ኮሮናቫይረስ፡ 'በፈጣሪ ይሁንታ ይህም ይታለፋል' ከቫይረሱ ያገገሙት

የጤና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመላው ዓለም ወደ 5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን የያዘው ኮቪድ-19፤ ዛሬ ላይ ስርጭቱ በምዕራባውያን አገራት እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም በአፍሪካ ግን አስፈሪነቱ እንደቀጠለ ነው።

የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ቀላል አይደለም። ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚወጡ ዜናዎችም ለሰሚ ጆሮ የሚያስደስቱ አይደሉም። በዚህ ሁሉ መካከል ግን በሽታውን ድል ነስተው የሚድኑ ሰዎች ታሪክ ለሌሎች መጽናኛ ሆነዋል።

ከእነዚህም መካከል የአምስት ሰዎችን ታሪክ ልናጋራችሁ ወደድን።

የፎቶው ባለመብት, Niharika Mahandru

የምስሉ መግለጫ,

ኒሃሪካ ማሃንደሩ

"አሁን መተንፈስ በመቻሌ እድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል" ትላለች ከኮቪድ-19 ያገገመችው ኒሃሪካ ማሃንደሩ።

ከዩናይትድ ኪንግደም ተነስታ እጮኛዋን ለመጎብኘት ወደ ስፔን ካቀናች በኋላ ነበር በቀናት ልዩነት ራስ ምታት እና ትኩሳት ጨምሮ ሌሎች የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት የጀመረችው።

ብዙም ሳትቆይ ህመሟ ተባብሶ ከከባድ ሳል በኋላ መተንፈስ አቃታት። ይህ ተከትሎ ከዚህ ቀደም የጤና እክል ያልነበረባት የ28 ዓመት ሴት ባርሴሎና ወደሚገኝ ሆስፒታል እንድትገባ ተደረገ።

"የነበርኩበት ሁኔታ በጣም ከባድ የሚባል ነበር። መተንፈስ ያቅተኝ ነበር። ጉሮሮዬ እየተዘጋ የሚሄድ አይነት ስሜት ነበር የሚሰማኝ። ይሄ ስሜት በጣም አስፈሪ ነበር" ትላለች ኒሃሪካ።

ሆስፒታሉ በበሽተኞች ተጨናንቆ ስለነበረ ወደ ቤት እንድትመለስ ተደረገች። በቀጣይ ቀን በኮቪድ-19 መያዟን የምርመራ ውጤቷ አረጋገጠ።

ፓራሲታሞል፣ ሃይድሮክሲክሎሪኪን እና አንቲባይቶኪስ መድሃኒቶችን ስትወስድ እንደነበረ ትናገራለች።

አሁን ላይ ከበሽታው ያገገመችው ወጣት "ለተደረገልኝ እንክብካቤ የጤና ባለሙያዎችን በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ" ትላለች።

'በመልካም ስሜት ከተሞላን ቫይረሱን እናሸንፈዋለን'

የፎቶው ባለመብት, Gafar Marhoun

የምስሉ መግለጫ,

ጋፋር ማርሁን

"በፈጣሪ ይሁንታ ይህም ያልፋል። ሁሉም ነገር ወደ ቀደመ ነገር ይመለሳል" ይላል ጋፋር ማርሁን።

የ26 ዓመቱ የአውቶብስ ሹፌር በባህሬን በኮቪድ-19 ተይዞ ህክምና ያገኘው የመጀመሪያው ሰው ነው።

ጋፋር ከባለቤቱ ጋር ወደ ኢራን ተጉዞ ከተመለሰ በኋላ ነበር በቫይረሱ መያዙን ያወቀው። ባለቤቱ ግን በኮቪድ-19 አልተያዘችም። ጋፋር እንደሚለው፤ በዱባይ አድርጎ ወደ ባህሬን ሲመለስ አውሮፕላን ላይ 'በተደጋጋሚ ሲያስል' ከነበረ መንገደኛ ቫይረሱ ሳይዘው እንዳልቀረ ይገምታል።

"በመልካም ስሜት ከተሞላን ቫይረሱን እናሸንፈዋለን። እኔ በበሽታውም ተይዤ ደስተኛ ነበርኩ። የጤና ባለሙያዎች ሁሉ በዚህ ሲደነቁ ነበር" ይላል።

"በቅድሚያ በባህሬን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው እኔ በመሆኔ ተወግዤ ነበር" የሚለው ጋፋር፤ ለሁለት ወራት ልጆቹን አለመያቱን ይናገራል።

ከቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ አገግሚያለሁ ያለው ጋፋር ልጆቼን እስካይ በጣም ጓጉቻለሁ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Jayantha

