የኮሮናቫይረስ፡ ለአሜሪካ ብቁው ፕሬዝዳንት ማን ነው? አንዱሩ ኮሞ ወይስ ዶናልድ ትራምፕ?

የነጻነት ሐውልት ጭምብል ተደርጎላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቢቢሲው የሰሜን አሜሪካ አርታኢ ጆን ሶፔል በአሜሪካ የሟቾች ቁጥር 100 ሺህ ማለፉት ተንተርሶ ትራምፕና ኮሮናን፣ ኮሮናን የኒውዮርክ ገዢን አንዱሮ ኮሞን እንዲሁም የዚያችን አገር እጣ ፈንታ የታዘበበት ጽሑፍ እንዲህ ያስነብበናል።

ታላቋ አሜሪካ ባለፉት 44 ዓመታት የዓለም ፖሊስ ነበረች። ጦርነት ያልገጠመችበት አህጉር፣ ያልቧጠጠችው ተራራ፣ ቦምብ ያላዘነበችበት ዋሻ የለም። ቶራቦራ ድረስ ሰምጣ ገብታለች።

አገር አፍርሳ አገር ሠርታለች።

ለምሳሌ ኢራቅን። ለምሳሌ አፍጋኒስታንን።

በአፍጋኒስታን ጦርነት ከ30 ሺህ በላይ የአገሬው ዜጎች ሞተዋል፤ የሞቱት የአሜሪካ ወታደሮች ግን 2 ሺህ ናቸው።

በኢራቅ ለ10 ዓመታት ጦር አስቀምጣ ነበር። በዚያ ጦርነት የሞቱ ኢራቃዊያን 50 ሺህ ይጠጋሉ። በዚህ ሁሉ ዘመን አሜሪካ የሞተባት የወታደር ቁጥር 4 ሺህ 500 ብቻ ነው።

ለ16 ዓመት በቆየው የቬትናም ጦርነት አሜሪካ 58 ሺህ ወታደር ነው የገበረችው።

ለሦስት ዓመት በቆየው የኮሪያ ጦርነትና ኢትዮጵያም የሰላም አስከባሪ ወታደር በላከችበት ውጊያ ላይ አሜሪካ 36 ሺህ ወታደሮችን አጥታለች።

ይህ ባለፉት 44 ዓመታት በጦርነት የጠፋውን ሕይወት ያህል በአራት ወራት ይጠፋል ማን አለ? ያውም በደቂቅ ረቂቅ ተህዋስ? ለዚህም ምክንያቱ የፕሬዝዳንቷ እንዝህላልነት ነው የሚሉ አሉ።

ትራምፕና ኮሮናቫይረስ

ትራምፕ ኮቪድ-19ን መጥፎ የቻይና ስጦታ ሲሉ ነው የሚጠሩት። ስማቸው ከዚህ ተህዋስ ጋር ባይነሳ ይመርጣሉ። ለዚህም ነው ለተህዋሱ መፈጠር ጥፋተኛዋ ቻይና ወይም የዓለም ጤና ድርጅት እንጂ እኔና አሜሪካ የለንበትም የሚሉት።

ኮቪድ-19 ከመሪዎች ሁሉ እንደ ትራምፕ አፈር ከድሜ ያስጋጠው ፕሬዝዳንት አለ ለማለት ያስቸግራል።

ለምሳሌ ከዚህ ወረርሽኝ በፊት በአሜሪካ የሥራ አጥ ቁጥር መሬት ነክቶ ነበር፤ በኮቪድ-19 ዘመን ግን ሰማይ ነካ።

ምጣኔ ሀብቱ ተመንድጎ ነበር፤ በኮቪድ ዘመን ሽባ ሆነ።

አሁን ከ30 ሚሊዮን አሜሪካዊያን በላይ ከመንግሥታቸው ድጎማ ጠባቂዎች ናቸው።

ይህን የትራምፕን በዋይት ሐውስ ዘመን አንድ ስኬት (ሥራ ፈጣሪነትን) ወረርሽኙ ጠራርጎ ወስዶታል።

ከዚህ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ሕዝባቸውን ታላቅ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ለማሳመን ነገሩ አልጋ በአልጋ አይሆንላቸውም። ምን ሊሉ ነው? ታላቅ አድርጊያችሁ ነበር ቫይረሱ ወሰደብኝ?

