ኮሮናቫይረስ፡ አንዳንዶች በኮሮናቫይረስ ሌሎች ደግሞ በሐሳዊ ዜና ወረርሽኝ እየሞቱ ነው

ብሪያን ሊ ሆስፒታል አልጋ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Brian Lee hitchens

የምስሉ መግለጫ,

ሚስቱና ራሱ እስኪያዙ ድረስ ቫይረሱ የለም ብሎ ያስብ የነበረው ብሪያን ሊ

የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች ግብረ ኃይል በሐሳዊ ዜና (fake news) ምክንያት ሰው ይሞታል? ሲል ጠየቀ።

የማኅበራዊ ሳይንት ተመራማሪዎች ሐሳዊ ዜና፣ መላምታዊ ድምዳሜ፣ የሴራ ወሬ ብዙዎችን ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለው ይደመድማሉ። ምን ያህል እውነት ነው?

አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስ አውሮፓዊያን የሸረቡት ሴራ እንጂ እውነት አይደለም ብለው የሚያምኑ ሺህዎች ናቸው። አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስን የወለደው 5ጂ ኔትዎርክ ነው የሚሉ አሉ። አሁንም ድረስ 'አረቄ ኮሮናቫይረስን ድራሹን ያጠፈዋል' ብለው ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ የሚጨልጡ በርካቶች ናቸው።

ከኢትዮጵያ እስከ ማዳጋስካር፣ ከታይላንድ እስከ ብራዚል፣ ከአሜሪካ እስከ ታንዛኒያ በሐሳዊ ወሬ ያልናወዘ፣ መድኃኒት ያልጠመቀ የለም።

ሳይንስ መፍትሔ የለውም ብለው ከደመደሙት ጀምሮ አምላክ ያመጣው መቅሰፍት ነው ራሱ ይመልሰው ብለው ሕይወታቸውን በተለመደው መልኩ የቀጠሉ የዓለም ሕዝቦች ብዙ ናቸው።

የሐሳዊ ዜና ምስቅልቅል

ለምሳሌ ብሪያን ሊን እንውሰድ። 46 ዓመቱ ነው። ፍሎሪዳ በሚገኝ ሆስፒታል አልጋ ላይ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ሆኖ ለቢቢሲ ሲናገር ኮሮናቫይረስ መንግሥት ዜጎቹን ሊያዘናጋ የፈጠረው የፖለቲከኞች ሴራ ነው ብሎ ያምን እንደነበር ገለጧል።

"ሁለት ነገር ይሆናል ብዬ ነበር የገመትኩት፤ አንዱ እንዳልኩት የመንግሥት ማስቀየሻ ዘዴ ሆኖ ነበር የታየኝ። በኋላ ደግሞ 5ጂ ኔትዎርክ ነው በሽታውን ያመጣው ብዬ በጽኑ አመንኩ፤ ቀጥሎ በጽኑ ታመምኩ።"

ብሪያን ብቻውን አይደለም። ባለቤቱም እንደዛ ነበር ያመነችው። በኋላ ሁለቱም የአልጋ ቁራኛ ሆኑ።

ቫይረሱ ውሸት ነው ብላችሁ እንድታምኑ ያደረጋችሁ ምንድነው? ተብለው ሲጠየቁ "በፌስቡክ ያነበብነው ሐሳዊ ዘገባ ነው ጉድ ያደረገን" ብለዋል በአንድ ድምጽ።

ቫይረሱም ይገድላል፤ ሐሳዊ ዜናም ይገድላል።

የቢቢሲ የምርመራ ቡድን የሐሳዊ ዘገባዎችና የሴራ ሽረባዎች ያደረሱትን የጉዳት መጠን ለማወቅ በርካታ አገራትን አስሷል።

ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ስለመሆኑም ተረድቷል።

ለምሳሌ በሕንድ በኢንተርኔት የተለቀቀ ወሬ ሰው ተደብድቦ እንዲገደል አድርጓል። በኢራን በሐሰተኛ ወሬ ምክንያት መርዝ የጠጡ ብዙ ናቸው። በ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ላይ በተነዛው ወሬ የቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነሮች ተደብድበዋል፣ የስልክ እንጨቶች በእሳት ተለኩሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየወሰድኩት ነው ያሉት ሀይድሮክሲክሎሮኪን

