ዶናልድ ትራምፕ ፌስቡክን ሊዘጉት ይሆን?

ፕሬዝደንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው ያሻቸውን ነገር ሲጽፉ ነው የኖሩት፡፡ በማኅበራዊ ገጻቸው ስለሚጽፉት ነገር ሃይባይ አልነበራቸውም።

ትዊተር ግን ትናንት ያልተጠበቀ ነገር አደረገ። የፕሬዝዳንቱ ሰሌዳ ላይ ከተጻፈው ሐሳብ ሥር ‹‹የትራምፕ መልዕክት እውነታነት ሊጤን ይገባዋል›› የሚል ምልክት አደረገ። ይህ የሚሆነው አንድ ተጠቃሚ የሐሰት ወይም ያልተረጋገጠ ሐሳብ ሲጽፍ ወይም ሲዘባርቅ ነው።

ይህ የትዊተር ድርጊት ፕሬዝዳንቱን ሳያበግናቸው አልቀረም።

እንዲያውም ዛሬ ዶናልድ ትራምፕ እነዚህ ማኅበራዊ 'አሳሳች ሊሆን ይችላል' አለ

እርግጥ ፕሬዝዳንቱ ይህን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን አላቸው ወይ የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። የሕግ መወሰኛው ምክር ቤትና የሕግ መምሪያው ምክር ቤት በአንድ ሊደግፋቸው ይገባ ይሆናል። ስለዚህ ከእለታት አንድ ቀን ብድግ ብለው ፌስቡሚዲያ የተባሉትን ጠራርጌ እዘጋቸዋለሁ ሲሉ ዝተዋል።

ሆኖም እርሳቸው እነ ፌስቡክን ለመዝጋት የማያዳግም ፍጹማዊ ሥልጣኔን እጠቀማለሁ እያሉ ነው። ‹‹ኤክዝኪዩቲቭ ኦርደር›› ይሉታል በነርሱ አገር።

ይህንን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ማብራሪያ ለመጠየቅ ጋዜጠኞች ብዙ ሞክረዋል። ሆኖም ፕሬዝዳንቱም የነጩ ቤተ መንግሥት ቃል አቀባዮችም ታሪካዊዋ መንኮራኮር ስትመጥቅ ለማየት ኬኔዲ የሕዋ ማዕከል ፍሎሪዳ በማቅናታቸው በሚፈለገው ፍጥነት ምላሽ አልተገኘም። በኤይር ፎርስ ዋን ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ፍሎሪዳ ያቀኑ ጋዜጠኞችም ጥያቄውን ለማንሳት ሞክረው ምላሽ አላገኙም።

ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የማያዳግም ፍጹማዊ ፊርማዬን ፈርሜ›› አፈር ከድሜ አበላቸዋለሁ የሚሏቸውን እነ ፌስቡክን የሚከሱት የወግ አጥባቂ አመለካከቶችንና ሐሳቦችን ሳንሱር ያደርጋሉ በሚል ነው። በሌላ አነጋገር እነ ፌስቡክ የዲሞክራቶች ደጋፊ ናቸው ወይም ለነርሱ ያደላሉ ሲሉ ይከሷቸዋል።

በዶናልድ ትራምፕ የትዊተር ሰሌዳ ላይ በድፍረት መጥቶ ‹‹እውነት ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ›› የሚል ምልክት ያደረገው ትዊተር ቁጡውን ፕሬዝዳንት ይበልጥ እንዲቆጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

ለዚህም ይመስላል ፕሬዝዳንቱ ወደዚያው የትዊተር ገጻቸው ዳግም በመመለስ፤

‹‹ማኅበራዊ ሚዲያዎች አሁንስ የሚሰራቸውን አሳጥቷቸዋል፤ ይህ እብደት ነው። የ2020ውን የአሜሪካ ምርጫ ሳንሱር ሊያደርጉት ይሻሉ። በ2016 ሞክረውት አልተሳካላቸውም። አሁንም ያን ሊያደርጉ ይፈልጋሉ። ምን እንደማደርጋቸው እኔ ነኝ የማውቀው፤ ጠብቁኝ›› የሚል ይዘት ያለው ዛቻ ጽፈዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተከታይ አላቸው።

የትዊተሩ አለቃ ጃክ ዶርሲ ለፕሬዝዳንቱ ትችት በትዊተር ሰሌዳው ምላሽ ሰጥቷል።

‹‹ለዚህ ኩባንያ ድርጊት ተጠሪ የሆነ ሰው አለ፤ ያ ሰው እኔ ነኝ። ሰራተኞቼን ለቀቅ ያድርጉ። ሐሰተኛ አምታች መረጃዎችን መመንጠሩን እንቀጥልበታለን›› ብሏል። ይህ የሚስተር ዶርሲ ምላሽ ዶናልድ ትራምፕን ይበልጥ ሊያቆስላቸው እንደሚችል ይጠበቃል።

ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው የ ‹‹ይጣራ›› ምልክት የተደረገባቸውን ሐሳብ ፌስቡክም ላይ ለጥፈውት የነበረ ሲሆን ፌስቡክ ግን ምንም እርምጃ አልወሰደባቸውም።

ፌስቡክ በተለይ ወረርሽኙን በተመለከተ የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን አጠፋለሁ እያለ ሲዝት ከርሞ ነበር። ፕሬዝዳንቱን ለምን ሃይ ለማለት እንዳልደፈረ ለጊዜው አልታወቀም።

ፎክስኒውስ ላይ በዚህ ጉዳይ ቃለ መጠይቅ የተደረገለት የፌስቡኩ አለቃ ማርክ ዙከርበርግ ግን የፕሬዝዳንቱን ዛቻ አጣጥሎታል፡፡ ‹‹ በሳንሱር የሚከሰሰውን ማኅበራዊ ሚዲያ ሳንሱር ለማድረግ መነሳት በራሱ ይጣረሳል›› ሲል ተችቷል።

ይህን የዶናልድ ትራምፕና የትዊተር እሰጣገባን ተከትሎ የፌስቡክና የትዊተር የስቶክ ገበያ ትናንት ተቀዛቅዞ ነበር ተብሏል።

ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ የፌስቡክ፣ የትዊተርና የጉግል ኃላፊዎችን ሐሳብ ለማካተት ያደረገው ሙከራ በጊዜው ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።