የደረሱበት ያልታወቀው ተማሪዎች ስድስት ወር ሆናቸው

አቶ ሐብቴ እማኘው
የምስሉ መግለጫ,

አቶ ሐብቴ እማኘው

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተነስተው ወደ መኖሪያ ቀያቸው በማምራት ላይ የነበሩ ተማሪዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መታገታቸው ከተነገረና ያሉበት ሳይታወቅ እነሆ ዛሬ ግንቦት 24 ስድስተኛ ወር ሆነ።

የተማሪዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው ችግር እንደተጠማቸው የሰሙት ኅዳር 24/2012 ዓ.ም ነበረ። ወላጆች ክስተቱን ከእራሳቸው ከልጆቻቸው ተደውሎላቸው እንደሰሙ የተናገሩ ሲሆን ጉዳዩ ትኩረት ለማግኘት ሳምንታትን ወስዶ ነበር።

ጉዳዩ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ እስካሁን ቀጥሏል። ቢቢሲ የደረሱበት ሳይታወቅ ስድሰት ወራት ስላስቆጠሩት ተማሪዎች ጉዳይ የተሰማ ነገር እንዳለ ለማጣራት የተወሰኑ የተማሪዎቹ ቤተሰቦችን አናግሯል።

ወይዘሮ እመቤት መለሰ የተማሪ አሳቤ አያል እናት

ተማሪ አሳቤ አያል የት እንዳሉ ካልታወቁት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። ስለነበረው ጉዳይ እንዲያጫውቱን ለመጠየቅ እናቷን ወይዘሮ እመቤት መለሰን ለማግኘት በልጃቸው ስልክ ነበር ያገኘናቸው።

ልጃቸው ሊተባበረን ፈቃደኛ ቢሆንም እናቱ በሐዘን መጎዳታቸውን ነግሮን "[ተማሪ አያል] በህይወት እንዳለች ነግራችሁ አናግሯት" ካልሆነ ከማልቀስ ውጪ ምንም እንደማያናግሩን ነግሮን ይህንንም እሱ ከነገራቸው በኋላ ነበር ተረጋግተው ማናገር የጀመሩት።

"ለመጨረሻ ጊዜ ታህሳስ አንድ ቀን አወራን" ሲሉ የነበረውን ነገር ያጫውቱን የጀመሩት ወይዘሮ እመቤት "ለመጨረሻ ጊዜ ታህሳስ አንድ ቀን አወራን። 'እኛ ታግተናል ይዘወናል። እንግዲህ አንገናኝም ደህና ሁኚ' ነበር ያለችኝ" ሲሉ የነበረው ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ሐዘን ክፉኛ በተጫነው ድምጽ ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች አጭር አጭር መልስ የሰጡን ወይዘሮ እመቤት ከፌደራል መንግሥት ጀምሮ እስከ ክልል መስተዳደር ድረስ የተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ጉዳዩን ለማሳወቅ መጣራቸውን ይናገራሉ።

ከዚያም በኋላ ልጃቸውና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ለዚሁ ጉዳይየ ተለያዩ ቦታዎች መሄዳቸውን ጠቅሰው "እኔ አልሄድኩም እዚሁ ነው [ቤታቸው] የማለቅሰው" ብለውናል።

ልጃቸው የደረሰችበትን ሳያውቁ ስላለፉት ስድስት ወራትም "ምን ኑሮ አለ። እሷን ነው የምናስብ እንጂ ምን ሃሳብ አለ። እኛ አንሰራ ምን አንል እንጉርጉሮ እና ለቅሶ ነው። በእሷ ሃሳብ ገብተን ምኑን አድርጌ ልስራው" ሲሉ ያሳለፉትን የሰቆቃ ጊዜያት ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ሐዘኑ ቢጎዳቸውም ደህና ነኝ የሚሉት የተማሪ አሳቤ እናት "ባለው ሁኔታ ደህና ነኝ እስከዛሬ። እኔ ነኝ ያሳደኳትም እኔ ነኝ ይዣት ያለሁ። ያው የሚያስፈራኝና የሚያሳስበኝ ወጥታ ከቀረች ነው" ሲሉ ይሰጋሉ።

