“ኢትዮጵያ ክትባቱ ሲገኝ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ አለባት” ዶ/ር ኢዮብ ገብረመስቀል

ዶ/ር ኢዮብ ገብረመስቀል

የፎቶው ባለመብት, DR. EYOB GEBREMESKEL

የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር ኢዮብ ገብረመስቀል

ኮሮናቫይረስ የበርካቶቻችን አኗኗር ከለወጠ ሦስት ወር አልፎታል። የዓለም ልሂቃን ለበሽታው ክትባት ወይም መድኃኒት ለማግኘት ቀን ከሌት መመራመራቸውን ቀጥለዋል።

አንዳንድ አገራት ለበሽታው ይሆናል ብለው ያመኑትን ክትባት በተለያየ ደረጃ እየሞከሩ ነው።

ቢሆንም አሁንም ድረስ ስለ ኮቪድ-19 ያልታወቁ እንዲሁም ገና በምርምር ላይ ያሉ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ለምሳሌ በሽታውን ከመከላከል አቅም (Immunity) ጋር በተያያዘ አጥኚዎች ገና መልስ ያላገኙላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ።

በሽታው ከየት መጣ፣ በሰውነታች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንዴት ያለ ነው? ዓለም በድህረ ኮሮናቫይረስ ምን ትመስል ይሆን? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎችን በዩናይትድ ኪንግደሟ ለንደን በሚገኘው ክዊንስ ሆስፒታል በድንገተኛ ክፍል ለሚሠሩት ዶ/ር ኢዮብ ገብረመስቀል አቅርበናል።

ቫይረሱ ሰውነትን የሚጎዳው እንዴት ነው?

ቫይረሱ የሚሰራጭባቸው አራት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። በሽታው ያለበት ሰው ሲስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲተነፍስ ቫይረሱ አየር ላይ በመንሳፈፍ ወደ ሌላ ሰው ይጋባል። ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ሲኖር በሽታው ይተላለፋል። በወረርሽኙ የተያዘ ግለሰብ የነካውን ማንኛውም ቁሳ ቁስ የሚነካ ሰውም ለበሽታው ይጋለጣል።

ዶ/ር ኢዮብ እንደሚናገሩት፤ አጥኚዎች እስካሁን ያልደረሱበት ቫይረሱ በደም፣ በሽንትና በአይነ ምድር ስለመተላለፉ ነው። እነዚህ ውስጥ ቫይረሱ እንዳለ ቢታወቅም የበሽታው መተላለፊያ መንገዶች ስለመሆናቸው ገና እየተጠና ነው።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው የሚያሳየውን ምልክት በደረጃ እንመልከት፦

ከአንደኛው ቀን እስከ አምስተኛው ቀን- ቫይረሱ በዋነኛነት ወደ ሰውነት የሚገባው በአፍንጫና በአፍ ነው። በአይን የሚገባበት ጊዜም አለ። በእነዚህ ቀናት ቫይረሱ የሚራባው በአፍንጫና በጉሮሮ ውስጥ ነው። የአፍንጫ መታፈን፣ የንፍጥ መንጠባጠብ፣ ትኩሳትና ሌላም የጉንፋን አይነት ምልክት ሊሰማ ይቻላል።

የበሽታው ምርመራ ከአፍንጫና ከጉሮሮ በሚወሰድ ናሙና የሚካሄደውም ለዚህ ነው።

ከአምስተኛው ቀን እስከ ሰባተኛና አስረኛ ቀን- ቫይረሱ ከአፍንጫና ከጉሮሮ በመተንፈሻ ትቦ በኩል አርጎ ወደ ሳምባ ይወርዳል። በዚህ ወቅት ይደክማል። ሳል ይጀምራል። ትኩሳት ከፍ ይላል፤ ሲብስም ያንቀጠቅጣል።

