አሜሪካ ሕግን በመጠቀም ጥቁር ዜጎቿ ላይ ግፍ ትፈፅማለች?

ተቃዋሚዎች የጆርጅ ፍሎይድን ፎቶ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሰሞኑ አሜሪካዊው ነጭ ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን አንገቱን ከመሬት አጣብቆ ትንፋሽ እስኪያጥረው ድረስ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ተንበርክኮበት በመቆየቱ ህይወቱ አልፏል።

ዓለምም ጆርጅ ፍሎይድ ህይወቱ እንድትተርፍ ሲማፀን፣ የሞቱ እናቱን እንዲደርሱለት ሲጣራ፣ የመጨረሻ እስትንፋሱን እንዲሁም ህይወት አልባ ሰውነቱን ተመልክቷል።

በሚኒያፖሊስ እንደ እንስሳ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት አሜሪካን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችን እንዲሁም የመብት ታጋዮችን ቁጣና ተቃውሞ አቀጣጥሏል።

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ለመቶዎች ዓመታት የቆየውን መዋቅራዊ ጭቆና፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የፖሊስ ጭካኔና ሌሎችም መሰረታዊ ችግሮች ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

ብዙዎችም ጥቁር አሜሪካውያን በባርነት ንግድ በግዞት ከመጡ ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍም፣ ለነፃነት የተደረጉ ትግሎችን እንዲሁም እንዴት አሜሪካ ጥቁር ዜጎቿ ላይ አሁንም ቢሆን እንዴት አይነት ግፍ እንደሚፈፀምባቸው እየተናገሩ ነው፤ እየፃፉም ነው።

ሚሊዮን ጥቁር አሜሪካውያን በማረሚያ ቤቶች በሚማቅቁባት፤ አገሪቱ ያወጣቻቸው ሕግና ሥርዓቶች መዋቅራዊ ጭቆና ያደርሳሉ ወይ?

እስቲ አገሪቱ ፍትህን በማስፈንና ወንጀልን በመቆጣጠር ዘርፍ ረገድ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚፈፀሙ መድሎዎችን እንመልከት

  • ቁር አሜሪካውያን በፖሊስ ጥይት ክፉኛ የመቁሰል ወይም የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ነው

ከታዳጊዎች ጀምሮ በተለያዩ እድሜ የሚገኙ ላይ ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊስ ጥይት ቆስለዋል እንዲሁም ተገድለዋል።

በአስራዎቹ የሚገኙ ጥቁር ታዳጊዎችም በፖሊስ በተገደሉባቸው ወቅቶችም ፖሊሶች "ለህይወታችን ፈርተን ነው፤ ሽጉጥ ሊያወጡ መስሎን ነው" የሚሉ ምላሾች ሲሰጡም ተሰምተዋል።

ይህንንም መሰረት በማድረግ የአሜሪካ ፖሊሶች ተጠርጣሪ ናቸው ብለው ጥይት የተኮሱባቸውን ሰዎች በምናጤንበት ወቅት ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊሶች በጥይት መመታት ወይም የመገደላቸው እድል ከፍተኛ ነው።

ከጥቁር አሜሪካውያን በመቀጠልም ከነጭ ሕዝቦች በበለጠም ቀደምት ሕዝቦች፣ እንዲሁም ላቲን አሜሪካውያንም በፖሊሶች ይተኮስባቸዋል እንዲሁም ይገደላሉ።

በአሜሪካ ከዓመት በፊት የነበረውን የሕዝብ ቁጥር ብናይ ጥቁር አሜሪካውያን አስራ አራት በመቶ ቢሸፍኑም፤ ፖሊስ ክፉኛ ካቆሰላቸው ወይም ከገደላቸው አንድ ሺህ ሰዎች ውስጥ 23 በመቶውን ይሸፍናሉ።

ይህም ቁጥር ከጎርጎሳውያኑ 2017 ዓመት ጀምሮ በተመሳሳይ መልኩ እየሄደ ሲሆን፤ በተቃራኒው በፖሊሶች በሽጉጥ የሚተኮስባቸው ወይም የሚገደሉ ነጮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

  • ጥቁር አሜሪካውያን ከነጮች በበለጠ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተገናኘ ለእስር ይዳረጋሉ

በአሜሪካ ውስጥ የአደንዛዥ ዕፅን መጠቀም በነጮችና በጥቁር አሜሪካውያን ተመሳሳይ ሁኔታ ቢኖረውም፤ ጥቁር አሜሪካውያን አደንዛዥ ዕፅ ይዘው ከተገኙ ዘብጥያ ይወርዳሉ።

Drug abuse arrests by race. .  Hispanics are not counted separately. Others is Asian, American-Indian, Hawaiian or Pacific islanders..

ለምሳሌ በጎርጎሳውያኑ 2018 የተደረጉ እስሮችን እንደ ማጣቀሻ ብናይ፤ በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ያለው እስር 750 ከመቶ ሺህ ሲሆን ለነጭ አሜሪካውያን ደግሞ 350 ከመቶ ሺህ ነው።

ነገር ግን ብሔራዊ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም ላይ ከጎርጎሳውያኑ 2018 በፊት በተደጋጋሚ የወጡ ቁጥሮችን ብናይ በነጭ አሜሪካውያንና በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ የዕፅ አጠቃቀም ልማድ ተመሳሳይ ነው።

ሆም የአሜሪካ የሲቪል መብቶች ህብረት ባደረገው ጥናት ጥቁር አሜሪካውያን ድንገት ዕፀ ፋርስ ይዘው ቢገኙ ያለምንም ምህረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ከነጮች ጋር ሲወደዳር 3.7 እጥፍ እንደሆነም መረጃው አመላክቷል።

  • በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥቁር አሜሪካውያን በእስር ላይ ናቸው

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በጥቃቅን ወንጀሎች እስር ላይ እንደሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለያየ ጊዜያትም አሜሪካ ጥቁርና ላቲን ሕዝቦቿን ወደ እስር ቤት በመወርወር ለነፃ የጉልበት ሥራ ዳርጋቸዋለች እንዲሁም የተለያዩ ኩባንያዎችም የእስር ቤት ጉልበትን በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ የሚኣመለክቱ በርካታ ፅሁፎች ወጥተዋል።

በእስር ላይ የሚገኙ ጥቁር አሜሪካውያን ከነጮች ጋር ሲወዳደር አምስት እጥፍ እንዲሁም ከላቲን አሜሪካውያን ጋር ሲወዳደር ደግሞ በእጥፍ ይበልጣል።

በጎርጎሳውያኑ 2018 ያለውን የህዝብ ቁጥር ስንመለከት የጥቁር አሜሪካውያን ቁጥር አስራ ሦስት በመቶ ቢሆንም በእስር ቤት ካሉት ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተቃራኒው ነጭ አሜሪካውያን የአገሪቱን የሕዝብ ቁጥር 60 በመቶ ቢሆኑም በእስር ቤት ካሉት ግን 30 በመቶው ብቻ ናቸው።

ይህም ማለት ከመቶ ሺህ ጥቁር አሜሪካውያን መካከል አንድ ሺህዎቹ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆን፤ የነጭ አሜሪካውያን ደግሞ 200 ከመቶ ሺህ ነው።

ይህ ቁጥር በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከአንድ ዓመት በላይ እስር ከተፈረደባቸው የተወሰደ ነው።

ምንም እንኳን ባለፉት አስር ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ቁጥር ቢቀንስም፤ አሁንም ከሌሎች ዘሮች በበለጠ ጥቁር አሜሪካውያን በእስር ይገኛሉ።