ትራምፕ በዚህ ተህዋስ አሜሪካዊ አይሞትም፣ ቢሞትም ከ20 ወይ ከ30 ሺህ አይበልጥም ብለው ነበር። ቀጥለው ቁጥሩን ወደ 50 ሺህ አሳደጉት። ቀጥለው ወደ 60 እና 70 ሺህ። አሁን ግን መቶ ሺህን አልፏል።

የተያዙት ዜጎች ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን እየተጠጉ ነው።

ይህ ደግሞ ትምፕን እየገዘገዘ የሚጥል እውነታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሚገርመው በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ትራምፕ ቀን ተሌት የሚያወሩት እርሳቸው ቶሎ እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ 2 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ሊሞቱ ይችሉ እንደነበረ ነው።

ከሞቱባቸው ዜጎቻቸው ይልቅ በእርሳቸው አመራር ያዳኗቸውን ሰዎች እንዲመለከት ሕዝባቸውን ይወተውቱታል። ሌት ተቀን።

ትራምፕ አንድ በበጎ የሚነሳላቸው ነገር በጥር ወር መጨረሻ አሜሪካዊ ያልሆኑ ከቻይና ወደ አሜሪካ ምድር እንዳይገቡ ማድረጋቸው ነው። ያ እርምጃ ብዙ አማካሪዎቻቸውን ቸል ብለው ያደረጉት በመሆኑ ይሞገሱበታል።

በእርግጥ ትራምፕ ያን ጊዜ የውጭ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን የገዛ ዜጎቻቸውን ጭምር ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ነበረባቸው ብለው የሚተቿቸው አሉ።

እርሳቸው ግን "እንዴት ዜጎችን ወደ አገራችሁ መግባት አትችሉም" እላለሁ ሲሉ ይከራከራሉ።

ትራምፕ ይህን እርምጃ መውሰዳቸው ቢያስመሰግናቸውም በየካቲት ወር ላይ ፈዘው መቀመጣቸው ከሁሉ በላይ ያስተቻቸዋል።

የካቲት ወር በአሜሪካ የመመርመሪያ መሣሪያዎች ቢሰሩበት፣ ቬንትሌተር ቢመረትበት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ቢካሄድበት ኖሮ አሁን ያለቀው ሕዝብ ግማሹ እንኳ አያልቅም ነበር ይላሉ የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች።

አንዲት ጋዜጠኛ ትራምፕ ስለሞቱት ሳይሆን ስለዳኑት እያወሩ ሲያስቸግሯት "በየካቲት ወር የት ነበሩ? ምን ሲሰሩ ነበር?" ብላ አፋጠጠቻቸው። እርሳቸው ወደ ጥር ወር መለሷት "በጥር መጨረሻ ድንበር ባልዘጋ ኖሮ…" በማለት።

"እኔ እየጠየክዎ ያለሁት ስለ የካቲት ነው…" አለቻቸው።

ሰውየው ተመልሰው "ጥር ላይ ማንም ሳይደግፈኝ፣ ዶ/ር ፋውቺ እንኳ እየተቃወመኝ ድንበር እንዲዘጋ የወሰንኩ ድንቅ ሰው ነኝ" ይላሉ።

"የተከበሩ ፕሬዝዳንት በድጋሚ እጠይቅዎታለሁ፤ በየካቲት ወር ምን ሰሩ?"

"ምን ያልሰራሁት አለ? እንቅልፋሙ ጆ ባይደን ምን ሲሰራ ነበር?…"

"እኔ ስለ ጆ ባይደን አልጠየክዎትም ክቡር ፕሬዝዳንት…"

"አንቺ ፌክ ነሽ፤ ከፌክ ኒውስ ነሽ! ጨርሰናል!"

ዶናልድ ትራምፕ ምን ብለው ነበር?

