በደቡብ ሱዳን በጎሳዎች መካከል በተነሳ ግጭት 300 ሰዎች ተገደሉ

ደቡብ ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ግጭቱ በአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች መካከል የተካሄደ ነው

በደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል አዲስ በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ 300 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

በዚህም በጆንግሌይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ከብቶችም ተዘርፈዋል። በተጨማሪም በርካታ ቤቶች ሲወድሙ የእርዳታ ድርጅቶች ንብረት የሆኑ መጋዘኖች ላይ ዝርፊያ ተፈጽሟል።

ከነዋሪዎች በተጨማሪ ሦስት የእርዳተ ሰጪ ድርጅቶች ሰራተኞች በግጭቱ ተገድለዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ለስድስት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነትን ያበቃው ስምምነት በየካቲት ወር ላይ ነበር የተፈረመው። ነገር ግን በአገሪቱ በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል የሚካሄደው ግጭት እንደቀጠለ ሲሆን ከየካቲት ወዲህ 800 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል።

አዲሱ ግጭት የጀመረው በሰሜን ምሥራቋ ፒሪ ከተማ ውስጥ በሚገኙ አርብቶ አደሮች መካከል ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያቸውን ጥለው ወደ ጫካ እንዲሸሹ አድርጓል።

የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት በግጭቱ የተገደሉት አብዛኞቹ ሰዎች በጥይት ተመትተው ነው። ከቆሰሉት ውስጥ የተወሰኑት ለተጨማሪ ህክምና ወደዋና ከተማዋ ጁባ በአውሮፕላን ተወስደዋል።

ከተገደሉት የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች መካከል አንዱ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን አባል ነው።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት 380 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ የካቲት ላይ በተደረሰው ስምምነት አገሪቱ ፕሬዝዳንታ ሳልቫ ኪርና የአማጺዎቹ መሪ ሬክ ማቻር የአንድነት መንግሥት አቋቁመዋል።

ቢሆንም ግን በአገሪቱ ማኅበረሰቦች መካከል የሚቀሰቀሰው የጎሳዎች ግጭት በቋፍ ላይ የሚገኘውን ስምምነትን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

የአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ከሚፋለሙት ጎሳዎች ላይ ጠመንጃዎችንና ላውንቸሮችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን መያዛቸውን ተናግረዋል።