አቶ ታደሰ ካሳ ስምንት ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስር ተፈረደባቸው

አቶ ታደሰ ካሳ

የፎቶው ባለመብት, AMMA

የባሕር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ስምንት ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስር ፈርዷል።

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በእነ ታደሰ ካሳ የክስ መዝገብ ሥር የነበሩ ሰባት ተከሳሾችን ጉዳይ በተመለከተ ዛሬ ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ ስምንት ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት እና 20 ሺህ ብር እንደተፈረደባቸው አማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

ፍርድ ቤቱ ግንቦት 11 በዋለው ችሎት በጥረት ኮርፖሬት የአክሲዮን ሽያጭ ዙሪያ ክስ የተመሠረተባቸው በእነታደሰ ካሳ የክስ መዝገብ የሚገኙ ዘጠኝ ሰዎች ጉዳይ ተመልክቶ የነበረ ሲሆን፤ ሁለት ተከሳሾቸን በነፃ አሰናብቶ፤ ሰባት ተከሳሾችን ደግሞ ጥፋተኛ ብሎ ነበር።

የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ባለስልጣናቱ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በጥረት ኮርፖሬሽንን ከቦርድ ሰብሳቢነትና ከዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሚናቸው ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል።

በዚሁ ክስ በ1ኛ እና 2ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት በ1ኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምኦን ላይ የስድስት ዓመት እስር እና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ወስኗል።

ከዚህም በተጨማሪ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት 2ኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ደግሞ የስምንት ዓመት የእስር ቅጣትና የ15 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ መበየኑን የሚታወስ ነው።