በደቡብ አፍሪካ አራስ ልጅ በኮሮናቫይረስ ምከንያት መሞቱ ተሰማ

የጤና ባለሙያ መመርመሪያ ይዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ።

በደቡብ አፍሪካ ከተወለደ ሁለት ቀን የሆነው አራስ በኮሮና ምክንያት መሞቱ ተሰማ። ይህም በደቡብ አፍሪካመበቫይረሱ ከሞቱ ግለሰቦች ሁሉ በእድሜ ትንሹ መሆኑን የአገሪቱ ጤና ሚንስትር ገልፀዋል።

የጨቅላው እናት ኮሮናቫይረስ እንዳለባት በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ሕጻኑ ከጊዜው ቀድሞ በመወለዱ ምክንያት የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ያስፈልገው ነበር ሲሉ የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚንስትር ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 ተይዘው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 339 የደረሰ ሲሆን ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ደግሞ 18 003 ደርሷል።

በደቡብ አፍሪካ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ እስከ 40 ሺህ ሰዎች ድረስ ሊሞቱ እንደሚችሉ ተተንብይዋል።

የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚንስትር ዶ/ር ዝዌሊ ማክሄዚ "በአሳዛኝ ሁኔታ በኮቪድ-19 ምክንያት ጨቅላ ሕፃን ሞቶብናል። ጨቅላው ከተወለደ ሁለት ቀን የሆነው ሲሆን መወለድ ካለበት ጊዜ ቀድሞ የተወለደ ነበር" ብለዋል።

እንዲሁም " ጨቅላው ሳንባው ላይ ችግር ስለነበረበት እንደተወለደ መተንፈሻ ተገጥሞለት ነበር" በማለት የሕጻኑን ህይወት ለማትረፍ ለተረባረቡ የጤና ባለሙያዎችና ለእናትየው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።

ቢቢሲ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ዳይሬክተር የሆኑትን ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግን በአፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ከሞቱ ሰዎች መካከል ይህ አራስ ህፃን በእድሜ ትንሹ መሆን አለመሆኑን ባጣራው መረጃ" እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት በአፍሪካ ይህ ጨቅላ በኮሮና ምክንያት የሞተ በእድሜ ትንሹ ሕፃን ነው" የሚል ምላሽ አግኝቷል።

በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከሞቱ ሌሎች ታዳጊዎች መካከል በዩናይትድ ኪንግደም የሞተው የሶስት ቀን ጨቅላ ሲገኝበት በሚወለድበት ወቅት እናትም ሆኑ ጨቅላ ሕፃኑ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተግለጿል።

ሕፃኑ ሲወለድ የልብ ምቱ በጣም ደካማ የነበረ ሲሆን ወደ ጭንቅላቱ በቂ ደምና ኦክስጅን አይሄድም ነበር ተብሏል።

በዚህም ምክንያት የተነሳ ኮቪድ-19 ለጨቅላው ሞት ሁለተኛ መሆኑ በሕክምና ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።

የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር በተጨማሪም እንደገለፁት በአገሪቱ ባለፉት 24 ሰዓታት ከተመዘገቡ 27 ሞቶች መካከል የሁለት ዓመት ሕፃን ይገኝበታል።

ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ስትሆን ግብጽና አልጄሪያ ደግሞ በኮሮና ምክንያት በሞቱ ሰዎች ቁጥር 680 እና 568 በማስመዝገብ ይበልጣሉ።

.