"አንደኛ ተማሪ ናት። እኔን ትደግፈኛለች ትመራኛለች ብዬ ነው የምቀመጠው። እንዲህ ሆና ቀረችብኝ። [እምባ በተናነቀው ድምጽ] 'አንደኛ ነኝ። እኔ ትምህርቴን ነው እንጂ የምቀጥል ለባል አልዳርም ነው ነበር የምትለኝ'" ሲሉ ልጃቸው ስለነበራት ሃሳብ እያነሱ ይናገራሉ ወይዘሮ እመቤት።

ምንም እንኳን ወራት ቢቆጠሩም አሁንም የልጃቸው መምጣት እየተጠባበቁ ነው። "መንግሥት ልጄን እንዲያመጣልኝ ነው የምፈልገው። ልጄን በሠላም ማግኘት እንጂ ሌላ ምንም ሃሳብ የለኝም" ሲሉ ጉጉታቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ሐብቴ እማኘው የተማሪ ግርማ ሐብቴ አባት

ከወራት በፊት ቢቢሲ የተማሪ ግርማ ሐብቴ አባት ከሆነት ከአቶ ሐብቴ እማኘው ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። ከዚያ ወዲህ ስላሉበት ሁኔታ ጠይቀናቸው "ምን አዕምሮ አለኝ። በአዕምሮዬ አይደለም የማነጋግራችሁ። የመንግሥትን ውጤት ነው የምጠብቀው። መንግስት ምን ያደርግልን ይሆን? እያልኩኝ ነው" ሲሉ አሁንም በጥበቃ ላይ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

አቶ ሐብቴ ልጃቸው መታገቱን ያወቁት ኅዳር 24 ነው። ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 5/2012 ድረስ ልጃቸው ስልክ እየደወለ ከቤተሰቡ ጋር ተነጋግሯል።

"የሥራ ወቅት በመሆኑ አጨዳ ላይ ስለነበርኩ ከእናቱ ጋር ነው የተነጋገረው" የሚሉት አቶ ሐብቴ "'ተይዘናል። ከሰው ጋር ነን። ችግር የለም። አያንገላቱንም። የምንለቀቅበትን ቀን ጸሎት አድረጉልኝ' ነው ያለው። ምን አደርጋለሁ እስካሁን ድረስ እያለቀስኩ ነው" ሲሉ ለመጨረሻ ጊዜ ያወሩትን ያስታውሳሉ።

"ከሰሞኑ ምንም የሰማነው ነገር የለም" የሚሉት አቶ ሐብቴ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችን ማናገራቸውን አስታውሰዋል።

"እነአቶ ንጉሡ ጥላሁን አናግረውናል። ሥራ እየሠራን ነው ብለውናል። ከእናነተ ጋር ነን እያሉን ነው። መንግሥትን ነው የምንጠበቀው። የመንግሥትን ምላሽ ነው የምንጠብቀው። ሌላ ምን የምናደርገው ነገር አለን። ከቤታችን ቁጭ ብለን እያለቀስን እያነባን ነው። ሥራ አንሰራም ልጆቻቸን ተበትነው ነው ያሉት።"

"ባለቤቴ ምንም ዋጋ የላትም በህክምና ላይ ነው ያለችው። ህክምና ላይ ነው ያለችው። በጸበል ላይ ነው ያለሁት። ምንም አዕምሮ የላትም። ከወለል ላይ ወደቀች። እግዚኦ እያለች እየተንፏቀቀች እህል አትበላ፤ ምን አትል ይኼው መከራችንን ነው የምናየው" ሲሉ የልጃቸው መጥፋት ቤተሰባቸውን እንደጎዳው ይናገራሉ።