ከአስረኛ ቀን ወዲያ- አደገኛ ወቅት ነው። ቫይረሱ ሳምባ ውስጥ የአየር መቀያየሪያ ወንፊቶች (Alveoli) ያጠቃል። እነዚህ ለመተንፈስ አስፈላጊ የሳምባ አካላት ናቸው። ቫይረሱ አስከትሎም የሰውነት ህዋሳትትን ይወራል። ሰውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚ ቫይረስ ጋር ሲገናኝ አዲስ ስለሚሆንበት እንዴት ማጥፋት እንዳለበት አያውቅም። ግን ቫይረሱን ይወጋል። ይህ ሳምባ ውስጥ የሚደረገው ትግል አንዳንዶችን ሕይወታቸውን ያሳጣል።

በመጨረሻ የአየር መቀያየሪያ ወንፊቶች በውሃና በመግል ይሸፈናሉ። ታማሚዎች መተንፈስ ያዳግታቸዋል። አንዳንዶች ኦክስጅን ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለመተንፈስ የሚረዳ መሣሪያ (Ventilator) አጋዥ ነው።

ወንፊቶቹ ሲጎዱ ኦክስጅን በጣም የሚያስፈልጋቸው አዕምሮ፣ ልብ፣ ኩላሊት አቅም ያጣሉ። የልብ መድከም፣ የአዕምሮ መዛል ወይም መወዛገብ፣ ሰመመን፣ ራስን መሳትም ሊከተል ይችላል።

ዶ/ር ኢዮብ እንደሚናገሩት፤ ኮሮናቫይረስ በያዛቸው ሰዎች ላይ አዲስ የታየው ነገር በልብና በሳምባ መካከል ያለው የደም ዝውውር መርጋቱ ነው። ይህም እጅግ አደገኛ ነው።

ቫይረሱ በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ ለምን ያህል ጊዜ ይኖራል?

በሽታው በግንባር ቀደምነት የሚተላለፈው በትንፋሽ ነው። ጉዳት የሚያመጣው የመተንፈሻ ስርዓት ላይ ነው። ስለዚህም ምግብ ስንበላ ጨጓራችን ውስጥ ቢገባ ምንም ችግር እንደማያመጣ ዶክተሩ “ኮሮናቫይረስ ስስ ስለሆነ የጨጓራ አሲዳችን ያሟሟዋል” በማለት ያስረዳሉ።

በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ ምን ያህል መቆየት ይችላል የሚለው አሁንም ድረስ እየተጠና ነው።

ዶ/ር ኢዮብ እንደሚሉት፤ ከ18 ዓመታት በፊት ተነስቶ የነበረውን የሳርስ በሽታ መነሻ በማድረግ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ኮሮናቫይረስ በፕላስቲክና በብረት ላይ እስከ 72 ሰዓት ይቆያል። መዳብ ላይ አራት ሰዓት፣ ካርቶን ላይ 24 ሰዓት፣ መስታወት ላይ አራት ቀን፣ እንጨት ላይ አራት ቀን እና ወረቀት ላይ አራት ቀን ይቆያል።

“ስናስልና ስናስነጥስ ደግሞ አየር ላይ ለሦስት ሰዓት ይቆያል” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሚመከር ምግብ አለ? አንዳንድ የደም አይነት ያላቸውን በበለጠ ያጠቃል የሚባለውስ እውነት ነው?

የድንገተኛ ክፍል የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ኢዮብ፤ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል በተለየ የሚመከር ምግብ ባይኖርም የተመጣጠነ ምግብ ሁሌም ያስፈልጋል ይላሉ። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያጎለብታልና።

በበሽታው ላለመያዝ እጅን አዘውትሮ መታጠብና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዳሉ ሆነው፤ የበሽታው ምልክት የሚታይበት ሰው ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፍ ራሱን ማግለል ይገባዋል።

ለወረርሽኙ በግንባር ቀደምነት ተጋላጭ የሆኑ ስኳር፣ ደም ብዛት፣ የኩላሊት በሽታና ልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች ህመማቸውን በአግባቡ መቆጣጠር አለባቸው።

“የደም ብዛት መድኃኒት መውሰድ፣ የስኳር መጠንን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። ችላ ካሏቸው ግን ሰውነታቸው ኮሮናቫይረስን ሊከላከል አይችልም።”

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ማድረግ የበሽታውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። በገበያ ሥፍራ፣ አውቶብስና ታክሲ ላይ፣ በእምነት ተቋማት ጭምብል ማድረግ ይመከራል።

