ቢል ጌትስ በክትባት ስም ክንዳችን ውስጥ ሊቀብሩት ያሰቡት ነገር አለ?

ቢል ጌትስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማኅበራዊ ድር አምባው በሴራ ንድፈ ሐሳብ አብዷል። ይህ የሴራ ትብታቦ (Conspiracy theory) በተለይ ከኮቪድ-19 ክትባት ጋር በተያያዘ ከሯል።

የሴራ ንድፎች እንዲሁ ቸል የሚባሉ ጉዳዮች አይደሉም። የሴራ ፈታዮችም ሥራ ፈቶች ሊባሉ አይችሉም። ምክንያቱ ደግሞ ብዛታቸው ነው። ልብ ማለት የሚገባን ስለ ሴራ ትንተና ስናስብ ስለ ብዙሃኑ ሕዝብ አስተሳሰብ እያወራን እንደሆነ ነው።

ሴራ ፈታዮች እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ከመሆናቸው የተነሳ መልዕክታቸው በአጭር ሰዓት ውስጥ ክፍለ ዓለምን ሊያጥለቀልቅ ይችላል።

ለምሳሌ ዩጎቭ የተባለ የጥናት ቡድን በአሜሪካ በ1ሺህ 640 ሰዎች ላይ በሠራው ቅኝት 28 ከመቶ አሜሪካዊያን ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ በክትባት ስም ክንዳችን ላይ አንዳች ረቂቅ ዲጂታል ሜሞሪ (microchip) ሊጨምርብን ይፈልጋል ብለው ያምናሉ። ይህ አሐዝ ከሪፐብሊካን ደጋፊዎች ዘንድ ሲደርስ 44 ከመቶ ይደርሳል።

ለመሆኑ ቢል ጌትስ ምን ፈልጎ ነው ሚሞሪ ዲስክ ክንዳችን ላይ የሚቀብረው?

ይህን ለመመለስ ኮቪድ-19 ቫይረስ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚለውን በሴራ ነዳፊዎች መነጽር ማየት ይኖርብናል።

በሴራ ነዳፊዎች እስሳቤ ቫይረሱን የፈጠረው የማይክሮሶፍት ፈጣሪ ቢል ጌትስ ነው። የዚህ አንድ ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱት ደግሞ ቢልጌትስ ከዚህ ቀደምም ይህ ቫይረስ ሊከሰት እንደሚችል ያውቅ የነበረ መሆኑን ነው።

ቢሊየነሩ ቢልጌትስ ዓላማው የዓለምን ሕዝብ ሁለመናውን መቆጣጠር ስለሆነ መጀመርያ ቫይረስን ፈጠረ፣ ቀጥሎ ደግሞ ክትባቱን ይፈጥራል ይላሉ። ክትባቱ ውስጥ ደግሞ በዓይን የማይታይ ረቂቅ ዲጂታል ሚሞሪ (microchip) ይቀብርብናል በማለት ያስባሉ።

ቢቢሲ ይህ ነገር እውነት ነው ወይ? ሲል የቢልጌትስ ፋውንዴሽንን ጠይቆ "ቅጥፈት ነው" የሚል ምላሽ አግኝቷል።

ይህ የሴራ ትንታኔ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ የሚያጠነጥን አይደለም።

የሩሲያ ኮሚኒስትር ፓርቲ መሪ "እነዚህ በሉላዊነት የሰከሩ ሰዎች በክትባት ስም በድብቅ ክንዳችን ውስጥ መቆጣጠርያ ሊከቱብን ይፈልጋሉ" ሲሉ ተሰምተዋል።

የቀድሞው የዶናልድ ትራምፕ አማካሪ ሮጀር ስቶን ከሰሞኑ በሰጡት አንድ አስተያየት ደግሞ "አንዳንድ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ መመርመር አለመመርመራችንን ለማጣራት እንዲረዳ አንዳች ነገር እጃችን ውስጥ ይቀበር እያሉ ነው" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ይሁንና ሚስተር ሮጀር አስተያየታቸው ላይ የቢል ጌትስን በስም አልጠቀሱም።

ይህ በቢልጌትስ ዙርያ የተተበተበው ሴራ እየተጠናከረ የመጣው ባለፈው መጋቢት ራሳቸው ቢል ጌትስ የሰጡትን አንድ አስተያየት ተከትሎ ነው።

". . . ወደፊት አንዳች የሆነ ዲጂታል ሰርተፍኬት ሊኖረን ይችል ይሆናል፤ ይህም ቫይረሱ ያለብን እና ነጻ የሆነው ለመለየት የሚያስችለን ነው የሚሆነው. . . ።" ብለው ነበር፤ በንግግራቸው መሀል።