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ምክር

በአሜሪካ አሪዞና የዓሳ ገንዳ ማጽጃ ኬሚካል ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል የሚል ዜና ያነበቡ ጥንዶች ኬሚካሉን ጠጥተው ሆስፒታል ገብተዋል።

ለዚህ አንዱ ተጠያቂ የሚሆኑት እንደመጣላቸው ይናገራሉ የሚባሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳይሆኑ አይቀሩም።

ዋንዳና ጌሪ ትራምፕ ስለሚያሻሽጡት ሀይድሮክሲክሎሮኪን በመጋቢት መጨረሻ ላይ ነበር የሰሙት።

ቤታቸው ውስጥ አንድ ተመሳሳይ ስም የተጻፈበት ጠርሙስ አገኙ።

ሀይድሮክሲክሎሮኪን አንዳች ተስፋ የሚሰጥ መድኃኒት እንደሆነ ቢነገርም የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ መድኃኒት ላይ የሚደረገው ምርምር እንዲቆም አዟል። ለዚህ ውሳኔ ያበቃው በቅርብ የተደረጉ ምርምሮች እንዲያው በሽታው ገዳይ መሆኑን ስላመላከተ ነበር።

የዚህ መድኃኒት ፈዋሽነት ወሬ የተነዛው በመስከረም መጨረሻ በኢንተርኔት ላይ ነበር። አንዳንድ የቻይና ሚዲያዎች ይህ መድኃኒት ጸረ-ቫይረስ ስለመሆኑ የድሮ ያልታደሰ መረጃ ይዘው አራገቡት።

ከዚያ ቀጥሎ አንድ የፈረንሳይ ሐኪም ይህንኑ የሚያጠናክር ነገር ተናገሩ። ቀጥሎ የቴስላ መኪና መስራች ኤሎን መስክ ስለ መድኃኒቱ አዳንቆ አወራ። ዶናልድ ትራምፕ ተከተሉት። ወሬው ወደ ላቲን አሜሪካ ሄደና የአእምሮ ጤናቸው ያጠራጥራል ወደሚባሉት የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጄየር ቦልሶናሮ ጋር ደረሰ።

ከሁሉም የከፋ ጥፋት የሰሩት ግን ዶናልድ ትራምፕ ሳይሆኑ አልቀሩም። በጋዜጣዊ መግለጫቸውም ሆነ በትዊተር ሰሌዳቸው ስለ ሀይድሮክሲክሎሮኪን ሳይናገሩ ማደር አቃታቸው።

"ቆይ! ብትወስዱት ምን ትጎዳላችሁ?" ሲሉ አበረታቱ። "አንዲት ሴትዮ የእኔን ምክር ሰምታ ዳነች" አሉ። ጋዜጠኞች በጥያቄ ሲያጣድፏቸው ደግሞ "ከመሞት መድኃኒቱን ወስዶ መሰንበት አይሻልም?" ማለት ጀመሩ።

ግንቦት ላይ ደግሞ ትራምፕ መድኃኒቱን ራሳቸው እየወሰዱት እንደሆነ ተናገሩ። ይህን ሁሉ ንግግራቸውን ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሰፊ ሕዝብ ሰምቶ ያጋራዋል። ሚሊዮኖች ይነጋገሩበታል። ሺህዎች ይተገብሩታል።

በናይጄሪያ ይህን መድኃኒት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ታመው የሆስፒታል አልጋ በማጣበባቸው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል።

በሚያዚያ ወር በቬትናም የ43 ዓመት ጎልማሳ ይህንኑ መድኃኒት ወስዶ መርዝ ሆኖበት በሃኖይ ሆስፒታል እየተሰቃየ ይገኛል። አይኑ ቀልቶ፣ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ፣ የሚያየው ነገር ጨልሞት ነበር የመጣው ይላሉ የክሊኒከኩ ዳይሬክተር ዶ/ር ጉይን።

"ሰውየው እድለኛ ነው፤ ቶሎ ወደ ክሊኒካችን ባይመጣ ሕይወቱ አትተርፍም ነበር" ብለዋል።

ባልና ሚስቱ ጌሪና ዋንዳ እድለኞች አልነበሩም። ቤታቸው ጓሮ ሀይድሮክሲክሎሮኪን የሚል አይነት ጽሑፍ የነበረበትን ኬሚካል የትራምፕን ምክር ተከትለው በመጠጣታቸው ወዲያውኑ ነበር ራሳቸውን የሳቱት። መተንፈስ አቃታቸው። ጌሪ ሞተ፤ ዋንዳ ግን ሆስፒታል ተኝታለች።