በተጨማሪም እንደ አሽከርካሪዎች፣ ነጋዴዎች ያሉና ሥራቸው ከብዙ ሰው ጋር የሚያገናኛቸው፣ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦች ጭምብልና ጓንት እንዲያደርጉ ይመከራል።

በሌላ በኩል ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጋለጥ የደም አይነት አለ? የሚለው ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ ሲናፈስ ነበር። ዶ/ር ኢዮብ፤ “ይህ በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ አይደለም” ይላሉ።

ከ18 ዓመታት በፊት የሳርስ በሽታ ሲሰራጭም መሰል መረጃ ተሰራጭቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን “ሰዎች ይህን ሰምተው የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ሊቀንሱ፣ ሊያዘናጉም አይገባም” ሲሉ ይመክራሉ።

ኮቪድ-19 ቻይና ውስጥ ሲከሰት ይወጡ የነበሩ መረጃዎች በሽታው በዋናነት እድሜያቸው የገፋ ሰዎችንና የተለያዩ በሽታዎች ያሉባቸውን እንደሚያጠቃ ያሳይ ነበር።

አሁን ግን ምንም በሽታ የሌለባቸውንና ወጣቶችንም ማጥቃቱ አስፈሪ እንዳደረገው ሀኪሙ ይገልጻሉ።

“በእድሜ የገፉ ማለትም 55 ዓመትና ከዛ በላይ የሆኑ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። በጠና ሊታመሙ ይችላሉ። እኔ ሳክማቸው የነበሩ የ90 እና 91 ዓመት ሴቶች ሞተዋል። በተለያየ ምክንያት የሰውነት መድህናቸው ዝቅ ያለ (Immunosuppressed) ተጋለጭ ናቸው። ለምሳሌ ኤችአይቪ፣ ካንሰር፣ የቁርጭምጭሚት ህመም፣ የቆዳ በሽታ ያለባቸው ይጠቀሳሉ።”

የፎቶው ባለመብት, DR EYOB GEBEREMESKEL

የምስሉ መግለጫ,

ዶክተር እዮብ ገብረ መስቀል (ከመሃል) ከባልደረቦቻቸው ጋር

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ

ኮቪድ-19 በምጣኔ ኃብት የበለጸጉ አገራትን የጤና ሥርዓት አቃውሷል። ሆስፒታሎች ማስተናገድ ከሚችሉት በላይ ህሙማን በላይ ያሉባቸው አገራትም ብዙ ናቸው።

በሽታው ያልጠናባቸው ሰዎች ራሳቸውን አግልለው በቤት ውስጥ እንዲያገግሙ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች አሉ። ይህም በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች ላለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል።

አንድ ሰው ትኩሳት ሲኖረው፣ ጣዕምና ሽታ የሚለይባቸው ህዋሳት አልሠራ ሲሉት፣ አፍንጫውና ጉሮሮው ሲታፈን፣ የጀርባና የእግር መዳከም ሲሰማው ራሱን ማግለል አለበት። ቢያንስ ለ14 ቀናት መቆየት ይገባዋል።

ዶ/ር ኢዮብ እንደሚሉት፤ በ14 ቀን እየተሻለው ወይም በሽታው እየጸናበት ይሄዳል። አንዳንዴ ያገገመ ቢመስልም እስከ 21 እስከ 28 ቀንም ቫይረሱ ሊኖርበት ይችላል።

“የበሽታው ምልከት ያለው ሰው ጭምብል ማድረግ አለበት። ከቤተሰቡ ጋር ንክኪ ማድረግ የለበትም። ተቀራርበው ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት የለባቸውም። በሽታው ያለበት ሰው ከሌለበት ሰው ጋር ከ15 ደቂቃ በላይ ከቆየ በሽታው ሊተላለፍ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። እጅ በተደጋጋሚ መታጠብ እና ግለሰቡ የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች በሳሙና እና ለብ ባለ ውሃ ማጠብም አስፈላጊ ነው። ቫይረሱ ስስ ነው። ሳሙናና ውሃ ሲነካው ይፈረካከሳል።”