እርግጥ ነው ጋዜጠኛዋ ያነሳችው ጥያቄ መሠረታዊ ነበር። በዚያ ወር ብዙ ሊሠራ ሲችል አልተሰራም።

መመርመሪያ መሣሪያ አልተዘጋጀም፤ ቬንትሌተር ማምረት አልተጀመረም፣ መሠረታዊ የሕክምና መሣሪያዎች አልተዘጋጁም፣ የዓለም ጤና ደኅንነት ክፍልን ትራምፕ አፍርሰውት ነበር፣ ለአንዲህ ዓይነት ጊዜ ይጠቅም የነበረ ፈንድ ወደ ሌላ ተዘዋውሯል። እነዚህ ናቸው የሚያስተቿቸው።

በአነዚህ ወራት ዶናልድ ትራምፕ ምን ሲናገሩ እንደነበር እናስታውስ…

ጥር 22፡ "ከቻይና ቫይረስ ተሸክሞ የገባው አንድ ሰው ነው። ተቆጣጥረነዋል። ሁሉም ነገር ሰላም ነው።"

የካቲት 2፡ "ሁሉም ነገር ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል። ቫይረሱ በየት አድርጎ ይገባል?"

የካቲት 10፡ "ያው እንደምታውቁት በሚያዚያ ሙቀት ስለሚሆን ቫይረሱ ብን ብሎ ነው የሚጠፋው፤ ልክ እንደ ተአምር። ይህ እውነት ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ። ከቻይናው አቻዬ ሺ ዢን ፒንግ ጋር በስልክ አውርቻለሁ፤ ጥሩ እየሰራ ነው። ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ እየሄደ ነው።"

የካቲት 11፡ "በአገራችን 12 ሰዎች ብቻ ናቸው በቫይረሱ የተያዙት፤ እነሱም እያገገሙ ናቸው፤ የሚያሳስብ ነገር የለም። ኧረ እንዲያውም 12ትም አይሞሉም!"

የካቲት 24፡ "ኮሮናቫይረስን በአሜሪካ በቁጥጥር ሥር አውለነዋል። ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ሲዲሲ እና የዓለም ጤና ድርጅት እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ ነው። የአክስዮን ገበያው ሞቅ ደመቅ ብሏል።"

የካቲት 26፡ "አሜሪካንን በሚያህል ትልቅ አገር 15 ታማሚዎች ብቻ ሲኖሩና እነሱም በቀጣይ ቀናት ሲያገግሙ ቁጥሩ ወደ ዜሮ ይወርዳል። እኛ እንዲህ እጹብ ድንቅ ሥራ የምንሠራ ሰዎች ነን።"

መጋቢት ወር መጣ። ሁሉም ነገር ወደ ሐዘን ተቀየረ።ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ፤ ከማን እንደተያዙ ግን አያውቁም። ዜጎች ለሆስፒታሎች ድረሱልን አሉ። ሆስፒታሎች ለመንግሥት ድረስልን አሉ። የጭምብል ያለህ፣ የቬንትሌተር ያለህ፣ የጓንት ያለህ…!

ሞት ከነአጀቡ በዋሺንግተን አድርጎ ኒውዮርክ ገባ። በኤልሜርሀስት ሆስፒታል ሬሳ ከመብዛቱ የተነሳ የሬሳ ፍሪጅ ያላቸው የጭነት መኪናዎች ደጅ ላይ በተጠንቀቅ መቆም ጀመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኒው ዮርክ ውስጥ ሬሳ ማስቀመጫ ቦታ ጠፍቶ ፍሪጅ ያላቸው የጭነት መኪኖች ጥቅም ላይ ውለዋል

አሜሪካዊያን መቀበርያ አጥተው የጅምላ መቃብር ተቆፈረላቸው።

ነርሶች ተገቢ የሕክምና እቃ የሚያቀርብላቸው አጥተው ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ፌስታል ላስቲክ ለብሰው ነበር። በታላቋ አሜሪካ ይህ ይሆናል ያለ አልነበረም።

በሕዝብ አሰፋፈሯ ጥቅጥቅ እጭቅ ያለች ናት።

ትራምፕ ያደጉባት ኒውዮርክ፤ የዓለም ደማቋ ከተማ ኒውዮርክ፣ የዓለም ሀብታሟ ከተማ ኒውዮርክ ድንገት የሞት አውድማ ሆነች።

መጀመሪያ ሟቾች ስም ነበራቸው፤ ከዚያ ቁጥር ሆኑ። መጀመርያ የሟቾች ቁጥር ያስደነግጥ ነበር፤ ቀጥሎ ቁጥር ቁጥርን እንጂ ሰውን መወከል አቆመ። ስሜት መስጠት ተወ።