ዋንዳ ካገገመች በኋላ እንደተናገረችው ለዚህ የዳረጋቸው ዶናልድ ትራምፕ ስለ ሀይድሮክሲክሎሮኪን መድኃኒት አብዝተው በመናገራቸው ለምን አልንሞክረውም በሚል ተበረታተው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በየዕለቱ ስለወረርሽኙ መግለጫ ይሰጣሉ

የአልኮል መርዝና ኢራን

በኢራን ደግሞ በመቶዎች የገደለው የአልኮል መርዝ ነው። የአልኮል መርዝ በሽታውን ሙልጭ አድርጎ ያጠፋል ሲባል ሰምተው ብዙዎች ለምን አንሞክረውም አሉ።

ያድናል የሚለው ነገር ከየት እንደተነሳ ባይታወቅም ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዳነበቡት ተናግረዋል።

ካምቢዝ ሱልጣኒጃድ የተባሉ የኢራን ባለሥልጣን እንደተናገሩት በዚህ የአልኮል መርዝ የሟቾች ቁጥር 800 ይጠጋል። ሁሉም ታዲያ ፌስቡክ ላይ ባነበቡት ነገር ተበረታተው ነው መርዙን የጠጡት።

ይህ የሆነው የአልኮል መጠጥ በሚከለከልባት ኢራን መሆኑ ደግሞ ሌላው አስገራሚ ምጸት ነው።

ቢቢሲ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ መርዛማው አልኮል ያድናል የሚለው ወሬ መጀመርያ የተሰራጨው በቴሌግራም ነበር።

ሻያን ሳንዳሪዛድ የቢቢሲ የጸረ-ሐሳዊ ዜና ቁጥጥር ግብረ ኃይል አባል ናት። እሷ እንደምትገምተው ነገሩ የኢራን ባለሥልጣናትን አሳፍሯቸው ነው እንጂ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በብዙ እጥፍ የበዛ ሊሆን ይችላል።

የቢቢሲ መርማሪ ቡድን ባረጋገጠው ሌላ ዜና እዚያው ኢራን ውስጥ የ5 ዓመት ልጅ በሐሳዊ ዜና ምክንያት አይነ ስውር ሆኗል። ወላጆቹ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል አረቄ መሰል አደገኛ መጠጥ አይኑ ላይ አፍስሰው ነው የገዛ ልጃቸውን ብርሃን ያጠፉት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ክፉኛ በበሽታው ከተጠቁት አገራት መካከል የሆነችው የኢራን ፕሬዝዳንትን ጨማሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት

ጓደኛዬ ሳሙና ጎርሷል

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀይድሮክሲክሎሮኪንን ብቻ አይደለም ሲያሻሽጡ የከረሙት። በሚያዚያ መጨረሻ ደግሞ የአልትራቫዮሌት ጨረር ቫይረሱን ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሚሰነዝሩት የግብር ይውጣ አስተያየቶች ኃላፊነት ወስደው አያውቁም። ሲሻቸው ፈርጠም ብለው በሐሳቡ ይገፉበታል። ሲሻቸው ደግሞ እንደዛ አላልኩም ብለው ሽምጠጥ አድርገው ይክዳሉ።

አንዳንዴ ደግሞ እረ እኔ የቀልዴን ነው እንደዛ ያልኩት ይላሉ። ዞሮ ዞሮ እያንዳንዱ ንግግራቸው የነፍስ ዋጋ ያስከፍላል። ለምሳሌ የንጽህና ኬሚካል ኮሮናቫይረስን ይከላከላል ከሚለው የትራምፕ ንግግር በኋላ በካንሳስ ያሉ አንድ ባለሥልጣን አንድ ዜጋ አንድ ሳሙና እንደዋጠ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር ዱንካን ማሩ በኒውዮርክ ኤልመሀረስ ሆስፒታል ሐኪም ናቸው። የትራምፕን ንግግር ተከትሎ የንጽሕና ኬሚካል የጠጡ በርካታ ህሙማንን ማከማቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ባለፈው ወር ብሪታኒያ ውስጥ በእሳት እንዲቃጠል የተደረገ የሞባይል ሰልክ ኔትወርክ ማማ

