ተማሪዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተደፍራ መገደሏ በናይጄሪያ ቁጣን ቀሰቀሰ

ኡዋቬራ ኡሙዙዋ

የፎቶው ባለመብት, UWAVERA OMOZUWA/FACEBOOK

ኡዋቬራ ኡሙዙዋ የተባለች የ22 ዓመት ተማሪ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተደፍራ መገደሏ ናይጄሪያዊያንን አስቆጥቷል፡፡ ገና ዩኒቨርስቲ ገብታ ማይክሮባይሎጂ ማጥናት የጀመረችው ይህቺ ወጣት ጸጥታው ስለሚስማማት ቤተ ክርስቲያን ሄዶ የማጥናት ልማድ ነበራት፡፡

ልጅቱ እያጠናች ሳለች ነው ባልታወቁ ሰዎች የተገደለችው ተብሏል፡፡ እህቷ እንደምትለው ደግሞ ከመገደሏ በፊት የመደፈር ጥቃት ደርሶባታል፡፡ ኡዋቬራ ነርስ ለመሆን ሕልም ነበራት፡፡

እኅቷ ጁዲዝ የኡዋቬራ ለቢቢሲ እንዳረጋገጠችው ሟች ጥቃቱ እንደደረሰባት ሆስፒታል ተወስዳ በሦስተኛ ቀኗ ነው ሕይወቷ ያለፈው ብላለች፡፡ ይህ ጥቃት የተፈጸመው በናይጄሪያ ቤኒን በምትባል ከተማ ውስጥ ነው፡፡

ጁዲዝ እንደምትለው ሟች እህቷ ከመገደሏ በፊት ተደፍራለች፡፡ ፖሊስ ልጅቱን ቤተ ክርስቲያን ሲያገኛት ቀሚሷ ተቀዳዶና ሸሚዟ በደም ርሶ እንደነበር አስታውቋል፡፡

ሆኖም የቤኒን ከተማ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግን ጥቃቱ ለጊዜው የግድያ እንጂ የመደፈር እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡

ሟች ዩኒቨርስቲ ገና መግባቷ ሲሆን አዘውትራ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ሄዳ የማጥናት ልማድ ነበራት፡፡ ከናይጄሪያ የሚወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚሉት ደግሞ ሟች በእሳት አደጋ ማጥፊያ ጭንቅላቷን ተደብድባ የተገደለችው ወደ ቤተክርስቲያኒቱ በዘለቁ ጎረምሶች ነው፡፡

ጎረምሶቹ ሟችን ከመግደላቸው በፊትም ደፍረዋታል፡፡ ናይጄሪያዊያን በክስተቱ በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣታቸውን በየማኅበራዊ ድር አምባው በሚጽፏቸው መልእክቶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