዎችን እየከወነ ራሱን በመደጎም ላይ ሳለ ታዲያ የደቡብ አፍሪካዋ ጆንሃንስበርግ ታማልለው ያዘች።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ከተማዋ አቅንቶ የተደላደለ ኑሮ የመሠረተውን የቅርብ ዘመዱን ተመስላ ነበር 'ጆበርግ' አማላይ ጥሪዋን የላከችው።

"ብዙ ጓደኞቼና ዘመዶቼ [ደቡብ አፍሪካ በመሄድ] ሰርተው እየተለወጡ ስለሆነ፤ እኔም ሰርቼ እለወጣለሁ በማለት ነው መስከረም ሁለት ቀን ጉዞ የጀመርኩት" ይላል ደጀኔ አዲስ አበባ ከተመለሰ እና የአስራ አራት ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

የቅርብ ዘመዱ ጥሪ ብቻ አልነበረም ያቀረበለት፤ ጉዞውንም አመቻችቶለታል- ይህም አሸጋጋሪዎችን ማገናኘትን እና ለእነርሱ የሚከፈለውን ገንዘብ መሸፈንንም ያካትታል።

ጉዞ በደቡብ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ

ከቢሾፍቱ ከተማ ወደ ሐዋሳ በማቅናት የተጀመረው ጉዞው፤ በሞያሌ በኩል ወደኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ማቅናትና ከዚያም በሞምበሳ በኩል ወደ ታንዛኒያ መሻገርን ያካተተ ነበር።

በየአገራቱ ባሉ የፀጥታ ኃይሎች እይታ ውስጥ ላለመግባት ሲባል ጉዞዎች የሚካሄዱት በምሽት ሲሆን፤ የመጓጓዣ ዘዴውም እንደየቦታው ይለያያል። እንዳንዴ በእግር፣ ሌላ ጊዜ በሞተር ብስክሌት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጭነት መኪና አሊያም በኮንቴይነር ውስጥ ነበር።

መዐልታትን በየበረሃው እና በየጫካው ተኝቶ ማሳለፍ ግድ ሲሆን፤ አሸጋጋሪዎቹ ሩዝና ኡጋሊ የሚባለውን ከበቆሎ የሚዘጋጅ ገንፎ መሰል ምግብ ያቀርባሉ።

ይሁንና የተደረጉት ጥንቃቄዎች እርሱን ጨምሮ ሃያ የሚጠጉ ተጓዦችን ታንዛኒያ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ከመያዝ አላዳኗቸውም።

በእስር ግን ከሁለት ቀናት የዘለለ ጊዜ አላሳለፉም። "እንዴት እንደተለቀቅን አናውቅም" የሚለው ደጀኔ ስደተኛ አዘዋዋሪዎቹ ለአሳሪዎቹ ገንዘብ ከፍለው ሳያስለቅቋቸው እንዳልቀረ ይገምታል።

አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ቁጥር በየጊዜው ይለያያል፤ "አምስትም፣ አስርም፣ ሃያም፣ ሰላሳም የምንሆንበት ጊዜ አለ።"

አዘዋዋሪዎቹም እንደዚሁ ይቀያየራሉ፤ አንደኛው አንድ ቦታን ያሳልፍና ሌላኛው ይተካል - እንደደጀኔ ትረካ።

አብረውት ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች መካከል የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሞክሩ መኖራቸው ከድንበር አሻጋሪዎቹ ጋር መጠነኛም ቢሆን የመግባቢያ ዕድልን ፈጥሯል።

ጉዞው ማላዊን አሻግሮት ሞዛምቢክ ሲያደርሰው ግን መከራ ነው የጠበቀው።

የምስሉ መግለጫ,

ደጀኔ አብረውት ወደ አገራቸው ከተመለሱት ወጣቶች ጋር

የኮንቴነር ውስጥ ሰቆቃ

በግምት ከምሽቱ ሦስት ወይንም አራት ይሆናል፤ "ያው ስንት ሰዓት እንደሆነ ስለማናውቅ" ይላል ደጀኔ፤ በሞዛምቢክ ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ቴቴ ክፍለ ግዛት የነበረውን መዘዘኛ ቆይታ ሲያስታውስ።

"ሃምሳ ሰባት ነበርን" ይላል ይቀጥልና አዘዋዋሪዎቹ "ወስደውን ፒስታ (የጠጠር ጥርጊያ) መንገድ ላይ አስቀመጡን" ቆይቶም ሃያ አንድ ተጓዦች ተጨመሩና ቁጥራቸው ወደሰባ ስምንት አደገ። ወዲያውም አዘዋዋሪዎቹ ሰባ ስምንቱን ተጓዦች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያጓጉዛል ያሉትን ኮንቴይነር አመጡ።

"ኮንቴነሩ ሲመጣ አንገባም ብለን እምቢ ብለን ነበር" ይላል ደጀኔ፤ በእምቢታ "የሮጡም ነበሩ።" ነገር ግን አዘዋዋሪዎቹ "በዱላም፣ በቆንጨራም" እየደበደቡ እና እያስፈራሩ ኮንቴነሩ ውስጥ እንዳጨቋቸው ያስታውሳል። "በግድ ነው ያስገቡን"፤ በዚህ መሃል "የተጎዱ፣ እግራቸው የቆሰለም አሉ።"

