የጣልያኑ ዕድሜ ጠገቡ ስታዲየም ሊፈርስ ነው

ሳንሲሮ ስታዲም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

በ94 ዓመት ውስጥ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረገለት ሳንሲሮ

ሳንሲሮ ስታዲየም የጣሊያን ሁለት የእግር ኳስ ቡድኖች በጋራ የሚያዙበት የኳስ ሜዳ ነው። ኤሲሚላንና ኢንተር ሚላን።

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1926 ነበር የተገነባው። ዝነኛው ሳንሴሮ ስታዲየም ታዲያ ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኗል፤ ይፍረስ አይፍረስ የሚለው ክርክር ለዓመታት የዘለቀ ሲሆን የጣሊያን ቅርስ ጥበቃ ስታዲየሙ ቢፈርስ ተቃውሞ የለኝም ብሏል።

ይህ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ውሳኔ ስታዲየሙ ፈርሶ አዲስና ዘመናዊ ስታዲየም ለማቆም የመጀመሪያው ሕጋዊ መንገድ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ 80 ሺህ ተመልካችን የሚይዝ ታሪካዊ ስታዲየም የሚፈርሰው አዲስና ዘመናዊ የሆነ ነገር ግን 60 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ ስታዲየም እንዲገነባ ስለተፈለገ ነው።

ባለፈው ዓመት ሁለቱ የጣሊያን ቡድኖች ከዚሁ ስታዲየም አጠገብ በጋራ አዲስ ስታዲም ለመገንባት ጥያቄ አቅርበው ነበር። አሁንም ግንባታውን የሚያካሄዱት ሁለቱ ክለቦች በጋራ ነው።

ሳንሲሮ ቅርስ ሆኖ መጠበቅ አለበት በሚሉና ምንም እንኳ ታሪካዊ ቢሆንም ዕድሜ አስገርጅፎታል በአዲስ መተካት አለበት በሚሉ መካከል ለዓመታት ክርክር ተደርጎበታል።

እነ ቫንባስተን፣ ራይካርድ፣ ማልዲኒ፣ ሼቪሼንኮና ካካ የኳስ ጥበባቸውን ያሳዩበትን ሳንሲሮን አፍርሶ ማስወገድ በፍጹም የማይዋጥላቸው ተመልካቾች ቁጥር ቀላል አይደለም።

የሚላን ከተማ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ግን ሳንሲሮ ፈርሶ አዲስ ስታዲየም ቢገነባ እንደማይቃወም አስታውቋል።

ስታዲየሙ ከተገነባ በኋላ የተሟላ ጥገና የተደረገለት በፈረንጆቹ 1990 ላይ ነበር።

ተመልካቾች እንደሚናገሩት አሁን አሁን ሳንሲሮ ስታዲየም ደጋፊዎች እየዘለሉ ሲጨፍሩበት አንዳች መንቀጥቀጥ ማሰማት ጀምሯል። ይህ ደግሞ የደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱበት አድርጓል።

ሳንሲሮ እንዲፈርስ የተፈለገበት ሌላው ምክንያት ገቢ ማምጣት አለመቻሉ ነው ይላሉ የኤሲሚላን ፕሬዝዳንት ፓውሎ ስካሮኒ።

"በርካታ ስታዲየሞች በአቅራቢያቸው የንግድ ሱቆች ስላሏቸው እና ለትላልቅ የንግድ ተቋማት የሚሆን መቀመጫ ስለሚያዘጋጁ ከፍተኛ ገቢ ያስገባሉ። ሳንሲሮ የድሮ ስታዲም ከመሆኑ አንጻር ይህን በማጣቱ ማስገባት የሚችለው 34 ሚሊዮን ዩሮ ብቻ ነው። አርሴናል ከመቶ ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያስገባል።"

ቦታውን በባለቤትነት የያዘው የሚላን ማዘጋጃ ቤት ይህ ካምቦሎጆ ቢፈርስ ምንም የታሪክ መደምሰስ የሚያስከትል አይደለም ሲል ስምምነቱን ገልጸዋል።

የሚላን ከተማ ከንቲባ ጁሴፔ ሳላ በበኩላቸው ይህ ስታዲየም ጨርሶዉኑ ከሚፈርስ የሆነ ክፍሉ ለታሪክ ቢጠበቅ ይመርጣሉ። የትኛው የስታዲሙ ክፍል ይጠበቅ የሚለው ግን የሚያግባባ ጉዳይ አልሆነም።

በርካታ የሁለቱ የጣሊያን ቡድን ደጋፊዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ኳስ የተመለከቱበትና ብዙ ትዝታን ያሳለፉበት በመሆኑ ሳንሲሮ እንዲፈርስ መፍቀድ ልባቸው የሚችለው ጉዳይ አልሆነም።

የኤሲሚላን ፕሬዝዳንት ፖውሎ ስካሮኒ እንደሚሉት "ሁላችንም ትዝታ አለብን፤ ሁላችንም ለዚህ ስታዲየም ስሜታዊ ነን። መፍትሄው እሱን አፍርሶ አዲስ ትዝታን መገንባት ነው።"

ሳንሲሮ አሁን 94 ዓመቱ ነው።