"ዲጂታል ሰርተፊኬቱ ማን እንደተመረመረ፣ ማን ቫይረሱ እንዳለበት፣ ማን ክትባት እንደወሰደ አጥርቶ ይነግረናል"› ሲሉም አብራርተዋል።

ይህን ተከትሎ ወዲያውኑ አንድ ጽሑፍ ታተመ። የጽሑፉ ርዕስ "ቢል ጌትስ ቫይረሱን ለመዋጋት ረቂቅ ድጂታል ሜሞሪ ክንድ ላይ መቅበር ያስፈልጋል አሉ" የሚል ነበር።

ይህ ጽሑፍ ደግሞ ለዘገባው መነሻውን ያደረገው በጌትስ ፋውንዴሽን ትብብር የተሰራ አንድ ጥናትን ነበር።

ጥናቱ የሚያወራው ሰዎች ክትባት ስለመውሰዳቸው የሚያሳውቅ የመረጃ ቋት ስለማዘጋጀት ነው። ክትባት ሲወስዱ የመርፌው ጫፍ ቀለም ስለሚኖረው ያን ጊዜ የወሰደውና ያልወሰደውን መለየት ከባድ አይሆንም ብሎ ያምናል።

ኾኖም በዚህ ጥናት የተጠቀሰው ቴክኖሎጂ ክንድ ውስጥ የሚቀበር ረቂቅ ሜሞሪ ዲስክ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ይህ በየመሸታ ቤቱ ወይ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች ሲዘጋጁ የከፈለና ያልከፈለ፤ ትኬት የያዘና ያልያዘን ለመለየት በር ላይ በታዳሚዎች አይበሉባ ላይ የሚታተመው ዲጂታል ቀለም ዓይነት ነው። ወይም ይበልጥ ለመረዳት ንቅሳት ልንለው እንችላለን።

ወ/ት አና ጃክሌኒክ የተባለች የዚሁ ጥናት ባልደረባ እንደምትለው ይህ የንቃሳት ሐሳቡ ራሱ ገና ሐሳብ ነው፤ ተግባራዊ እንኳን አልተደረገም። በጭራሽ ሰዎችን ለመከታተልም የሚተገበር ጥናት አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, TOBIAS SCHWARZ

የምስሉ መግለጫ,

በርካታ የሴራ ትንተናዎች በአሁኑ ጊዜ ቢል ጌትስ ላይ ያተኮሩ ናቸው

ቢል ጌትስ ሊቆጣጠረን ነው የሚሞክረው?

የማይክሮሶፍቱ ፈጣሪ፣ በጎ አድራጊና ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ ለሴራ ፈታዮች የተመቹ ሰው ሆነዋል።

በእንግሊዝ አንድ ብዙ ተከታዮች ያሉት የትዊተር ሰሌዳ "ቢል ጌትስ በቫይረሱ በአሜሪካ 700 ሺህ ሰዎች እንደሚሞቱ አረጋገጡ" ብሎ ጻፈ። ይህን ካለ በኋላ ጽሑፉን አሌክስ ጆንስ ከተባለ አንድ ቀኝ አክራሪ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ገጽ ላይ ከነበረ ቪዲዮ ጋር አሰናሰለው።

ይህ የትዊተር መልዕክት 45 ሺህ ሰዎች ተጋርተውታል። ሰዎች ያልተረዱት ነገር ግን ቢል ጌትስ ያንን አለማለታቸውን ነው።

በቪዲዮው ላይ ቢል ጌትስ እያወሩ የነበረው በሕክምናው ዓለም ክትባት ጊዜና ሰፊ ጥናት የሚፈልግ እንደመሆኑ፤ ይህ ሳይደረግ ቢቀር የጎንዮሽ ጉዳቱ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለማሳየት የተናገሩት ነበር። በተለይም በሽማግሌዎች ዘንድ።

ይህንንም ለማስረዳት መላምታዊ ቁጥር አስቀመጡ።

"ለምሳሌ እንበልና ከ10 ሺህ ሰዎች በአንዱ አዛውንት ላይ እንኳ ክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ቢያመጣ በአሜሪካ 700 ሺህ ሰዎች ሞቱ ማለት ነው" የሚል።

ይሁን እንጂ የሴራ ተንታኞች እንደሚሉት ቢል ጌትስ በዚያ ንግግራቸው በአሜሪካ 700 ሺህ ሰዎች ያልቃሉ አላሉም። ያንን ለማስፈጸምም እየሠሩ አይደለም። ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃም የለም።

የሚደንቀው ይህ የሴራ ትንተና አራማጆች ቢል ጌትስን በተመለከተ እየፈጠሩ ያሉት ተጽእኖ ከጣሊያን የተወካዮች ምክር ቤት ሸንጎ ድረስ ሰተት ብሎ መግባቱ ነው።

ዴንትሮ ላ ኖቲዚያ የተባሉ አንድ የጣሊያን ፓርላማ አባል "ቢል ጌትስን ወስደን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለምን አንገትረውም" ሲሉ ጠይቀዋል።

