ኮሮናቫይረስ፡' 'ጨለምተኛው' ፕሮፌሰር "ዓለም ለ10 ዓመታት ትማቅቃለች" አሉ

ፕሮፌሰር ኖሪኤል ሮቢኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፕሮፌሰር ኖሪኤል ሮቢኒ

ኖሪኤል ሮቢኒ ስመ ጥር የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰር ናቸው። መጪውን ዘመን በመተንበይ ይታወቃሉ። ሆኖም ሰውየው በጎ በጎው ስለማይታያቸው 'ጨለምተኛው ኢኮኖሚስት' የሚል ቅጽል ተበጅቶላቸዋል።

ትንቢታቸው ጠብ አይልም የሚባሉት ፕሮፌሰር ሮቢኒ ከዚህ በፊት ባንኮችና የቁጠባ ቤት ገዢዎች በፈጠሩት ሀሳዊ የቢዝነስ ሽርክና የዓለም ኢኮኖሚ ይናጋል ብለው ከማንም በፊት ተንብየው ነበር፤ እንዳሉትም ሰመረላቸው። ይህ የሆነው በፈረንጆች 2008 የዛሬ 12 ዓመት ነበር።

ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ቀድመው ያዩት እኚህ ሰው ታዲያ ከሰሞኑ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኮቪድ-19 የፈጠረው ምስቅልቅል ቢያንስ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዓለምን ያናጋታል፤ የዓለም ምጣኔ ሃብትም ለ10 ዓመታት ይማቅቃል ብለዋል።

ሰውየው እንደሚሉት ይህ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ውሎ በዓመት ውስጥ ምጣኔ ሃብቱ ማንሰራራት ቢጀምርም ነቀርሳው ግን ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ይቆያል። እንዲያውም አንዳንድ የሥራ ዘርፎች ጨርሶውኑ ላያንሰራሩ እንደሚችሉም ተንብየዋል።

ወረርሽኙን ከ2008ቱ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ጋር ሲወዳደርም ሆነ በ1930ዎቹ ከተከሰተው የዓለም ክፉው የምጣኔ ሃብት ድቀት ጋር ሲተያይ የአሁኑ የከፋ እንደሆነ ሮቢኒ ያብራራሉ።

ያን ጊዜ ምርት በዓለም ላይ እንዲቀንስ ወይም የቀውሱን ምልክቶች በተግባር ለማየት ከችግሩ በኋላ ዓመታትን ወስዶ ነበር። ኮሮናቫይረስ ግን ከእነዚህ ሁለቱ ቀውሶችም በላይ ነው። በባህሪው ይለያል።

ያስከተለውን የምርት ማሽቆልቆልን በግላጭ ለማየት ዓመታት ወይም ወራት አልወሰደበትም። በሳምንታት ውስጥ በመላው ዓለም ምርት ተንኮታክቷል። ይህ የሚነግረን መጪው ዘመን ፍጹም ጭጋጋማ መሆኑን ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

"በዚያ ዘመን 3 ዓመት የወሰደው የምርት መንኮታኮት በዚህ ዘመን 3 ሳምንት ነው የወሰደበት።"

"ዩ" እና "ኤል"

ፕሮፌሰሩ ከምጣኔ ሃብት ቀውስ በኋላ የማገገሙን ሂደት ሲያስረዱ በሁለት የእንግሊዝኛ ሆሄያት ይመረኮዛሉ። ዩ እና ኤል ["U" እና "L"]። ዩ በእኛ ሀሌታው 'ሀ' ብለን ልንተረጉመው እንችላለን።

የሀሌታው ሀ የማገገም ሂደት የሚያሳየው አንድ ምጣኔ ሀብት በአንዳች መጥፎ አጋጣሚ ሲንኮታኮት ቀስ በቀስ መሬት ይነካል። ከዚያ ወደነበረበት ለመመለስ የሀሌታው ሀ ቅርጽን ይዞ ሲንፏቀቅ ቆይቶ፣ በብዙ አዝጋሚ ሂደት ምጣኔ ሃብቱ ይመለሳል። ይህ ሂደት ዓመታትን የሚወስድ ነው። ከዚህ የተሻለው ደግሞ በቪ "V" ይወከላል። ቶሎ ወድቆ ቶሎ የሚያንሳራራ ምጣኔ ሃብት።

