በምዕራብ ትግራይ በመሬት ካሳ ጉዳይ ለተቃውሞ የወጡ '45 ሰዎች ታሰሩ'

የፎቶው ባለመብት, Amdom Gebreslasie FB page
በትግራይ ክልል ምዕራብ ዞን ቆራሪት በምትባል ከተማ በተቀሰቀሰ አዲስ ተቃውሞ ላለፉት ሁለት ቀናት መንገድ ዝግ ሆኖ መቆየቱ ተነግሯል።
የከተማዋ ነዋሪዎቹ በተቃውሞው ላይ "የመሬት ካሳ ይከፈለን፣ ለከብቶች መዋያ ቦታ ይሰጠን፣ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ይረጋገጥልን፣ በከተማዋ የመሬት ጉዳይ ጽ/ቤት ይዋቀርልን" የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ ደስታ ሃጎስ እና መምህር ገብረዋህድ፤ "የመሬት ካሳው ጥያቄው ስለቆየብን ተቸግረናል፤ የምንበላው አጥተናል። መንግሥት ከገጠር ወደ ከተማ ሲያስገባን ቃሉን ይጠብቃል ብለን አምነን ነበረ፤ ነገር ግን እስካሁን ካሳው አልተሰጠንም፤ ካሳው ይሰጠን" ሲሉ ጥያቄያቸው ይህ እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህም ጥያቄም በሰላማዊ ሰልፍ ተጀምሮ፤ ሰው እየተሰባሰበ ድንጋይ በመወራወር፣ መንገዶችን ወደ መዝጋት ማምራቱ የተነገረ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ የተዘጋው መንገድም የተከፈተውም ትናንት ነው።
የከተማው መስተዳደር እና ምክር ቤት እንደ አዲስ እየተዋቀረ ባለባት ቆራሪት ከተማ ከአመራሮቹ አንዱ አቶ ኪዳነማሪያም አባይ፤ ከሕዝቡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ትክክል መሆኑን አምነው፤ "አንዳንድ ሰዎች ግን የሕዝቡን ጥያቄ ተገን በማድረግ ድንጋይ እንዲወረወር፤ መንገድ እንዲዘጋና ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ አድርገዋል" ብለዋል።
"የሕዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለስን ነው" ያሉት አቶ ኪዳነማሪያም፤ አሁንም ጥያቄዎቻቸው ተገቢ ስለሆኑ እንደሚመልሱ እና ጥያቄዎቹን ለበላይ አካልም እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
አቶ ኪዳነማሪያም አክለውም "ያልተፈለገ አመጽና አድማ የፈጠሩ ሰዎችን ሥርዓት ማስያዝ ስላለብን የተወሰኑ ሰዎችን ወስደን ልንገስጽ እንፈልጋለን። የታሰሩ ሰዎችም አሉ። እነሱን መክረን እንመልሳቸዋልን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተቃውሞውን ተከትሎ 45 ሰዎች እንደታሰሩ ቢነገርም፤ አመራሩ ግን ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋ።
ስለቆራሪት ከተማ
ቆራሪት ከተማ የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው ከሚሰራቸው አንዱ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትን ተከትሎ በ2005 ዓ.ም ተዋቀረች። በተለይ ለስኳር የሸንኮራ አገዳ ምርት በጣም ሰፊ መሬት ያስፈልግ ስለነበር ለዚህ አገልግሎት ሲባል ከእርሻ መሬታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች ነበሩ።
እነዚህን አርሶ አደሮችን አሁን ከተማዋ ወደምትገኝበት ቦታ ተወስደው ቆራሪት የሚባል ከተማ ተመሰረተች። አርሶ አደሮችም ኑሯቸውን እዚያው አደረጉ።
ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ለነበራቸው የእርሻ መሬት እንዲሁም የከብቶች መዋያ ላለፉት 7 ዓመታት የመሬት ካሳ ሲጠይቁ ቆይተዋል። አንዳንዶቹ ጥያቄያቸው የተመለሰላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ እስካሁን ድረስ የመሬት ካሳ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ።
ከሰሞኑ ሲያነሱት የነበረው ጥያቄም የመሬት ካሳ ይሰጠን የሚል ሲሆን፤ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄያቸው እንዲመለስ፤ መሬታቸው ወደ ልጆቻቸው በውርስ መልክ በማስተላለፍ የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የህወሓት አቋምና የብልጽግና መልስ
የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው ህወሓት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ በክልልም በአገርም ደረጃ ህገ መንግሥታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል። ውሳኔው የምርጫ ቦርድና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚሳተፍበትና ዕውቅና የሚሰጡት ምርጫ ለማካሄድ ነው። ብልጽግና ፓርቲ፤ ሕገ መንግሥታዊ ምርጫ እናካሄዳለን በማለታችን ምክንያት፣ ለሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ክብር ስለሌለው፤ ጦርነት አውጆብናል ብሏል ባወጣው መግለጫ። በብልጽግና ፓርቲ በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አወሉ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።