"[አሁን ወቅቱ] የእርሻ ወራት ነበር። እርሻ አላርስ ብዬ ቅጡ ጠፍቶኝ ዛሬ ቤተሰቦችን በመንከባከብ እና አይዟችሁ በማለት ላይ ነው ያለሁት። መንግሥት እየረዳን ነው" ሲሉ ተስፋቸውን በመንግሥት ላይ መጣላቸውን ይናገራሉ።

ልጃቸውን ፍለጋ መሄጃው መንገድ የጠፋባቸው አቶ ሐብቴ ባለፉት ወራትን በጭንቅ እንዳሳለፉ ይናገራሉ "ከቤቴ ሆኜ ከማሰብ እና ከመጨነቅ በስተቀር። የማውቀው ነገር ለኝም።"

የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ልጃቸው ግርማ ከደብተሩ ውጭ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አባቱ ይናገራሉ። "የሚበላውን እንጅራውን እንኳን አያውቀውም። ሞኝ ዝም ብሎ የዋህ ነው። እሱ ነው የሚያስለቅሰኝ። ትምህርቱና የዋህነቱ ነው የሚያስለቅሰኝ። ሞኝ ነው የሚያውቀው ነገር የለም በቃ [እያለቀሱ]።"

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የታገቱት ተማሪዎች፡ የቤተሰብ ሰቀቀን እና የመንግሥት ዝምታ

አቶ ሐብቴ ከወራት በኋላም ተስፋ ሳይቆርጡ የልጃቸውን መምጣት እየተጠባበቁ ነው። "መንግሥት ሥራ እየሰራን ነው እያለን ነው። መንግሥት በእነሱ ሃሳብ ላይ ነው ያለነው ብሎ ነግሮናል። ዞሮ ዞሮ እምነቴ መንግሥት ላይ ነው ያለው። በገቡበበት ገብቶ ጉዳዩን መንግሥት ይፈታዋል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

አቶ ታረቀኝ ሙላቴ፤ የተማሪ ጤናዓለም ሙላቴ ታላቅ ወንድም

የደረሱበት ካልታወቀው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንዷ ጤናዓለም ሙላቴ አንዷ ናት። ከስድስት ወራት በፊት እንደታገተች የምትደዋወለው ከታላቅ ወንድሟ አቶ ታረቀኝ ሙላቴ ጋር ነበር።

"በወቅቱ እንደታገተች እኔ ጋር ነበር የምትደውለው 'ታግቻለሁ' አለች። 'ታግቻለሁ ምንም ማድረግ አልችልም' አለች" ሲሉ ክስተቱን ያስታውሳሉ።

"ከተያዘችበት ቀን አንስቶ እስከ በተለያዩ ቀናት በስልክ ታወራኝ ነበር። መጨረሻ ላይ 'በህይወት አለን እስካሁን ባለው እንሞታለን ብለን አናስብም። ምናልባትም ከዚህ በኋላ ስልክ ላይሠራ ይችላል። አትጨናነቁ በቃ'" እንዳለቻቸው ይናገራሉ።

እሳቸውም ስለደኅንነታቸው ሲጠይቋት "የያዟቸው ሰዎች 'አይዧችሁ አንገድላችሁም እህቶቻችን ናችሁ። እናንተን ምንም አናደርጋችሁም እያሉን ነው፤ እናንተ ጸሎት አድርጉልን' ብላ ነግራኛለች" ብለዋል።

ከዚህ በኋላም በስልክ ግንኙነታቸው ተቋረጠ። አቶ ታረቀኝ በተደጋጋሚ ስልክ ለመደወል ቢሞክሩም ጠፉ በተባለበት አካባቢ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ መገናኘት ስላልቻሉ እህታቸውን ተማሪ ጤናዓለምን ሳያገኙና ስለእሷ ሳይሰሙ እንሆ ወራት ተቆጠሩ።

