ሁለቱ አሜሪካውያን በግል መንኩራኩር ሕዋ በመርገጥ ታሪክ ሰሩ

የአሜሪካ ጠፈርተኞች

የፎቶው ባለመብት, NASA

ሁለቱ የአሜሪካ ጠፈርተኞች ቦብ ቤንከን እና ዶግ ሃርሊ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ [አይኤስኤስ] በሰላም አርፈዋል።

ስፔስኤክስ በተሰኘው የግል ኩባንያ የተገነባቸው ድራገን የሚል መጠሪያ የተሰጣት መንኮራኩር [ካፕሱል] የዓለም አቀፉ ጠፈር ጣቢያን ተቀላቅላለች። ጣቢያው ከቻይና ወደ ሰማይ 422 ኪሎ ሜትር ላይ እየተንሳፈፈ ይገኛል።

ከብዙ ሙከራና ምርምር በኋላ በተሳካ ሁኔታ የመነጠቀችው የስፔስኤክስ መንኩራኩር ዶግና ቦብን ይዛ ኑሯቸውን ሕዋ ላይ ያደረጉ የአሜሪካና ሩስያ ጠፈርተኞች ተቀላቅላለች።

ቦብና ዶግ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ከአሜሪካ ምድር ወደ ህዋ የመጠቁ የመጀመሪያዎቹ ጠፈርተኞ ሆነዋል። አልፎም የግል መንኮራኩር በመጠቀም ወደ ሕዋ የበረሩ የመጀመሪያዎቹ በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።

የአሜሪካው የጠፈር ተመራማሪ ተቋም ናሳ ከዚህ በኋላ ወደ ሕዋ ደርሶ መልስ የሚደረጉ ጉዞዎችን በግል የጠፈር በራሪ መንኮራኩሮች ሊያደርግ እንደሚችል ፍንጭ ታይቷል።

ቢሊየነሩ የስፔስኤክስ ባለቤት ኢላን መስክ መንኮራኩሩ ወደ ሕዋ በሰላም መምጠቋ እጅግ አስደስቶታል።

ሁለቱ ጠፈርተኞች ወደ ሕዋ ጉዟቸውን ከጀመሩ ከ19 ሰዓታት በኋላ ነው ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የደረሱት። መንኮራኩሯ ወደ ጠፈር የተጓዘችው ከመሬት ሆነው በሚያንቅሳቅሷት ኮምፒውተሮች በመታገዝ ነው። ጠፈርተኞቹ ሲያርፉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንጂ ትምህርት የተሰጣቸው ሹፍርናው መሬት ባሉ ሰዎች የተመራ ነበር።

ጠፈርተኞቹ ጣቢያው ሲደርሱ የመንኮራኩሯ በር ተከፍቶ ወደ ጣቢያው በመንሳፈፍ መግባታቸው ተነግሯል። የጣቢያው መሪና የናሳ ጠፈርተኛ የሆኑት ክሪስ ካሲዲ እንዲሁም የሩሰያ ጠፈርተኞች ተቀብለዋቸዋል።

ጠፈርተኞቹ ከትንሽ እረፍት በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ቦብ አሳውቋል።

'ወደ ዚህ ስንመጣ [ወደ ጠፈር] ለሰባት ሰዓታት ገደማ ጥሩ እንቅልፍ ተኝተናል። የመጀመሪያው ለሊት ሁሌም ከባድ ቢሆንም ድራገን ግን በመልካም አየር የተሞላች ነበረች። ለዚህም ነው ጥሩ እንቅልፍ ያገኘነው' ሲል ዶግ በራድዮ መገናኛ መልዕክቱን አስተላልፏል።

የናሳ አለቃ የሆኑት ጂም ብራይደንስታይን ጥንዶቹ ላደረጉት የተሳካ በረራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዓለም መንኮራኩሯ በተሳካ ሁኔታ ስትበር ተመልክቷል፤ እኛም ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

ስፔስኤክስ ባለፈው ዓመት ወደ ጠፈር መንኮራኩር ቢልክም በውስጡ የሚተነፍስ ፍጡር አልነበረም። ቅዳሜ ዕለት ወደ ጠፈር የበረሩት ዶግና ቦብ ጣብያው ውስጥ ያሉ ማሽኖችን መርምረው ለባለሙያዎች አስተያየት መስጠት ነው ዓላማቸው።

የኦላን ድርጅትና ናሳ ቀጣይ ዕቅዳቸው ስድስት ሰዎች ማሳፈር የምትችል የጠፈር ታክሲ መገንባት ነው። ይህ ደግሞ 2.6 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ ይችላል ተብሏል።

ሁለቱ ጠፈርተኞች ሕዋ ላይ ምን ያክል ጊዜ እንደሚቆዩ አልታወቀም። ነገር ግን እስከ አራት ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ ይገመታል።

ሕዋ ላይ ቦብና ዶግና ጨምሮ 63 ሰዎች ይኖራሉ። በየቀኑ በተጠና መልኩ የሚኖሩት ጠፈርተኞች ዋነኛ ሥራቸው ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማካሄድ ነው።