ታዋቂዎቹ ጠላፊዎች 'አኖኒመስ' በፍሎይድ ሞት ማግስት የፖሊስን ወንጀል ለማጋለጥ ተመልሰው ይሆን?

የአኖኒመስ ጭምብል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ ታንቆ መገደሉን ተከትሎ የአሜሪካ ግዛቶች በተለያዩ ተቃውሞዎች እየተናጡ ይገኛሉ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ለበርካታ ጊዜያት ከሚዲያ አይን ተሰውረው የነበሩት መረጃን በመመንተፍ እንታገላለን የሚለው 'አኖኒመስ' የተሰኘው የጠላፊዎች ቡድን አባላትም ከተደበቁበት ብቅ ብለዋል።

ኢ-ፍትሃዊነትን አስፍነዋል በሚሏቸው ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የሳይበር ጥቃትም በማድረስም የጠላፊዎቹ ቡድን በሚዲያው ዘንድ ከፍተኛ እውቅናን አትርፏል።

በቅርብ ዓመታት ድምፃቸውን አጥፍተው የነበረ ሲሆን በቅርቡ የደረሰውን የጆርጅ ፍሎይድን ግድያንም ተከትሎ የሚኒያፖሊስ ፖሊሶች የሚፈፅሙትን በርካታ ወንጀሎች ለዓለም እናጋልጣለን በማለትም ማንሰራራታቸው እየተነገረ ነው።

ሆኖም ይህ ሚስጥራዊ ቡድን በዚህ ወቅት ምን ሊያጋልጥ ይችላል የሚለውንም ማወቅ አይቻልም።

አኖኒመስ ማናቸው?

የጠላፊዎቹ ቡድን ማንነት አይታወቅም፤ እንዲሁም እንደሌሎች ቡድን መሪም የላቸውም። ራሳቸውን የሚገልፁትም "እልፎች፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ስብስብ" በማለት ነው።

ማዕከላዊ የሆነ የመመሪያ መዋቅር በሌለበት ማንኛውም ሰው የቡድኑ አባል መሆን ይችላል።

ይሄም ማለት አባላቱ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ይለያያሉ፤ እንዲሁም ነጠላ የሆነ አጀንዳ የላቸውም።

ነገር ግን በአጠቃላይ ኃይልን ያለአግባባብ የሚጠቀሙትን ኢላማ ያደረገ የመረጃ መንታፊዎች ቡድን ነው። አሰራራቸውም ድረገፆችን በመጥለፍ እንዲሁም የሳይበር ጥቃቶችን በማድረስ ለሕዝቡ ያጋልጣሉ።

ምስላቸውም ጭምብል ሲሆን፤ ይህ ጭምብልም አለን ሙር የተባለው ፀሐፊ ሙሰኛ የሆነን የፋሽስት መንግሥት ለማንኮታኮት የተደረገ የሕዝብ አብዮት ላይ የሚያጠነጥነው 'ኖቭል ቨርሰስ ፎር ቬንዳታ' የተሰኘው ፅሁፍም ከፍተኛ እውቅናን አትርፎለታል።

በቅርቡ ምን አከናወኑ?

ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር ተያይዞ የደረሱ የሳይበር ጥቃቶች አኖኒመስ ያከናወናቸው ናቸው እየተባሉ ነው።

አንደኛ የሚኒያፖሊስ ፖሊስ ድረገፅ በጊዜያዊነት ከጥቅም ውጪ ሆኖ ነበር። ምንም እንኳን ድረገፆችን በጊዜያዊነት ከጥቅም ውጪ ማድረግ ይህን ያህል የረቀቀ ባይሆንም ለሳይበር ጥቃት አድራሾቹ ግን ስኬት ነው።

ይህም የድረገፆችን ዋነኛ ማዕከልን በመረጃዎች በማጨናነቅ እንዳይሰራ በማድረግ ከጥቅም ውጭ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፤ ልክ የመገበያያ ድረገፆች ተፈላጊ ምርትን ለመግዛት በርካታ ሰዎች በሚጎበኙበት ወቅት እንደሚፈጠረው ማለት ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከፖሊስ ክፍሉ ተጠለፉ የተባሉ የኢሜይል አድራሻዎችና የይለፍ ቃሎች የመሳሰሉ የመረጃ ስብስቦችም ብዙዎች አኖኒመስ መንትፏቸዋል በሚልም እየተጋሩ ነው።

ነገር ግን የፖሊስ ድረገፁ በአኖኒመስ ተጠልፏል ለሚለው ምንም የተረጋገጠ መረጃ የለም። ትሮይ ሃንት የተባለ ተመራማሪም እነዚህ መረጃዎች በአሁኑ ወቅት የተጠለፉ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በነበሩ ክፍተቶች የተገኙ እንደሆኑ ይናገራል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገፅም ላይ "ነፍስህን ያሳርፍ ጆርጅ ፍሎይድ" የሚል መልዕከት ከአኖኒመስ አርማ ጋር የወጣ ሲሆን ይህም ሁኔታ ሌላኛው ቡድኑ ተመልሷል የሚለው ማመላከቻ ነው።

የፎቶው ባለመብት, UN

ከዚህም በተጨማሪ በትዊተርም ላይ ፖሊሶች በሬድዮዋቸው ሙዚቃ ሲያጫውቱ እንዲሁም መገናኛ ዘዴዎችን ሲያጠፉም የሚያሳዩ ቪዲዮዎችም የቡድኑ ነው ተብሎ ወጥቷል።

ነገር ግን በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች እነዚህ ቪዲዮዎች እውነተኛ ከሆኑ የጠላፊዎች ሥራ ሳይሆን ከተሰረቁ ኮምፒውተሮች ላይ የተገኙ መረጃዎች መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተወንጅለውባቸው የነበሩና በከሳሾቻቸው በጎ ፈቃድ የተተው የፍርድ ሂደቶችም በአኖኒመስ የመረጃ ጠላፊዎች አማካኝነት ተብሎም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረገፆች ላይ እየተጋራ ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በዘር ጉዳይ አኖኒመስ ምን ብሎ ያውቃል?