ሺህዎች ረገፉ። በዚህ እጅግ አስከፊ ወቅት አንድ ጀግና ብቅ አሉ። የኒው ዮርክ ገዢ አንድሩ ኩሞ።

ትራምፕ በኒው ዮርክ ኪዊንስ ውስጥ አድገው በማንሃታን ነግደው የናጠጠ ሀብታም ሆነው ይሆናል። እውነተኛ የኒው ዮርክ ልጅ መሆናቸውን ያስመሰከሩት ግን አንድሩ ኩሞ ናቸው።

ኩሞ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ሟቾችን አፈር ምሰው ቀብረው በሬሳቸው ላይ የእርሳቸውን ስኬት፣ የእርሳቸውን ዝና አይዘምሩም።

ማዘን ሲኖርባቸው ያዝናሉ፤ ማልቀስ ካለባቸው ያለቅሳሉ፤ ሲቆጡም ተቆጡ ነው። በአጭሩ ሰው ናቸው ይሏቸዋል። ከሕዝብ ጋር ናቸው። ኒው ዮርካዊያን በወረርሽኝ እየወደቁ በመሀሉ በእርሳቸው ፍቅር ትንሽ ትንሽ ወደቁ።

የኒው ዮርክ ገዢ አንድሩ ኩሞ ልክ እንደ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ዲጂታል ሰሌዳቸው ላይ ሰንጠረዥ እየዘረጉ አስተዳደራቸው ምን እየሰራ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፤ ምን እንዳልሰራ፣ የትኛው መድኃኒት፣ የትኛው የሕክምና መሣሪያ እንደጎደለው፤ ነዋሪዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው/እንደሌለባቸው ይተነትናሉ።

የእርሳቸውን የቲቪ መግለጫ ሰዎች እንደ ተከታታይ ድራማ ይመለከቱታል። ይህ ትራምፕን አስኮረፈ። ትራምፕም የእራሳቸውን "ሾው" ጀመሩ። ልዩነቱ እርሳቸው ስለእራሳቸው ብቻ ያወራሉ። ኩሞ ግን ስለ ኒው ዮርካዊያን ያወራል።

ዶናልድ የሚናገሩት ሁሉ ይተናነቃል። አንድሩ ኩሞ የሚናገሩት ግን ጠብ አይልም።

ሁለቱም በኒው ዮርክ የኩዊንስ ሰፈር ልጆች ናቸው። ሆኖም በባህሪም በሥራም አልተገናኝቶም ናቸው። ኩሞ ስለራሳቸው ቁጥብ ናቸው፤ ጊዜያቸውን በአልባሌ ዝባዝንኬ አያጠፉም። ሁልጊዜም እጥር ምጥን ያለና ወደ መሠረታዊ ጉዳይ ያተኮረ መግለጫን ይመርጣሉ።

ኩሞ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር አንድ ሁለት ተባብለው ያውቃሉ። ያ ጸብ ግን ኩሞ ትራምፕን ማመሰገን ባለባቸው ጊዜ እንዳያመሰግኗቸው አላደረገም።

ትራምፕ በኩሞ መደነቅን እጅግ ይወዳሉ። "ኩሞም አድንቆናል" ብለው በቪዲዮ አቀናብረው፣ ጋዜጠኛ ጠርተው እዩልኝ ብለው ያውቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

አንድሩ ኩሞ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደረግላቸው

የኒው ዮርኩ ገዢ የሰው ልብ ላይ የገቡበት ጥልቀት አስደናቂ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት ዲሞክራት ሆነው የኖሩት አንድሩ ኩሞ በሪፐብሊካኖች ከዶናልድ ትራምፕ ይልቅ መወደዳቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ዲሞክራቶችማ ውስጥ ውስጡን ምነው በቀጣይ ምርጫ ጆ ባይደን ቀርቶብን አንድሩ ኩሞ በወከለን ይላሉ።