ከቢል ጌትስ ሌላ ያሉ የክትባት መላምቶች

በጣሊያን ጸረ-ክትባት እንቅስቃሴው ተጧጡፏል።

አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተመለከቱት የተባለ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል በጣሊያን ዝነኛ ሆኗል። የቪዲዮው ጭብጥ ቫይረሱ ሆን ተብሎ መፈጠሩን የሚያወሳ ነው።

የዚህ ቪዲዮ ተራኪ ስቴፋኖ ሞንታናሪ ይባላል። ጣሊያናዊ ተመራማሪ ነው። እንዲያውም በፋርማሲ ቅመማ ዘርፍ ዲግሪ አለው። እሱ እንደሚለው ቫይረሱ የተፈጠረው የሰው ልጆች በግዳጅ ክትባት እንዲወስዱ ለማመቻቸት ነው። ከክትባቱ ጀርባ ደግሞ ቢል ጌትስ አለ ይላል።

"ይህ ወረርሽኝ እንዲቀጥል ይደረጋል። እንዲቀጥል የሚደረገው ክትባት እንድንወስድ ለማስፈራራትና ለማሳመን ነው። ከዚያ ሐብታሞች የበለጠ ሀብታም ይሆናሉ" በማለት ሞንታናሪ ለማሳመን ይሞክራል።

የዚህ ሴራ ተንታኞች በእሲያም ተበራክተዋል። ሕንድ በየጊዜው አዳዲስ አሉባልታዎች የሚሰሙባት አገር ናት። በዚያ አገርም ቢሆን ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣን ክትባት ላለመቀበል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

ሕንድ ውስጥ ያሉ የሴራ አራማጆች አገራቸው ክትባቱን ከላም ሽንት እንደምታገኝ ያምናሉ።

በሕንድ በፌስቡክ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ዘመቻ ከዚሁ ከላም ሽንት ጋር የተገናኘ ሆኗል።

መረጃውን ሺህዎችና ሚሊዮኖች በየቀኑ የሚጋሩት ጉዳይ ነው። ነገሩ 'አህመዳባድ ሚረር' ከተሰኘ ጋዜጣ ዜና ጋር የተያያዘ ነው።

ይህ ጋዜጣ በሕንድ ቅዱስ ከሆኑ ላሞች መድኃኒቱ ሊገኝ ይችላል የሚል ይዘት ያለው ዘገባ ሰርቶ ነበር።

ክትባቱ የሚቀመመው ታዲያ ከላም ሽንት፣ ከቅቤና አዛባ ይሆናል።

ከዚህ ዘገባ ቀደም ብሎም ቢሆን በርካታ ሕንዳዊያን ቫይረሱን ለመከላከል የላም ሽንት መጠጣት ጀምረው ነበር። አሁንም እየጠጡ ነው። በዚያ አገር ለላም ትልቅ ቦታ ይሰጣታል። ላም ቅድስት ናት።

የሚገርመው ደግሞ ይህ ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘው ሴራና መላምት በጊዜ ሂደት መልኩን እየቀየረ መሄዱ ነው። ነገሩን መጀመሪያ የሴራ ፈታዮች ምንጭ አድርገው የወሰዱት አህመዳባድ ሚረር ከተባለ ጋዜጣ ቢሆንም ጋዜጣው መድኃኒት ከሽንት ይገኛል ብሎ አልጻፈም።

ከዚያ ይልቅ ጋዜጣው አንድ ሐኪምን ጠቅሶ የዘገበው "የላም ሽንት መድኃኒትነት ስላለው ለኮቪድ-19 የሚሆን ንጥረ ነገር ሊገኝበት ይችላል" የሚል ጽሁፍን ነበር ያሰፈረው።

የሴራ ትንተና አራማጆች ግን ጉዳዩን ከዚህ ብዙ አርቀው ወስደውታል።

ቢቢሲ የሕንድ ሕክምና ምርምር ማዕከል ኃላፊ የሆኑትን ዶ/ር ራጂኒ ካንትን ስለ ላም ሽንት ወይም አዛባ ኮሮናቫይረስን ይፈውሳሉ ወይ ሲል ጠይቋቸዋል።

እርሳቸው ሲመልሱ "ይህን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት መረጃ የለም፤ የተደረገ ምርምር ስለመኖሩ አላውቅም" ብለዋል።

በሕንድ የግብርና ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመ አንድ ክፍል ግን ለኮሮናቫይረስ ለጊዜው ክትባት ባይገኝም ምናልባት ክትባቱ ከላም ሽንትና አዛባ፣ እንዲሁም ቅቤም ተቀላቅሎበት መድኃኒት ለማግኘት ሙከራ ይደረጋል ብሏል።