ባለሙያው እንደሚናገሩት፤ ብዙ በለይቶ ማቆያ ያሉ ሰዎች ከሰባት ቀን በኋላ ቢሻላቸውም የሚብስባቸውም አሉ። በሽታው የሚብሰውና አደገኛ የሚሆነው ከሰባተኛ እስከ 12ተኛ ባለው ቀን መካከል ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በነዚህ ቀናት ውስጥ እየተሻለው ካልመጣ፣ እየተዳከመ ከሄደ በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ አለበት።

ግለሰቡ ተዳክሞ ወይም የሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ወደ ሆስፒታል ከሄደ ሊደረግለት የሚችለው ድጋፍ ውስን ስለሆነ ከሰባት ቀን በኋላ ከፍተኛ ክትትል እንደሚያሻም ያክላሉ።

ከበሽታው ማገገም ምን ማለት ነው?

በበሽታው የተያዙ ሰዎች በድጋሚ ሊያዙ ይችላሉ ወይስ በሽታውን የመከላከል አቅም (Immunity) ያዳብራሉ? የሚለው ገና ምርምር እየካሄደበት ነው።

ዶ/ር ኢዮብ፤ ከሌሎች በሽታዎች በተገኘ እውቀት መሠረት ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ለአጭር ጊዜ በሽታውን የመከላከል አቅም ያዳብራሉ ይላሉ። ሀሳቡን እንዲህ አብራርተውታል. . .

“ነገር ግን ለረዥም ጊዜ የሚሆን በሽታን የመከላከል አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም። በክረምት ከሚይዘን ጉንፋን (Seasonal Flu) ጋር ተመሳሳይ ባህሪ አለው። አንድ ሰው በዚህ ዓመት ጉንፋን ከያዘው ብዙ ጊዜ በድጋሚ ጉንፋኑ አይዘውም። ምክንያቱም በዚህ ዓመት ያለው የጉንፋን ቫይረስ ተመሳሳይ ነው።

በሚቀጥለው ዓመት ግን ቫይረሱ ይቀየራል። ሰውየው ለሚቀጥለው ዓመት ቫይረስ የሚሆን በሽታ የመከላከል አቅም ስለማይኖረው በበሽታው ይያዛል። ኮሮናቫይረስም ተመሳሳይ ነው የሚል ግምት አለ።

ተመራማሪዎች ክትባት ለማግኘት እየተጣጣሩ ያሉት ለዚሁ ነው። ክትባት ሰውነት ሁሌ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ያደርጋል። Antibody Test [ፀረ እንግዳ አካላት] ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ትግል በከፍተኛ ደረጃ ወደፊት ይወስደዋል።”

ኮሮናቫይረስ ይጠፋል?

ዓለም በድህረ ኮሮናቫይረስ ምን ትመስል ይሆን? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው። ወረርሽኙ ከምድረ ገፅ ይጠፋል ወይስ አኗኗራችንን እስከወዲያኛው ቀይሮ አብሮን ይኖራል? የሚሉትም መልስ አላገኙም።

ዶ/ር ኢዮብ ሌሎች ተመሳሳይ ቫይረሶች እና በሽታዎችን መነሻ አድርገው እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ አንድ ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ከጀመረ ወይም ከለመደ በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አይቻልም። ኮሮናቫይረስ ወቅት ጠብቆ እንደሚመጣ ጉንፋን (Seasonal Flu) ሆኖ ይቆያል።

“ሆኖም ግን አሁን የሚያደርስብን አይነት ጉዳት ያደርስብናል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱን የብዙዎቻችን ሰውነት እየለመደው ይመጣል። ክትባቶችና በድኃኒቶች መፈጠራቸውም አይቀርም” ሲሉ ያብራራሉ።

የሰው ልጆችን ሲቀጥፉ የነበሩ በሽታዎች ብዙዎቹን መቆጣጠር ችለናል።

በዶክተሩ ገለጻ፤ ባለፈው 20 ዓመት ብቻ ኮሮናቫይረስ ሲከሰት ሦስተኛው ነው። ኮሮናቫይረስ 1፣ ኮሮናቫይረስ 2፣ ሜርስ (Middle East Respiratory Syndrome) መከሰታቸውን ያጣቅሳሉ። ሜርስ ከሌሊት ወፍ በግመሎች አልፎ ሰውን ያጠቃ በሽታ ነው።

“እነዚህ ቫይረሶች የመጡበት የሌሊት ወፍ ወደ 500 የሚሆኑ ሌሎች ቫይረሶች አሉት። ከእንስሳ እየዘለሉ ወደ ሰው የሚመጡ ቫይረሶች ወደፊትም ይገጥሙናል።”

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ከእንቅስቃሴ ገደብ መነሳት በኋላ ዓለም ምን ትመስል ይሆን?