5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ ቫይረሱን ያመጣል የሚለው ሴራ

ሐሳዊ ዜናዎችና የሴራ ትንተናዎች የንብረት ጉዳትም አድርሰዋል። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም 70 የሚሆኑ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ማማዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ 5ጂ ቴክኖሎጂ ነው ቫይረሱን ያመጣው የሚለው ወሬ ነው።

በሚያዝያ ወር ኢንጂነሩ ዳይላን ፋረል ቫን መኪናውን ከተርማስተን ወደ ሌስተር እየነዳ ነበር። በሥራ የተወጠረበት ቀን በመሆኑ ትንሽ የሻይ እረፍት ለማድረግ እያሰበ ሳለ የተቃውሞ ድምጽ ወደሰማበት አቅጣጫ ዞር አለ።

መጀመርያ ያሰበው ተቃውሞው ወደ ሌላ ሰው ያነጣጠረ እንደነበረ ነው። ለካንስ "5ጂ ይውደም" የሚለው ተቃውሞ ወደሱ የሥራ መኪና ያነጣጠረ ነበር።

"አንደኛው ተቃዋሚ ወደእኔ ተጠግቶ ዘለፈኝ፤ አንተ ሞራል የሌለህ ሰው ነህ፤ 5ጂ ሕዝብ እየጨረሰ ነው" አለኝ። በጣም አስፈሪ ነበር፤ ሊደበድቡኝ ሲሉ ፈጣሪ ነው ያተረፈኝ፤ የመኪናዬ በር ዝግ ነበር።"

በ5ጂ ቴክኖሎጂ ዙርያ ብዙ የሴራ ትንተናዎች በድረ ገጾች ለዓመታት ሲነገሩ ነበር፤ ይህ ነገር ሄዶ ሄዶ ከኮሮናቫይረስ ጋር መገናኘቱ ግን አስገራሚ ነው።

ኮሮናቫይረስና የዘር ጥቃት

በመጋቢት ወር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በሰጡት መግለጫ ወረርሽኙ ወደ ዘር ጥቃት ሊዛመት እንደሚችል ገምተው ነበር።

የፈሩት ደርሷል። በርካታ እሲያዊያን በበርካታ የአሜሪካ፣ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገራት ውስጥ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በሽታውን ያመጣችሁብን እናንተ ናችሁ በሚል።

ለምሳሌ በሚያዚያ ወር ሦስት የሕንድ ሙስሊሞች በዴልሂ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሙስሊሞች በሽታውን አሰራጭተውታል የሚል ሐሳዊ ዜና ማኅበራዊ ሚዲያውን ሞልቶት ስለነበረ ነው።

ሌላ አንድ ወጣት በተመሳሳይ በሐሰተኛ ዜና የተነሳ ሲገደል ጓደኛው ቆስሏል።

በእንግሊዝ ደግሞ ነጭ ያልሆኑ የኮሮናቫይረስ በሽተኞች አልጋ አይሰጣቸውም፤ ባሉበት እንዲሞቱ እየተደረገ ነው የሚል ወሬ በመወራቱ ብዙ ችግር ተፈጥሮ ነበር።

ሕንድ ውስጥ በኢንዶር ከተማ ሐኪሞች አንድ ቫይረሱ እንዳለበት የተገመተን ሰው ለመውሰድ በሄዱበት በድንጋይ ተደብድበው ሕይወታቸው ለጥቂት ተርፏል። ምክንያቱ ደግሞ በዋትስአፕ የተሰራጨ ሐሰተኛ ወሬ ነው። ሐኪሞቹ የመጡት ጤነኛ የሆኑ ሙስሊሞችን ለመውሰድ ነው የሚል ነበር።

ከሐኪሞቹ መሀል ሁለቱ አካል ጉዳተኛ ሆነው ቀርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ,

ብሪያንና ባለቤቱ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አንድ ድግስ ላይ ታድመው

"አታካብዱ!" ሲል የነበረው ብሪያን

የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች አደገኛነታቸው ብቻ ሳይሆን ጥቅማቸውም የትየለሌ ነው።