በቡድኑ አባላት መካከል አካሄዳቸው ተመሳሳይ ባለመሆኑ የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲሁም ጉዳዮችን ያነሳሉ። ከዚህም ቀደም ከዘር ጋር በተገናኘ የቡድኑ አባላት የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተዋል።

በጎርጎሳውያኑ 2014 በፈርጉሰን ሚዞሪ በፖሊስ የተገደለውን ማይክል ብራውንን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ በአገሪቱ ተነስቶ ነበር።

በዚህም ወቅት ተቃዋሚዎች አንድ ጥቃት ቢደርስባቸው የአፀፋ ምላሹ የከፋ እንደሚሆንም ዛቻና ማስፈራራያም ልከው ነበር።

እንዳሉትም የከተማ አስተዳደሩን ድረገፅ ከጥቅም ውጪ በማድረግ እንዲሁም የከተማዋን የፖሊስ ኃላፊንም ኢላማ አድርገው ነበር።

በቀጣዩ ዓመትም እንዲሁ "በነጭ የበላይነት የሚያምነውና ጥቁሮችንም በመግደል" የሚታወቀው የኩ ክላክስ ክላን (ኬኬኬ) አባላትም ላይ የሳይበር ጦርነት አውጀዋል። የአባላቱንም ግላዊ መረጃዎች ይፋ እንደሚያደርጉም አሳውቀው ነበር።

ሆኖም አንዳንድ አባላቶቹ ፀረ- ነጭ ዘረኝነት ያካሂዳሉ በሚልም የብላክ ላይቭስ ማተር እንቅስቃሴ ድረገፅ ላይ ጥቃት አድርሰዋልም ተብሏል።

አኖኒመስ ተመልሷል ማለት ይቻላል?

የጆርጅ ፍሎይድ መሞት በአገሪቱ ውስጥ ከጎርጎሳውያኑ 1968 የማርቲን ሉተር ኪንግ መገደልን ተከትሎ ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞና ቁጣን እንዳስከተለ የኒውዮርኩ የቢቢሲ ዘጋቢ ኒክ ብርያንት ገልጿል።

የአኖኒመስ ቡድን የሚኒያፖሊስን ወንጀሎች አጋልጣለሁ አለ በተባለበት ፌስ ቡክ ገፅም በተመሳሳዩ ከሌላ ዓለም ስለመመጡ ፍጡራን (ዩፎዎች) እና የቻይና ዓለምን በበላይነት የመምራት እቅድን በተመለከተ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

ምንም እንኳን እነዚህ ጉዳዮች ይህንን ያህል እይታ ባይስቡም የሚኒያፖሊስ ፖሊስ ድረገፅ በጊዜያዊነት ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጠላፊዎቹም ቡድን እንደገና መወያያ ሆኗል።

በሳይበር ጥቃቶች ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ይህ ቡድን በመጀመሪያም የሚዲያዎች ርዕሰ ዜና መሆን የቻለውም በጎርጎሳውያኑ 2008 ነው።

የሰው ልጅ አይሞትም በሚለው እምነታቸውም መወያያ የሆኑትንም የሳይንቶሎጂ እምነት ድረገፅን ከጥቅም ውጪ በማድረግ እንዲሁም መገናኛ ዘዴዎቻቸውንም በመረበሽ አኖኒመስ ይታወቃል።

ከዚያም ተከትሎ በመጣው የዓለም የኢኮኖሚ እንዲሁም የፖለቲካ ቀውሶች ላይም እጃቸውን አስገብተዋል። የአረብ የፀደይ አብዮትን ደግፈዋል በተጨማሪም አሜሪካ ውስጥ የተካሄደውን የ'ኦኩፓይ ዋል ስትሪትን'ም ተቃውሞ እንዲሁ ከሚጠሩባቸው በርካታ ተቃውሞቻቸው የሚወሱ ናቸው።

ለተለያዩ አላማዎችም ድጋፎቻቸውን በመስጠት በተለያዩ አገራት ለሚደረጉ ሰልፎችና ተቃውሞችም አስተዋኦቸውን አድርገዋል። ሆኖም በቅርብ ዓመታት በትልልቅ ሚዲያዎች ላይ ስማቸው ደብዝዞ ነበር።

ነገር ግን ለዓመታት የገነቡት አብዮታዊ ምስል እንዲሁም ኃይል ያላቸውን አካላት የመገዳደር ጉልበታቸው በተቃውሞ እየተናጠች ባለችው አሜሪካ ስማቸው እንደገና እንዲያንሰራራ ሆኗል።