በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያዊን ለአንድ ጉዞ ከፍተኛ ገንዘብ ተጠየቅን አሉ

በሌባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ለመዝገባ በኮንስላ ደጃፍ ላይ ሲጠባበቁ

የፎቶው ባለመብት, JOSEPH EID

የምስሉ መግለጫ,

በሌባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ለመዝገባ በኮንስላ ደጃፍ ላይ ሲጠባበቁ

ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ በሌባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ጉዞ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ ጠየቀን ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ።

በሌባኖስ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለሚደረግ አንድ በረራ 680 ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን እና የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ደግሞ በቆንስላው በኩል ተመዝግበው 580 ዶላር ክፈሉ መባላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌባኖስ በርካታ ዓመታትን የቆየችው ትነበብ በኃይሉ፤ "የምግብ እርዳታ የሚቀበሉ ልጆች እንዴት አድርገው ነው 580 እና 680 ዶላር መክፈል የሚችሉት? በአገሪቱ የጠፋ ዶላር ከየት ነው የሚመጣው? ዋጋው በጣም የበዛ ነው" ትላላች።

ከዚህ ቀደም ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለሚደግ በረራ ተወደደ ከተባለ 350 ዶላር ይከፈል እንደነበረ ትነበብ ትናገራለች።

"በዚሀ አስቸጋሪ ወቅት ይህን ያክል ገንዘብ ከየትም ሊመጣ አይችልም። አይደለም እኛ የሌባኖስ ዜጎች እራሳቸው ዶላር ቸግሯቸዋል። 580 ዶላር ለማግኘት እና ኤምባሲ ለመመዝገብ ገላቸውን እስከ መሸጠ የደረሱ አሉ" ብላለች።

የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ውዝፍ እዳ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል ሌባኖስን በሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።

በውዝፍ እድ ውስጥ የምትገኘው ሌባኖስ፤ ሥራ አጥ በሆኑ ወጣቶች በተቃውሞ ስትነጣ ቆይታለች። የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ የተጣለው ገደብ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ እንዳይወጡ ቢያግድም፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ግን 'ከድጥ ወደ ማጡ' እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።

የፎቶው ባለመብት, ANWAR AMRO

የምስሉ መግለጫ,

ሚያዚያ 23 በቤይሩት ጎዳናዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ የበረታባቸው የሌባኖስ ወጣቶች ማስክ አድርገው ለተቃውሞ በወጡበት ወቅት

ወደ ውጪ የምትልከውን ምርት ማምረት ያቃታት ሌባኖስ ገንዘቧ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለውን ልዩነት ሰማይ እንዲነካ እና ከፍተኛ የዶላር እጥረት እንዲከሰት አድጓል።

የአገሪቱ መንግሥት በአገሪቱ ያጋጠመውን የዶላር እጥረት ለማስታገስ በማዕከላዊ ባንኩ ውስጥ የባለሃብቶችን ተቀማጭ ዶላር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ለማድረግ መገደዱን ዘ ኒውዮር ታይምስ ከቀናት በፊት ዘግቦ ነበር።

እንደ ትነበብ ከሆነ በሌባኖስ ያጋጠመው ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ አሰሪዎቻቸው ደሞዝ መከፍል ስላቃታቸው ሠራተኞችን ከቤት እያስወጡ ይገኛሉ።

በዚህም በርካታ ዜጎች ጎዳና ላይ ወድቀዋል። "ብዙ ልጆች ሜዳ ላይ ከመውደቅ ብለው፤ ምግብ እያገኘን ቤት ውስጥ ብንቀመጥ ይሻላል ብለው ያለ ደሞዝ በአሰሪዎች ቤት እየሰሩ ይገኛሉ" ስትል ትነበብ ትናገራለች።

"ከዚህ በረራ ትርፍ አናገኘም"

ቢቢሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገጽ ላይ ማረጋገጥ እንደቻለው ለምሳሌ ዛሬ ግንቦት 13 ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለሚደረግ የነጠላ ጉዞ በረራ 680 ዶላር ይጠይቃል።

በሌባኖስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአካባቢ ማናጀር የሆኑት አቶ ዳንኤል ጽጌ የቲኬት ዋጋው ከተለመደው ውጪ ለምን ከፍ እንዳለ ጠይቀናቸው ነበር። አቶ ዳንኤል፤ አየር መንገዱ ከቤይሩት-አዲስ አበባ በሚያደርገው በረራ ትርፍ እያገኘ እንዳልሆነ አጥብቀው ይናገራሉ።

"ይህ የንግድ በረራ አይደለም። ይህን የትኬት ዋጋ ያወጣነው ወጪያችንን እንዲሸፍን ብቻ ነው። ምንም አይነት ገቢ አያስገኝም። ወጪውን እንዲሸፍን ብቻ ነው። ዝርዝር ስሌት አለን።"

ጨምረውም "ከዚህ ቀደም ከቤይሩት ተነስተው በአዲስ አበባ በኩል አድረግው ወደ ሌሎች አገራት የሚሄዱ ተሳፋሪዎችም በዚህ በረራ ላይ ይኖሩ ነበር። 3ሺህ እና 4ሺህ ዶላር ድረስም የሚከፍሉ አሉ። አሁን ግን ይህ የለም። አሁን የምናሳፍረው መንገደኞች በቁጥር ጥቂት ናቸው። በዚያ ላይ ወደ አዲስ አበባ ብቻ የሚሄዱ ናቸው" ይላሉ።

አቶ ዳንኤል "አውሮፕላኑ መብረር የሚችለው ዝቅተኛው ዋጋ ይህ [680 ዶላር] ነው" ብለዋል።

ቻርተር በረራ

በመካከለኛ ምሥራቅ በምትገኘው ሌባኖስ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህም መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው መሆናቸውን በአገሪቱ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የመኖሪያ ፍቃድ ከሌላቸው መካከል አንዷ ዘሃራ መሐመድ [ስሟ የተቀየረ] ናት። የጎዞ ሰነድ ስለሌላት ቆንስላው በጠየቀው መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ 580 ዶላር ከፍላ ወደ አገሯ ለመመለስ መጠባበቅ ከጀመረች 6 ወራት አልፈዋል።

"መቼ እንደምንሄድ አልነገሩንም። ፎቶግራፍ ሰጥተን ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ ነው የተባልነው። እየጠበቅን ባለበት ጊዜ ኮሮናቫይረስ ተከሰተ" ትላለች።

እንደ ዘሃራ ያሉ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎች ከሌባኖስ መንግሥት ጋር በመሆን የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ነገ ሊደረግ በነበረ በረራ ለማውጣታ ታቅዶ የነበረው ቻርተር በረራ 'ላልተወሰ ጊዜ መራዘሙን' አቶ ዳንኤል ነግረውናል።

"ለነገ [ዓርብ ግንቦት 14] ታቅዶ የነበረው እና ቆንስላው ያዘጋጀው ቻርተር በረራ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። ነገር ግን ተሰርዟል ማለት አይደለም። እንደሰማሁት ከሆነ መዘጋጀት ያለባቸው ተጨማሪ 'ዶክመንቶች አሉ'። ሰነዶቹ ሲሟሉ በሚቀጥሉት ቀናት በረራው ይኖራል ብለን እናምናለን" ብለዋል አቶ ዳንኤል።

በሌባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ በበኩላቸው "ያላለቀ ጉዳይ ስላለ ነው። መውጫ ቪዛ ላይ ያላለቀ ነገር አለ። አዲስ አሰራር አምጥተው [የሌባኖስ መንግሥት] እሱን እያስጨርስን ነው። በቅርብ ጊዜ ይሄዳሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ አክሊሉ በቆንስላው በኩል ተመዝገው ከሌባኖስ ለመውጣት ለሚጠባበቁ ዜጎች፤ "በዚህ ቀን ትወጣላችሁ ብለን አልተናገርንም። ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ ብቻ ነው ያልነው" ይላሉ።