"ለመንግሥት አሳወቅን። እነሱም ያለወን ነገር መንግሥት በአጭር ቀን ይፋ ያደርጋል" መባላቸውንና ልጆቹ በህይወት መኖራቸው ቢነገራቸውም "ከዚያ ወደዚህ ምንም ብለውንም አያውቁም። ማንም ደውሎልን አያውቅም። እኛም ያየነው የለም። ለፈጣሪ እየጸለይን ነው" ብለዋል።

የጤናዓለም ጉዳይ አለመታወቅ ባለፉት ወራት ቤተሰቡ ላይ ከባድ ሃዘንን ጭኗል ይላሉ አቶ ታረቀኝ "እናቴ ለቅሶዋ ወደር የለውም። መያዟን ከሰማችበት ቀን ጀምራ ሸራ አንጥፋ ውጪ ነው የምትተኛው። በየደብሩ እና በየጸበሉ ነው የምትንከራተተው።" ሲሉ እናታቸው ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ስለእህታቸው ለመስማት ወራትን የጠበቁት አቶ ታረቀኝና ቤተሰባቸው "ምናለ ሞቷን ወይንም ህይወቷን ቢያሰማን በሚል ነው እየተጨናነቅን ያለነው። መንግሥት ባለበት አገር ለወራት የደረሰችበት አለመታወቁ መላ ቤተሰቡን እየጎዳው ነው። እኛ ፖለቲካ አናውቅም ፖለቲካ አልጠየቅንም፤ ብቻ መንግሥት የእህቶቻችንን ሞት ወይ ህይወታቸወን ያሳውቀን።"

ተማሪዎቹ በህይወት አሉ ብለው የሚያምኑት አቶ ታረቀኝ ለማወቅ ግን ምንም መንገድ አለመኖሩ ቤተሰባቸውን አስጨንቆታል። "ካሉ አሉ ተብሎ ቢነግረን ካልሆነ ደግሞ ምን እናደርጋለን ማንም ሰው ላይሞት አልተፈጠረምና ከሞቱ ቤተሰብ እና አገር ይዘህ አልቅሰን እርማቸውን እናወጣ ነበር፤ አሁን ግን ያለንበት ጭንቀት አይወራል" በማለት መደበኛ ህይወታቸው እንደተስተጓጎለ ይናገራሉ።

መንግሥት ምን እያደረገ ነው?

ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ኃይል አቋቁሞ ለወራት የደረሱበት ስላልታወቁት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ በቅረቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ መንግሥት ከሰሞኑ አስታውቋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ግብረ ኃይል ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል እየሰራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለአሃዱ ቴሌቪዥን መናገራቸው ተዘግቧል።

ስለጉዳዩ መረጃ ለመስጠት የተገባው ቃል ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ እንደቻለ ነው ኃላፊው የተናገሩት።

ጨምረውም ከውስብስበነቱ ባሻገርም በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በርካታ ሰዎች በጉዳዩ ውስጥ መሳተፋቸው ጊዜ መጠየቁን እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 28 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ንጉሡ ገልጸዋል።

"ታግቼ ነበር ተማሪ ነበርኩ "ብለው በተለያየ መልኩ የቀረቡ ወደ 4 ያህል ተማሪዎች እንደተያዙ ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማድበስበስ የሞከሩም ተይዘዋል ብለዋል።

በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ግብረ ኃይል ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ስለጉዳዩን በመደበኛ መልኩ መረጃ ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ሲጠናቀቅ ዝርዝሩ ለሕብረተሰቡ ይገለጻል ሲሉ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል።

"ጉዳዩ በርካታ አካባቢዎችንና አካላትን አነካክቷል" ያሉት አቶ ንጉሡ፤ "የአማራ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት እንዲሁም በከፊል ከቤንሻንጉል ክልል የሚያገናኘው ነገርም ስላለ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሆነው በጋራ እየሰሩ ነው" ብለዋል።