የሚደንቀው የአንድሮ ኩሞ የ45 ደቂቃ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ጎበዝ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጥፍጥ ያለች ናት።

በተመሳሳይ ዕለታዊ መግለጫ የሚሰጡት ዶናልድ ትራምፕ 'ሲነሽጣቸው' እስከ 2 ሰዓትና ከዚያ በላይ ካሜራ ደቅነው ሊያወሩ ይችላሉ። ሁሉም ጋዜጣዊ መግለጫቸው ሲጨመቅ ግን ከሚከተለው ጭብጥ አያልፍም።

• እኔ ብዙ ሚሊዮን አሜሪካዊያንን ከሞት ባልታደግ ኖሮ ይቺ አገር አብቅቶላት ነበር

• እኔ አሜሪካንን በኢኮኖሚ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ከፍታ ላይ አስቀምጫታለሁ

• እንቅልፋሙ ጆ ባይደን እኔን ማሸነፍ አይችልም

• እኔ አሜሪካንን በቬንትሌተር እራሷን እንድትችል አድርጊያታለሁ

• ናንሲ ፒሎሲ አስቀያሚ ሴት ናት

• ብዙ ርዕሳነ መንግሥታት እየደወሉ ያደንቁኛል

• ሲኤንኤን ሐሰተኛ ሚዲያ ነው

• ዲሞክራቶች በእኔ ላይ እያሴሩ ነው

• አገረ አሜሪካንን ዘግተን ልንቀመጥ አንችልም፤ በራችሁን ክፈቱ

ዶናልድ ትራምፕ ይህ ተህዋስ ድብርት ውስጥ እንደከተታቸው ግልጽ ነው። ቢያንስ ሁለት እጅግ የሚወዱትን ነገር አሳጥቷቸዋል።

አንዱ የጎልፍ ጨዋታ ነው። ሌላው ደግሞ የደጋፊዎቻቸው የፖለቲካ ስብሰባ ጩኸት። ትራምፕ በደጋፊዎቻቸው ተከበው ዲሞክራቶች ላይ መሳለቅ ነፍሳቸው ነው። ደማቸው የሚሞቀው ስማቸው እየተጠራ በደጋፊዎቻቸው ሲዘመርላቸው ነው ይሏቸዋል።

ይህ ክፉ ደዌ ከመጣ ወዲህ ግን በየቁኑ ከፊታቸው የሚደቀኑት ደጋፊዎቻቸው ሳይሆኑ እንደ ደመኛ የሚያይዋቸው ጋዜጠኞችና ካሜራዎቻቸው ናቸው።

ስለዚህ በየጊዜው ድብርት ተጭኗቸው ነው መግለጫ የሚሰጡት።

የአሜሪካ ታማሚ ሕዝብ የኦክሲጂን ቬንትሌተር ይሻል፤ ትራምፕ ለመተንፈስ የደጋፊ ጭብጨባና ጩኸት ይሻሉ። ይህ ክፉ ተህዋስ ይህንን አሳጥቷቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ከፕሬዝዳንት ትራም ጋር

የትራምፕ ምክትል "ብልጡ" ማይክ ፔንስ

ሌላው በዚህ ወረርሽኝ ቁልፉ ተዋናይ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ናቸው።

እሳቸው የማይመሩት ግብረ ኃይል የለም። በትራምፕ የሚዋቀር ነገር በሙሉ በበላይነት ፔንስ ይመሩታል።

በትራምፕና በተቋማት መሀል ያሉት ድልድይ ፔንስ ናቸው፤ በትራምፕና በ50ዎቹ ግዛት ገዢዎች መሀል ያሉት ድልድይ እሳቸው ናቸው። ቆፍጣና ሰው ናቸው። ምንም ነገር ቢረሱ ሁለት ነገር አይረሱም።

አንዱ ትራምፕን ማድነቅ ነው። ለሁሉም ስኬቶች የአለቃቸውን የትራምፕን ስም ይጠራሉ።

ውድቀት ካለም የእሳቸው ጥፋት እንጂ የአለቃቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ማይክ ፔንስ ሌላ የማይረሱት ነገር ለቅሶ መድረስን ነው። ንግግሩን በትራምፕ ስም ከቀደሱ በኋላ ሕይወታቸው ላጡ አሜሪካዊያን ሐዘናቸውን መግለጽ በፍጹም አይረሱም።