የምስሉ መግለጫ,

ጃያንታ ራንሲንግሄ በስሪ ላንካ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጡ እና ካገገሙ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ውስጥ አንዱ ነው።

ጃያንታ ራንሲንግሄ በስሪ ላንካ በኮቪድ-19 መያዛቸው ከተረጋገጠ እና ካገገሙ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ውስጥ ይካተታል።

የ52 ዓመቱ አስጎብኚ አገሩን ሊጎበኙ ከመጡ 4 ጣሊያናዊያን ጎብኚዎች ጋር አብሮ ከሰነበተ በኋላ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል።

"የካቲት 9 ላይ በቫይረሱ መያዜ ሲነገረኝ፤ ለህይወቴ ሰጋሁኝ። የምሞት መሰለኝ" ይላል የ52 ዓመቱ ጎልማሳ።

የጤና ባለሙያዎች ጃንያታ መደናገጥ እንደሌለበት ለማረጋጋት ሲሞክሩ፤ ባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ደግሞ ''ቫይረሱን ልታጋቡብን ትችላላችሁ'' በሚሉ ጎረቤቶች የተለያዩ ጥቃቶች እየተሰዘሩባቸው ነበር።

እንደውም ከጎረቤቶቻቸው መካከል አንዷ መኖሪያ ቤታቸውን በእሳት ለማጋየት ሰዎች ስታስተባብር ነበር።

የጤና ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት ስለበሽታው መረጃ በመስጠት ሊታደጓቸው ችለዋል።

ለ18 ቀናት በጤና ተቋም የሰነበተው የ52 ዓመቱ ጎልማሳ፤ መጋቢት 12 ላይ ወደ መኖሪያ ቤቱ ተመልሷል።

"ከካንሰር ጋር መኖር ከቻልኩ፤ ከኮቪድ-19 ጋር መቆየት አይከብደኝም"

የምስሉ መግለጫ,

በአንጀት ካንስር የሚሰቃየው የቢቢሲ ዜና አንባቢ ጆርጅ አላጊአህ

በአንጀት ካንስር የሚሰቃየው የቢቢሲ ዜና አንባቢ ጆርጅ አላጊአህ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ይታዩበት ነበር።

የካንስር ህመምተኛ የሆነው ጋዜጠኛ፤ የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ማሳየቱን ተከትሎ ባደረገው ምርመራ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል።

"ለስድስት ዓመታት የካንስር ህመምተኛ ሆኜ ቆይቻለሁ። ከካንስር ጋር መኖር ከቻልኩ፤ ከኮቪድ-19 ጋር መቆየት አይከብደኝም ብዬ ራሴን አሳምኜ ነበር" ይላል ጆርጅ።

የ64 ዓመቱ የቀደመ የጤና እክል ስለነበረው በኮቪድ-19 ሳቢያ ህይወቱ አደጋ ላይ ነው ተብሎ ተገምቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ጆርጅ ከቫይረሱ አገግሟል ምንም እንኳ ባለቤቱ የቫይረሱን ምልክት ማሳየት ብትጀምርም።

የፎቶው ባለመብት, Tiger Ye

የምስሉ መግለጫ,

ታይገር ዪ

ታይገር ዪ የ21 ዓመት ተማሪ ነው። ነዋሪነቱም የቫይረሱ መነሻ ነች ተብላ በምትገመተው ዉሃን ቻይና ነው።

'በቫይረሱ እንዴት እንደተያዝኩ አላውቅም' የሚለው ታይገር፤ በቅድሚያ ያሳይ የነበረው ምልክት፤ የጡንቻ ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀስ እና ትኩሳት ነበሩ። ከዚያም ያስመልሰው እና ተቅማጥ ተከተለ።

"በህይወቴ በጣም የታመምኩበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም" ብሏል የ21 ዓመቱ ወጣት።

"ማስመለሱ በጣም ህመም ነበረው። ሳለቅስ ነበር። የምሞት መስሎኝ ነበር። የምበላው ምግብ ሁሉ ይወጣ ነበር። እንደዛም ሆኖ ሆዴ በጣም ይወጠር ነበር። እያንዳንዱ የሰውነቴ ክፍል ህመም ነበረው" በማለት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

በዉሃን የሆስፒታሎች አልጋ በቫይረሱ ህመምተኞች ተጨናንቀው ስለነበረ፤ ወደ ሆስፒታል በመሄድ ህክምና ማግኘት አልቻለም ነበር። ራሱን ለይቶ ለ10 ቀናት መድሃኒት እየወሰደ ከቆየ በኋላ ለውጥ ማሳየት ጀመረ።

"ስለ ሁኔታው ማሰብ አልፈልግም። እጅግ አስቀያሚ ነገር ነው" የሚለው ታይገር፤ ከበሽታው ለመዳን የቤተሰቦቹ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ይናገራል።