ምዕራብ ኦሮሚያ፡ ለልጃቸው ስንቅ ለማድረስ ወጥተው አስከሬኑን መንገድ ላይ ያገኙት እናት እሮሮ

ወጣት ለሊሳ ተፈሪ

የፎቶው ባለመብት, የቤተሰብ ፎቶ

"ልጄ ታስሮ ወደሚገኝበት ቦታ እንጀራ ይዤለት ስሄድ አጣሁት . . . የልጄ አስክሬን በሸራ ተጠቅልሎ ሜዳ ላይ ተጥሎ አገኘሁ" ሲሉ በምዕራብ ኦሮሚያ ልጃቸው በጸጥታ ኃይል የተገደለባቸው እናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወጣት ለሊሳ ተፈሪ በምዕራብ ወለጋ ዞን የገንጂ ወረዳ ነዋሪ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት በአካባቢው ተሰማርቶ በሚገኘው የመንግሥት ኃይል በቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሁለት ቀናት በኋላ ሞቶ መገኘቱን የለሊሳ ቤተሰቦች ይናገራሉ።

ግንቦት 2/2012 ዓ.ም ከገበያ ስፍራ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ለሊሳ ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ግንቦት 4 አስክሬኑ ሜዳ ላይ ተጥሎ መገኘቱን ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ጫልቱ ሁንዴሳ እና አባቱ አቶ ተፈሪ ዱጉማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሊሳ ትዳር ለመመስራት በዝግጅት ላይ እንደነበረ እና እጮኛውን ለማግኘት በወጣበት ወቅት መያዙን የቤተሰብ አባላቱ ይናገራሉ።

'እንደወጣ ቀረ'

የለሊሳ ተፈሪ እናት ወ/ሮ ጫልቱ ሁንዴሳ እንደሚሉት ከሆነ፤ ለሊሳ አዲስ አበባ ከተማ የምትገኝ እህቱ ጋር ይኖር እንደነበረ እና ወላጆቹ ወደሚኖሩበት አከባቢ ከተመለሰ ሁለት ወራት አልሆነውም።

በቀጣዩ ዓመት ለማግባት አቅዶ የነበረው ለሊሳ፤ በጉዳዩ ላይ ከእጮኛው ጋር ለመመካከር ገንጂ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባለ የገበያ ቦታ ቀጠሮ ይዞ እጮኛውን ለመግኘት እንደወጣ አለመመለሱን ይናገራሉ ወ/ሮ ጫልቱ ይናገራሉ።

"ቀኑ ሰንበት ነበር። ከእሷ ጋር እያወራ ገበያ ላይ ያዙት። ታስሮ ይገኘበታል ወደተባለው ቦታ እንጀራ ይዤለት ስሄድ ከዚያ አጣሁት። 'ማንን ነው የምትፈልጉት?' ሲሉ ጠየቁኝ 'ለሊሳ ተፈሪ' ብዬ ስመልስላቸው 'እሱ ከዚህ ወጥቷል' አሉኝ።"

ወ/ሮ ጫል ልጃቸው የት እንደተወሰደ ደጋግመው ሲጠይቁ በአንድ የጸጥታ አባል ተመነጫጭቀው እና 'አጸያፊ ስድብ' ተሰድበው መባረራቸውን ይናገራሉ።

የምስሉ መግለጫ,

የለሊሳ ወላጆች

"የልጄ አስክሬን በሸራ ተጠቅልሎ ሜዳ ላይ ተጥሎ አገኘሁ"

ከዚያ በኋላ ለሊሳ ታስሮ ነበር የተባለበት አከባቢ ያሉ ሰዎች 'ጠዋት ላይ እጁን አስረውት [የለሊሳን] ወደ ጉደያ [በቅርበት ያለ ስፍራ] ወስደውታል እዚያ ፈልጉ' ይባላሉ።

ከዘያ "ለእሱ ይዤ የወጣሁትን እንጀራ አስቀምጬ ፍለጋ ስወጣ፤ የልጄ አስክሬን በሸራ ተጠቅልሎ ሜዳ ላይ ተጥሎ አገኘሁ። የልጄን ሞት እዚያው ተረዳሁ" በማለት የለሊሳ እናት ተናግረዋል።

ወላጆቹ እንደሚሉት የለሊሳ ህይወት ያለፈው በጥይት ተመቶ ነው።

"ያለ ለሊሳ ማን አለኝ?" ሲሉ የሚጠይቁት ወ/ሮ ጫልቱ ለሊሳ አያቱን ጨምሮ ወላጆቹን ይረዳ የነበረው እሱ መሆኑን ይናገራሉ።

ለሊሳ ለምን ታሰረ?