በዚህ ረገድ አለቃቸው ትራምፕ ደካማ ናቸው። ለፖለቲካ ሲሉ እንኳ ማዘን አይችሉም።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ከፕሬዝዳንት ትራም ጋር

ክቡር ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ

ሌላው የኮቪድ-19 አለቃ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ናቸው። የጤና ግብረ ኃሉን በሞያ የሚመሩ ናቸው። የእርሳቸው ሚና ለትራምፕ ሳይንሳዊ ድጋፍ መስጠት ነው። ሆኖም አልተሳካላቸውም። እርሳቸው የገነቡትን ትራምፕ ያፈርሱታል።

የአሜሪካ ሕዝብ ከዶናልድ ትራምፕ ይልቅ ዶ/ር ፋውቺ የሚሉትን ቢሰማ ይመርጣል። ሆኖም ትራምፕ የሚቃረናቸውን ሰው ቀይ ካርድ ነው የሚሰጡት። ለዶ/ር ፋውቺም ተደጋጋሚ ቢጫ ካርድ አሳይተዋቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እንደ ቸርችል የጦር ጊዜ ጀግና መሪ ለመሆን ይሞክራሉ። የቢቢሲ ዘጋቢ ጆን ሶፔል እንደሚለው ግነ "በአብዛኛዎቹ ጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸው ላይ ተገኝቻለው። ትራምፕ በጭራሽ የጦርነት ጊዜ መሪ ተክለስብዕና የላቸውም" ይላል።

ከመግለጫዎቹ ሁሉ የከፋው ለ2 ሰዓት የቆየው ነው። 45 ደቂቃ የምርጫ ቅስቀሳ አደረጉ። ለሌለ ብዙ ደቂቃ እንዴት ታላቅ መሪ እንደሆኑ ደሰኮሩ፤ ለሌላ ደቂቃዎች የአሜሪካ ሚዲያ እርሳቸው ላይ እንደሚጨክን ተናገሩ፤ ለሌላ ደቂቃ በታሪክ ስኬታማው መሪ እርሳቸው እንደሆኑ ለማሳመን ሞከሩ።

በዚህ ዘለግ ባለ መግለጫ ለአንድ ደቂቃ እንኳ ስለሚሞተው ሕዝባቸው ግድ ሰጥቷቸው አንዲት የሐዘን ቃል አልወጣቸውም።

ያም ሆኖ ትራምፕ ከአገር መሪነት ይልቅ የመድረክ ሰው ተደርገው ስለሚታሰቡ ይሆናል ሕዝብ አይጨክንባቸውም፤ ሚዲያውም ለፌዝ ካልሆነ አያመርባቸው ይሆናል።

እርሳቸው ግን ይናገራሉ። እንደ አሜሪካ አንድም አገር የጅምላ ምርመራ አላደረገም ይላሉ። "It's not even close" (ጭራሽ ከእኛ ጫፍ የሚደርስም የለም) በጣም የሚወዷት ሀረግ ናት።

እርሳቸው ግን ይናገራሉ፤ አንድም አገር እንደኛ ቬንትሌተር ያለው የለም ይላሉ። ሁሉም አገር ያለው ቬንትሌተር ቢደመር የእኛን አያህልም ይላሉ፤ "not even close" የሚወዷት ሀረግ ናት።

እርሳቸው ግን ይናገራሉ፤ " የሌሎች አገር መሪዎች በእኛ ይቀናሉ፤ ቬንትሌተር አውሰን ይሉኛል፤ አንዳቸውም የእኛን ያህል አላመረቱም።" "not even close."

ጀርመኖች ናቸው በአሜሪካ የሚቀኑት? ደቡብ ኮሪያ ትሆን? ነው ታይዋንና ኒውዚላንድ?

ትራምፕ እውነታቸውን ይሆናል፤ አሜሪካ አንደኛ ናት! በሟቾች ቁጥርም የሚያህላት የለም። "Not even close."