ተጓዦቹ ኮንቴነተሩ ውስጥ መታጨቃቸው ያዘለውን አደጋ ገምተው ቢማፀኑም፤ ውስጡን ቢደበድቡም አዘዋዋሪዎቹ በሩን ከመጠርቀም አልተመለሱም።

ጉዞው ሲጀምር ጩኸት ማሰማታቸውን ቀጠሉ።

"አንዲት ሴት አብራን ነበረች፤ '[ኮንቴነሩን] አትሰብሩትም ወይ?' እያለች" የኮንቴነሩን ግድግዳ መደብደቡን ታበረታታ ነበር። "እኛም በቦክስም፣ በእግርም እየታገልን ነበር። የሚሰማ [ግን] አልነበረም።"

እንስቷ "ቀድማ እንደሞተች አውቃለሁ" ይላል ደጀኔ። "እየለመነች፤ እየተናገረች ፀጥ አለች። [. . . ] እኔም እየደከምኩ መጣሁ።"

ድካሙ ሲበረታበት ራሱን ስቶ ወደቀ። ኮንቴነሩ ግን መሄዱን አላቆመም።

ከንጋቱ "አስራ አንድ ሰዓት የሚሆን ይመስለኛል። [ስነቃ] በሩ ተከፍቷል። ሲከፈት እግሬ ላይ ልጆች ወድቀዋል፤ ዐይኔን ስከፍት ሰማይ ነው የሚታየኝ።" በቦታው የነበሩ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች 'ኢትዮጵያዊያና ናችሁ?' እያሉ ሲነጋገሩ ማዳመጡንም ያስታውሳል።

ወደ አገር ቤት

የስድሳ አራት ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ከቀጠፈው በኮንቴነር የመተፋፈን አደጋ የተረፈው ደጀኔ በተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እገዛ ከሌሎች አስር ተራፊዎች ጋር ወደአገር ቤት ተመልሷል።

ከአደጋው በኋላ ከቤተሰቡ አባላት ጋር የነበረውን የስልክ ውይይት ሲያስታውስም "'ማን ነው?' አሉ። ደጀኔ ነኝ፤ ስላቸው አላመኑም። ያው እንደሞትኩ ነው ያሰቡት" ይላል።

አደጋው እና የተጓዦቹ ሞት በወርሃ መጋቢት የብዙሃንን አትኩሮት የሳበ ዜና ስለነበረ፤ መረጃውን ማግኘታቸው አልቀረም፤ ሆኖም ስለተራፊዎቹ ማንነት የሚያውቁት ነበር አልነበረምና እርሱም ሞቶ እንደሆነ ጠርጠረው ነበር።

ስልኩን ያነሳችው ታላቅ እህቱ በድንጋጤ እንደዘጋችውና ከደቂቃዎች በኋላ ተረጋግታ እንዳናገረችው ለቢቢሲ ተናግሯል።

አገር ቤት ውስጥ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝለት ሥራ ማጣቱ የደቡብ አፍሪካን ጉዞ እንዲሞክር እንደገፋፋው የሚናገረው ደጀኔ "ከዚህ በኋላ ግን ለምኜ እበላለሁ እንጂ ሁለተኛ የደቡብ አፍሪካን ጉዞ አልሞክርም" ይላል።

ይሁንና አደጋ የበዛባቸውን ኢ-መደበኛ የስደት መንገዶች የሚሞክሩ ወጣቶች ያሰቡበት ቦታ እስኪደርሱ ድረስ ሙከራቸውን ባንዴ እንደማያቆሙ ይዘገባል።

ከደጀኔ ጋር ከነበሩ ተጓዦች መካከል እንኳ ለሁለተኛ ጊዜ ሙከራ የሚያደርጉ ነበሩበት። አንዳንዶቹ እንዲያም የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መግባቢያ ቋንቋ የሆነውን ስዋሂሊኛ ይሞካክሩ ነበር።

ኮቪድ-19 የደቀነው ፈተና

ደጀኔ እና ጓደኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ሮጠው ከናፈቋቸው ወዳጆቻቸው እቅፍ ውስጥ እልገቡም፤ እንደማንኛውም ወደአገር ቤት እንደሚመለስ ተጓዥ አስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ መቀመጥ፣ ከዚያም መመርመር እና ዓለምን እየናጣት ከሚገኘው የኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው።

ምልሰታቸውን ያገዘው እና ያቀላጠፈው የአይኦኤም የኢትዮጵያ የበላይ የሆኑት ማውሪን አቺንግ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ባለበት ወቅት ደጀኔን ለመሳሰሉ ኢ-መደበኛ ስደተኞች እገዛ ማድረግ እጅግ ፈታኝ ሆኖብናል ይላሉ።

ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲደረጉ ሒደቱ የስደተኞቹን ጤና በጠበቀ መልኩ መከናወን አለበት። ከዚህም በዘለለ ስደተኞቹ ሳይታወቃቸው ወረርሽኙን እንዳያስፋፉ ጥንቃቄ መደረግ ግድ ይሆናል።

"ስለዚህም ለወትሮው የማናደርጋቸውን እምርጃዎች እንከውናለን" ይላሉ አቺንግ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "አቋማችን ግልፅ ነው፤ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ባለበት ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እንቅስቃሴ አይመከርም።"

በመሆኑም አቺንግ አገራት በአንድ ወይንም በሌላ ምክንያት ድንበሮቻቸውን አልፈው የገቡ ስደተኞችን ለመመለስ ከመጣደፍ ይልቅ እንክብካቤ እንዲሰጧቸው ይመክራሉ።