Herd Immunity (ኸርድ ኢሚውኒቲ) ምንድን ነው? ለኮሮናቫይረስ ይሠራል?

ይህ አንድ በሽታ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳይሰራጭ በሽታውን የመቋቋም አቅም መገንባት ማለት ነው። በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የሚሰማው ኸርድ ኢሚውኒቲ ለኮሮናቫይረስ ይሠራል ወይ? ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ኢዮብ “መፍትሔ አይሆንም። ፍትሐዊ አይደለም። ያለንበትን ወቅት ያሻግረናል ብዬም አላምንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ይህ ማኅበረሰባዊ በሽታ የመከላከል አቅም ሊገነባ የሚችለው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው በክትባት ነው። ለምሳሌ ፖልዮ፣ ፈንጣጣ፣ ኩፍኝን ለመሰሉ በሽታዎች ክትባት በመስጠት በማኅበረሰቡ በሽታው እንዳይሰራጭ ማድረግ ተችሏል።

ሁለተኛው መንገድ አንድን ማኅበረሰብ ለበሽታው አጋልጦ፣ ከተጋለጡት ውስጥ የተረፉት ወይም ያልሞቱት በተፈጥሮ በሽታን የመቋቋም አቅም መገንባት ነው። ይህ ለኮቪድ-19 እንደማይሠራ እንዲህ አብራርተውልናል. . .

“በሽታው እንደልቡ እንዲፈነጭ በማድረግ፣ ከዛ የተረፈው ማኅበረሰብ ሰውነቱ ጥንካሬ ይገነባል የሚለው አያስኬድም። ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ እድሜያቸው የገፋ፣ ህመም ያለባቸውና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የደከመ (Immunosuppressed) ሰዎችን ለይቶ በማስቀመጥ በማኅበረሰቡ ውስጥ ‘ኸርድ ኢሚውኒቲ’ እንዲገነባ ማድረግ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።

ይሄ ማለት ኮሮናቫይረስ ማንን እንደሚያጠቃ እውቀት አለን ማለት ነው። ነገር ግን ቫይረሱ አሁን ላይ በሽታ የሌለባቸውን እንዲሁም ወጣቶችን እየገደለ ነው። ብዙ ሰው ያሳጣል። ምጣኔ ኃብታዊ ቀውስም ይፈጥራል። በዓለም ላይ ያለ ማንም መንግሥት እንደ መፍትሔ ቢያቀርበው ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ማለት አይቻልም። ብቸኛው አማራጭ ክትባት ነው።”

ተመራማሪዎች ክትባት ወይም መድኃኒት ለማግኘት ተቃርበዋል?

ተመራማሪዎች ከፍተኛ መረባረብ ላይ ናቸው። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ክትባት ወይም መድኃኒት ከተፈጠረ መልካም ነው ይላሉ ዶ/ር ኢዮብ።

ከዚህ ቀደም ክትባት ወይም መድኃኒት የማግኘት ሂደት ከአስር እስከ 15 ዓመታትም ይወስድ ነበር። እስካሁን በፍጥነት የተገኘው ክትባት የኢቦላ ሲሆን፤ አምስት አመት ወስዷል።

ኮሮናቫይረስ ግን ይህን ያህል ጊዜ ይወስዳል ተብሎ አይታመንም። “ኮሮናቫይረስ 1 ከኮሮናቫይረስ 2 ጋር ተመሳሰይ ስለሆነና ባለፉት 18 ዓመታት ብዙ የመድኃኒትና ክትባት ጥናቶች ስለተደረጉ ጊዜ አይወስድም የሚል እምነት አለ” ይላሉ።

