ኮሮናቫይረስ ያቃወሰው የዓለም አቀፍ የትምህርት ዕድል

የምረቃ ገዋን የለበሰች ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ29 ዓመቱ ራውናቅ ሲንግ ከሁለት ዓመታት በፊት በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መነጋገር ጀምሮ ነበር።

በአውሮፓውያኑ ጥር 2020 ላይ ደግሞ ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚገኘው የባርክሌይስ ዩኒቨርስቲ ኮሊጅ ፤'ስ ስኩል ኦፍ ቢዝነስ’ ማመልከቻውን ተቀብሎ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲልክ ጠይቆት ነበር።

"ዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ ማመልከቻዬን እንዲቀበለኝ በማሰብ ለአምስት ዓመታት ስሰራበት የነበረውን መስሪያ ቤት ለቅቄ አዲስ የተመሰረተ ሌላ ንግድ ነክ ድርጅት ውስጥ ገባሁ።’’

ሲንግ ይህንን ያደረገው ለመማር ካሰበው ትምህርት ጋር የሚቀራረብ ሥራ ለመስራት ብሎ ነበር። ክፍያውም ቢሆን ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ጥረቱ ውጤት አስገኝቶለት የባርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ማመልከቻውን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎት በመጪው መስከረም ትምህርት ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነበር።

ነገር ግን ሳይታሰብ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እንዳልነበረች አደረጋት።

ሲንግ ብቻውን አይደለም፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተለያዩ የዓለማችን ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር ዝግጅታቸውን አጠናቀው በመጠባበቅ ላይ ከነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንዳውያን መካከል ነው።

ሁሉም ወደፊት ምን እንደሚሆን አያውቁም፤ ኮሮናቫይረስ መድኃኒት አልያም ክትባት ተገኝቶለት ነገሮች ወደቀድሞው ሁኔታቸው ይመለሱ አይመለሱ በእርግጠኝነት ማወቅ አይችሉም።

ከቻይና በመቀጠል ሕንድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ትታወቃለች። እንደ አገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2019 ብቻ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕንዳውያን በተለያዩ የውጭ አገራት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር።

በየዓመቱ ሰኔ እና ግንቦት በሕንድ የሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቪዛ ለማግኘት በአገራት ቆንስላ እና ኤምባሲዎች በር ላይ ተሰብስበው ይታዩ ነበር። የዘንድሮው ሁኔታ ግን ከሌላ ጊዜው ለየት ያለ ይመስላል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ጋዜጠኝነት ለመማር ፍላጎት ያላት የ23 ዓመቷ ባሩዋ ሌላኛዋ ለትምህርት ወደ ውጭ ለመሄድ ተዘጋጅተው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ናት።

"በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት ይታያል፤ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚሆን አናውቅም፤ የትምህርት ቪዛ ይሰጠን አይሰጠን የምናውቀው ነገርም የለም" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ,

ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በትምህርት አሰጣጡ ላይ ለውጥ አድርጓል

በርቀት መማር

አንዳንድ በዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች የመጀመሪያውን ሴሚስተር ወደሚቀጥለው ዓመት እንዲያስተላለፉ አማራጭ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ግሪንዊች የተባለው ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፈለጉ የፊት ለፊት ለፊት ትምህርት ከኦንላየን ትምህርት እያሰባጠሩ መማር የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ከሌሎች አገራት የሚመጡት ተማሪዎች ደግሞ የዘንድሮውን የመጀመሪያ ሴሚስተር ወደሚቀጥለው ዓመት ማስተላለፍ እንደሚችሉ አስታውቋል።

ታዋቂው ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ትምህርት በኦንላየን ይቀጥላል ብሏል።

ሲንግ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በጉጉት ሲጠብቀውና ሲዘጋጅለት የነበረው የውጭ አገር ትምህርት በኮሮናቫይረስ ምክንያት መሰናከሉ እንዳበሳጨው ይናገራል።

ባሩዋ በበኩሏ "እኛ ዋነኛው በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የምናመለክትበት ምክንያት በካምፓሶች ተገኝተን መማር ስለምንፈልግ ነው። በእነዚህ አገራት ዕድል ካገኘን መስራትም እንፈልጋለን። ስለዚህ ባህሉንና አኗኗሩን በቦታው ሄደን ማየት አለብን። በኦንላየን የሚባለው ትምህርት ከምንም ቢሻልም ምርጫዬ ግን አይደለም" ትላለች።

ወደ ውጭ አገራት ሄዶ መማር ቀላል የማይባል ወጪ አለው። ተማሪዎች ለተለያዩ ሥራ ማስኬጃዎች በዶላርና በፓውንድ ነው የሚከፍሉት። የቪዛ እና የአውሮፕላን ጉዞ ወጪም አለ።

ስለዚህ ተማሪዎች በኦንላየን የሚማሩ ከሆነ የቪዛ እና የአውሮፕላን ቲኬት ወጪ ይቀርላቸዋል ማለት ነው። ነገር ግን አብዛኞቹ ከነወጪው በውጭ አገራት ሄዶ መማሩን ነው የሚመርጡት።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላ ጉዳይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመረቁ በውጭ አገራት ሥራ እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸው ነው።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የበርካታ አገራት ኢኮኖሚ መድቀቁን ተከትሎ ደግሞ ከዚህ በፊት ሠራተኞችን በብዛት ይቀጥሩ የነበሩ ትልልቅ ድርጅቶች እንደውም ሠራተኞቻቸውን እየቀነሱ ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታት ነገሮች ቢስተካከሉ እንኳን እነዚህ ድርጅቶች በቶሎ ሠራተኞችን ይቀጥራሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

ያላቸውን ጥሪት አሟጠው በአሜሪካና በዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪያቸውን የሚይዙ ተማሪዎች ወደአገራቸው ተመልሰው መስራት አዋጪ አይሆንላቸውም። በዚህም ምክንያት በተማሩበት አገር ሥራ ማፈላለግን ይመርጣሉ።

አሜሪካ ውስጥ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለኢኮኖሚው እስከ 45 ቢሊየን ዶላር ድረስ በየዓመቱ ያበረክታሉ። በእንግሊዝ ደግሞ ከእነዚሁ ተማሪዎች ብቻ ዩኒቨርሲቲዎች እስከ 7 ቢሊየን ፓውንድ ያገኛሉ።

ስለዚህ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገቡት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከተማሪዎቹ ይህን ያህል ገንዘብ የሚሰበስቡት አገራትና የትምህርት ተቋማቱም ጭምር ናቸው።

ሲንግ ምንም እንኳን የወደፊቱን መተንበይ ባይችልም በሚቀጥለው ዓመት ወደ አሜሪካ ሄዶ ትምህርቱን መከታተል እንደሚጀምር ተስፋ ያደርጋል።