ለምሳሌ ብሪያንን እንውሰድ። ብሪያን እንደ ሌሎች ሰዎች ቫይረሱ ውሸት ነው ብሎ አላመነም። ወይም በ5ጂ የመጣ በሽታ ነው ሲል አላሰበም።

እሱ ያሰበው ቫይረሱ እውነት ሆኖ ሳለ ነገር ግን መገናኛ ብዙሃን ነገሩን ከሚገባው በላይ አጋነውታል። ማኅበራዊ ሚዲያውም እያካበደ ነው ብሎ አሰበ።

ባለቤቱ የአስም በሽተኛ ናት። እርሱ ሾፌር ነበር። ሱፐርማርኬት እየሄደ በነጻነት እቃ ገዝቶላት ይመጣል። ራሱን ማግለል አስፈላጊ ሆኖ አላገኘውም።

ድንገት ቫይረሱ ያዘው። ደነገጠ። ባለቤቱንም ለአደጋ አጋለጣት።

በነገሩ በማዘኑ ወደ ፌስቡክ ገጹ በመሄድ ተናዘዘ። እኔን ያያችሁ ተቀጡ ሲል ጻፈ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በትልልቅ ሚዲያዎች ከሚነገሩ ማስጠንቀቂያዎች ይልቅ እንደ ብሪያን ያሉ ተራ ዜጎች የሚጽፏቸው ነገሮች የተሻለ ውጤትን ያስገኛሉ፤ ተአማኒነታቸውም ከፍ ያለ ነው።

በሐሳዊ ዜና ሕይወት ይጠፋል ሲባል ሐሰት አይደለም

በዚህ ጽሑፍ የተነሱት ምሳሌዎች እንጂ ጠቅላላ ጉዳትን አያስቃኙም። ኢንተርኔት የመረጃ ሱናሚ ነው። ፍሬውን ከገለባ መለየት አይቻልም። የመቆጣጠሪያ መንገዱም ቀላል አይደለም። ትዊተር በትራምፕ ሰሌዳ ላይ ሐሳዊ መረጃ ምልክት ማድረጉ አንድ እርምጃ ቢሆንም ነገሩ ውቅያኖስን በጭልፋ እንደማለት ነው።

ለዚህም ነው ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ሐሰተኛ መረጃን ኢንፎዴሚክ ሲል የሰየምው። ራሱን የቻለ በሽታ፤ ራሱን የቻለ ወረርሽኝ ሆኗል ለማለት ነው።

ባለፈው ዓርብ ሁለት ወጣቶች ወደ ኒውዮርክ ኩዊንስ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል በአምቡላንስ መጡ። አብረው ነበር የሚኖሩት።

"ከአንድ ሰዓት በኋላ አንደኛው ወጣት ዓይኔ እያየ ሞተ" ይላሉ ዶ/ር ፈርናንዶ። ሌላኛው በቬንትሌተር ነው እየተነፈሰ ያለው።

"ለምን ቶሎ ወደ ሐኪም ቤት እንዳልመጡ ስጠይቃቸው የሰጠኝ መልስ 'ፌስቡክ ላይ ቫይረሱ ተራ ጉንፋን ነው' የሚል ነገር በማንበባችነው ነው ብሎኛል።"

ክትባት አወስድም የሚሉ ዜጎች ሊፈጠሩ ይችላሉ

ቀጣዩ ስጋት እንደው ተሳክቶ ለተህዋሱ ክትባት ቢፈጠር እንኳ ሚሊዮኖች ለመከተብ ፍቃደኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።

አንዱ ምክንያት በፌስቡክ ገና ከወዲሁ የሚነዛው ወሬ ነው። መንግሥታት የሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ፈልገው ነው ቫይረሱን የፈጠሩት፤ አሁን ደግሞ በክትባት ሊጨርሱን ነው ብለው የሚያምኑ በርካታ ናቸው።

'ቢልጌትስ ሀብቱን ለመጨመር ሲል ነው ቫይረሱን ፈጥሮ ክትባቱን ያመጣው' ሊሉ የሚችሉ ሺህዎች አሉ።

በሴራ ትንታኔ ያምን የነበረው የፍሎሪዳው ብሪያን ከሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ መልዕክት አለኝ ይላል።

"አትጃጃሉ፤ እኔን አይታችሁ ተቀጡ!"