ለኮሮናቫይረስን መድኃኒት ወይም ክትባት ለመፍጠር ለዓለም ጤና ድርጅት ወደ 600 ማመልከቻዎች ገብተዋል። በዘርፉ ጥሩ ሂደት ላይ ካሉ አገሮች ቻይና፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና እስራኤልን መጥቀስ ይቻላል።

ዶክተሩ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ክትባት ወይም መድኃኒት ሲገኝ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በምን ያህል ፍጥነት ይቀርባል የሚለው እንደሆነ ይናገራሉ።

“ከኤችአይቪ የተማርነው ነገር መድኃኒት ወይም ክትባት ሲፈጠር አምራቾቹ በኢትዮጵያና በተቀሩት የአፍሪካ አገራት ላይ ከባድ የድርድር ጫና እንደሚፈጥሩ ነው። በኤችአይቪ ጊዜ መድኃኒት እያለ ተከልክለን ነበር። ያኔ የደረሰብን በደል ሊደገም አይገባም” በማለት ይገልጻሉ።

ይህ በኮሮናቫይረስ እንዳይደገም፣ ኢትዮጵያና ሌሎችም የአህጉሪቱ አገራት ክትባቱ ሲገኝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካሁኑ መዘጋጀት እንዳለባቸውም ያስረግጣሉ።

ኢትዮጵያና የክትባቱ ተስፋ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ለበሽታው ክትባት ለማግኘት ምርምር ላይ ናቸው። የተለያዩ የሙከራ ደረጃዎች መታለፋቸውም ይገለጻል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት፤ በቫይረሱ ላይ በሚደረጉ ምርምሮችን አገራት እንዲባበሩ ‘Solidarity Trial’ የተባለ አሠራር አለው።

በዚህ ከ70 በላይ አገራት በተሳተፉበት መዋቅር ኢትዮጵያውያኑ ፕ/ር ጣሰው ወልደሀና (የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት)፣ ፕ/ር አበባው ፍቃዱ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ)፣ ፕ/ር አሸናፊ ታዘበው አማረ (ከጎንደር ዩኒቨርስቲ) መሳተፋቸው ለዶ/ር ኢዮብ ተስፋ ይሰጣቸዋል።

“ድምጻችን እንዲሰማ፣ ክትባት ሲገኝ ተጠቃሚ እንድንሆንም ያደርጋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ክትባት ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ያበረታታል።” ይላሉ።

ኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀትን ከዘመነኛው ሳይንስ ጋር በማጣመር ክትባቱን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ያክላሉ።

የተራቀቀ የጤና ተቋም በሌላት ኢትዮጵያ፤ ብዙሃኑ በቀላሉ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ይቸገራሉ። ይህም የበሽታውን ሥርጭት አስጊ ያደርገዋል። በበቂ ሁኔታ ውሃ አለመዳረሱ፣ አብዛኛው ማኅበረሰብ በተጠጋጋ ሁኔታ መኖሩም ችግሩን ያባብሰዋል።

የህክምና ባለሙያው አገሪቱ ቅድሚያ መስጠት ያለባት ወረርሽኙን ለመከላከል እንደሆነ ይናገራሉ።

“ዋና መመሪያ ፖሊሲዋ መሆን ያለበት በሽታውን መከላከል ነው። ያላትን አቅም በሙሉ ተጠቅማ በሽታው እንዳይስፋፋ እርምጃ መውሰድ አለባት። በሁለተኛ ደረጃ የመድኃኒትና ክትባት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያድጋትን ፖሊሲ መከተል አለባት። ክትባት ሲገኝ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ አለባት።”

አንዳንድ አገራት የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት እንቅስቃሴ የመገደብ እርምጃ ወስደዋል። የኢትዮጵያን ደካማ ምጣኔ ኃብት ከግምት በማስገባት ይህ ውሳኔ ከባድ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ዶክተሩ በበኩላቸው ምናልባትም በተመረጡ ቦታዎች ብቻ በከፊል እንቅስቃሴ ማቆም እንደ አማራጭ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ። የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ሊገታ እንደሚችል የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ መናገራቸውም ይታወሳል።