ታህሳስ 2012 ዓ.ም

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ታህሳስ መጨረሻ ላይ ለጋዜጠኞች፤ ስለተማሪዎቹ መረጃውን ለመከላከያ እና ፌደራል መንግሥት መስጠታቸውን ገልጸው፤ ከተለቀቁት ተማሪዎች ውጪ "አራት ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ መረጃው አለኝ" ብለው ነበር።

ጥር 2/2012 ዓ.ም

ቢቢሲ ታግተው ከሚገኙት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል በሦስተኛው ቀን አመለጥከሉ ካለችው ተማሪ አስምራ ሹሜን አናግሮ ነበር። እሷም 17ቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 13ቱ ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግራ ነበር።

ጥር 19/2012 ዓ.ም

ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ የደረሱበት ያልታወቀው የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደኅንነት ያሳሰባቸው በተለያዩ የአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰልፎች አካሄዱ።

ጥር 21/2012 ዓ.ም

ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ከታገቱት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች ጋር ተወያዩ። በውይይቱም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ጥር 23/2012 ዓ.ም

በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ካገጠሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። ጨምረውም "በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለማድረስ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ እየተረባረበ" መሆኑንም አመልክተዋል።

መጋቢት 2/2012 ዓ.ም

የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ከአማራ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ባህር ዳር ተገኝተው ነበር። በባህር ዳር ቆይታቸውም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን በመሄድ ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ቢሞክሩም በተለያየ ምክንያት ኃላፊዎችን ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸዋል።

መጋቢት 17/2012 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መንግሥት ከወራት በፊት ባልታወቁ ሰዎች ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ታግተው የደረሱበት ስላልታወቁት 17 የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የወሰደውን እርምጃ እንዲያስታውቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

ማን ምን አለ?

ለወራት የደረሱበት ስላልታወቀው ተማሪዎች የተለያዩ ወገኖች መግለጫና አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል። ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የወሰደው እርምጃ የለም በማለት በርካቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

ከእነዚህ መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ባወጣው መግለጫ የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ እና ጥቃት አድራሾቹ ለሕግ እንዲቀርቡ መጠየቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው መግለጫም፤ የታገቱት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲለቀቁ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአስቸኳይ እንዲወጣ ጠይቋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ፌደሬሽን በተማሪዎቹ ላይ እየተፈፀመ ያለውና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት እንዲቆሙ፤ ጥፋተኞችም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

የአማራ ሴቶች ፌደሬሽንና እና የአማራ ሴቶች ማኅበርም የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ያለውን አቋም መንግሥት ግልፅ ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል።

የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በተማሪዎቹ ላይ የተፈፀመውን ድርጊት አውግዞ፤ ይህ የመንግሥት ችግር እንደሆነ እንደሚያምን ገልጾ ነበር።

'የታገቱት ተማሪዎች ይለቀቁ' የሚል ዘመቻም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። መንግሥትም መፍትሄ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ቆይቷል።

ለስድስት ወራት የደረሱበት ያልታወቁት እነዚህ የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በሚመለከት እስከ ዛሬ ድረስ በማን እንደተያዙና ያሉበትን ቦታ በእርግጠኝነት የገለጸ ወገን የለም።

ተማሪዎቹ ከጠፉበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የክልልና የፌደራል የመንግሥት አካላት ያሉበትን ለማወቅ ጥረት እያደሩ እንደሆነ ቢገልጹም "እዚህ ናቸው" የሚል ግን አልተገኘም።

ተማሪዎቹ የደረሱበት ሳይታወቅ በማን እጅና ለምን አላማ ለወራት እንደተያዙ አለመታወቁ የወላጆችንና የቤተሰቦችን ጭንቀት የከፋ አድርጎታል።

ለዚህም ነው መኖር መሞታቸውን አውቀን ተረጋግተን እንቀመጥ ካልሆነም እርማችንን አቅጥተን ለስቃያችን ፍጻሜ እናብጅለት የሚሉት።