ከዚህ ቀደም ለሊሳ ታስሮም ሆነ ጥፋተኛ ተብሎ ተከሶ እንደማያውቅ ወላጆቹ ይናገራሉ። አሁን ተይዞ በነበረበት ወቅትም ወደ ፍርድ ቤት አለመወሰዱን ይናገራሉ። ለምን እንደተሳረም ከሚመለከተው አካል የተነገራቸው ምንም መረጃ የለም ይላሉ።

"ፍርድ ቤት ሳይቀርብ፣ ጥፋተኛ ሳይባል፣ ሞት ሳይፈረድበት በመንግሥት ጦር ተገደለ" ይላሉ ወላጅ አባቱ አቶ ተፈሪ ዱጉማ።

እናቱ እንደሚሉት ለሊሳ 'ቻይና ካምፕ' ተበሎ በሚጠራው ቦታ ታስሮ እያለ፤ ለሊሊሳ ምግብ ይዘው የሄዱ ወጣቶችን "ወታደሮች 'እሱ ሸኔ ነው' ብለው አበረሯቸው።"

ወላጅ እናቱ ግን ልጃቸው የሸኔ አባል ስለመሆኑ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ታጠቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን መንግሥት 'ሸኔ' ሲል ይጠራቸዋል።

እነዚህ ታጣቂዎች የቀድሞ የኦነግ ጦር አባላት ነበሩ ሲሆን መንግሥት እና የአገር ሽማግሌዎች የቡድኑ አባላት ትጥቅ ፈተው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ለማስገባት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል።

የምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ጸጥታ መደፍረስ

ባለፉት ሳምንታት በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ መደፈረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙት ገንጂ እና ላሎ አሳቢ በሚባሉ ወረዳዎች ግጭቱ ተባብሷል ይላሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱበታል በሚባለው ደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ አካባቢ በመንግሥት ኃይሎና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መኖሩ ነዋሪዎችና የአከባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ገልፈው ነበረ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጉጂ ዞን በተፈጠረ ግጭት 12 የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውን የዞኑን ምክትል አስተዳዳሪ ጠቅሰን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

የምስሉ መግለጫ,

የለሊሳ ተፈሪ የቀብር ስፍራ

የመንግሥት ምላሽ

በወጣቱ ግዳያ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የምዕራብ ወለጋ አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡመታ "ይህ ጉዳይ የቆየ ነገር ነው። ለመገናኛ ብዙሃንም ማብራሪያ ስሰጥ ነበር። አሁን የልማት ሥራ ግምገማ እና የሥራ እድል የመፍጠር ጉዳዮች ላይ ተጠምደን ነው ያለነው። በእዚህ ጉዳዮች ላይ ብትጠይቀኝ ይሻላል" በማለት በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ምላሽ እንደሌለ በመናገር የእጅ ስልካቸውን ዘግተዋል።

አቶ ኤሊያ በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ባለፉት ቀናት ተከስቶ ከነበረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ለጀርመን ድምጽ "መንግሥት በአካባቢው የሕግ የበላይነት በማስከበር ላይ ይገኛል። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሕግን ከማስከበር ውጭጪ በነዋሪው ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም። በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እና ሸማቂዎች መካካል በነበረው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች ካሉ አጣርተን ይፋ እናደርጋለን" ማለታቸው ተዘግቧል።

የጀርመን ድምጽ በዚህ ዘገባው በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ከማክሰኞ ግንቦት 11 ጀምሮ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የአምስት ሰዎች ህይወት አልፏል ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል አበበ ገረሱን ስለጉዳዩ ብንጠይቅም "ከኃላፊቴ ተነስቻለሁ" ብለዋል። የኮሎኔል ገረሱ ከኃላፊነት መነሳት ግን በመንግሥት ይፋ አልተደረገም።

ቢቢሲ ከጥቂት ወራት በፊት በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ስላለው የጸጥታ ችግር የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላን በጠየቀበት ጊዜ በተወሰደው እርምጃ አካባቢዎቹ ከታጣቂዎች ነጻ ወጥቷል ብለው ነበር።