አሁን የገጠመን ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤ ኮቪድ-19 ያስከተለው የምጣኔ ሃብት ድቀት የሀሌታው ሀ ቅርጽን ሳይሆን የእንግሊዝኛው ሆሄ "L"ን ወይም በእኛ የ"ረ" ቅርጽ የያዘ ነው። ይህም ማለት በአንድ ጊዜ ዘጭ ያለው ምጣኔ ሃብት ጨርሱኑ አያንሰራራም ወይም ለማንሰራራት አሥር ዓመት ይወስድበታል። 'ጨለምተኛው' ፕሮፌሰር እንዲያውም የኮቪድ-19 ተጽእኖ የመጪውን ዘመን ምጣኔ ሃብት በአይ ሆሄ "I" የሚወከል እንዳይሆን ይሰጋሉ። እንደወደቀ የሚቀር ኢኮኖሚ።

በፕሮፌሰሩ ትንቢት መሠረት በዚህ ወረርሽኝ ሥራ ያጡ ዜጎች ወደ ሥራቸው የመመለስ ዕድላቸው አነስተኛ ነው። ከተመለሱም በጊዝያዊ ሠራተኝነት እንጂ ቋሚ ሥራ የሚያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ከደመወዝ ውጭ ያሉ ጥቅማጥቅሞች ከዚህ በኋላ የሚታሰቡ አይሆኑም። በዝቅተኛና መካከለኛ የቅጥር ሥራ ላይ ያሉ ሰዎችም ቢሆን የሥራ ዋስትና አይኖራቸውም። ይህ በብዙ የምርት ዘርፎች ላይ ይታያል ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ከዚህ በኋላ ምርት አይጨምርም፤ የአገራትም ሆነ የኩባንያዎች እድገት ባለበት እርገጥ ይሆናል፣ ሰዎች ገቢያቸው ይደቃል፤ ገበያ ይተናል፣ ፍላጎት ይከስማል።

"ሰዎች ስለ ቢዝነስ መልሶ መከፈት ያወራሉ፤ ቢከፍቱስ ማን ይገዛቸዋል? ጀርመን ሱቆችን ከፈተች፤ ገዢ ግን የለም። ቻይና ትልልቅ የንግድ መደብሮቿ ክፍት ናቸው፤ ማን ይገዛቸዋል? ከፍተው ነው የሚዘጉት፤ በረራዎች ተስተጓጉለዋል…ይህ ሁኔታ ለዓመታት የሚቀጥል ነው የሚሆነው" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ፕሮፌሰር ሮቤኒን ከበለጸጉ አገራት ይልቅ ታዳጊ የእሲያ ምጣኔ ሃብት በሁለት እግሩ ለመቆም የተሻለ እድል እንዳለውም ተናግረዋል።

"ዓለም ለሁለት ትከፈላለች"

ፕሮፌሰር ኖሪኤል ሮቢኒ ሌላው ትንቢታቸው ዓለም ልክ እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በሁለት ግዙፍ እድሮች እንደሚሰባሰብ ነው። የእድሮቹ አባቶች የሚሆኑትም ቻይናና አሜሪካ ይሆናሉ ይላሉ።

ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸው እየሻከረ እንደሚሄድና የራሳቸውን የምጣኔ ሃብት አጋሮች ማሰባሰብ እንደሚጀምሩ አስምረውበታል። አብዛኛዎቹ የእሲያና ታዳጊ አገራት ከእነዚህ ሁለት አገሮች ወደ አንዱ እድር እንዲገቡ የሚገደዱበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ፕሮፌሰሩ ተንብየዋል።

"ሁለቱ የእድር አባቶች ወይ ከእኔ ጋር ነህ፣ ከእኔ ካልሆንክ ደግሞ ከጠላቴ ጋር ነህ ማለት ይጀምራሉ። ይህ ማለት ወይ የእኔን 5ጂ ትጠቀማለህ፣ አልያም የጠላቴን፤ ወይ የእኔን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትጠቀማለህ ወይም የጠላቴን…እየተባለ ሁለት ዓለም ይፈጠራል። ታዳጊ አገራትም በሁለት ቢላ መብላት አይፈቀድላቸውም" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ከኒውዮርክ ቤታቸው ሆነው ቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር ሮቢኒ ጨለምተኛው ፕሮፌሰር ስለመባላቸው አስተያየት ሲጠየቁ "ከዚያ ይልቅ እቅጩን ነጋሪው ፕሮፌሰር የሚለው ስም ይመጥነኛል" ብለዋል።