ለሥራ ቢሮ መሄድ ብሎ ነገር ከናካቴው ሊቀር ይሆን?

ጭር ያለ የከተማ ውስጥ ጎዳና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

እንቅስቃሴዎች ውስን ይሆናሉ

ለብዙዎቻችን ቤታችን ቢሯችን ሆኖ ሰንብቷል፤ በኮሮናቫይረስ ተህዋስ ምክንያት። ይህ ጽሑፍ እየተሰናዳ ያለውም በአንድ ከቤቱ እየሰራ በሚገኝ የቢቢሲ ሠራተኛ ነው።

መኝታን ቢሮ ማድረግ ይቀጥል ይሆን?

እርግጥ ነው ከቤት ሆኖ መሥራት በድኅረ ኮሮናቫይረስ ዘመን ደንብ የሚሆንባቸው መሥሪያ ቤቶች እንደሚኖሩ ከወዲሁ እየተነገረ ነው።

ይህ ሀቅ ከኩባንያ ኩባንያ ቢለያይም ቅሉ፤ ቀጣሪዎች በዚህ አጋጣሚ ሠራተኞቻቸው ከቤት ሲሰሩ ኩባንያቸው ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ እንደሚሆን በትንሹም ቢሆን ተረድተዋል።

በዚህ ሀሳብ ገፍተውበት ቢሮ ድርሽ እንዳትሉ ቢሉንስ?

ይህ የማይመስል የነበረ ነገር በብዙ ኩባንያዎች ዘንድ እየተጤነ ነው።

"ለምን ቢሮ እንከራያለን?"፣ "ለምን በአንድ ቢሮ ሕንጻ ሺህ ሠራተኞች ይርመሰመሳሉ?" ያሉ የሥራ አስፈጻሚዎችና ቀጣሪዎች ቀስ በቀስ ቢሮዎቻችንን ወደ ሠራተኞቻቸው ሳሎን ሊያመጡት ሽር ጉድ ይዘዋል።

ይህ ነገር የከተማን ሕይወት በጠቅላላ ሌላ መልክ ሊያሲዘው ይችላል። ማኅበራዊ ሕይወትና ትዳርም መልኩን ይቀይር ይሆናል።

በዚህ ጉዳይ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን ሦስት ባለሞያዎችን መርጠናል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ጭር ያሉ መሐል

መሀል ከተማዎች ጭር ይሉ ይሆን?

ፖል ቼሽየር (በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር)

ሰዎች ማኅበራዊ እንሰሳ ናቸው። ውጤታማ ለመሆን የግድ ፊት ለፊት ከባለጉዳይ ጋር መገናኘት ያሻቸዋል። ለ20 ዓመታት የተደረገ ጥናት ያንን ነው የሚያስረዳው። አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ የግድ ከሰው ጋር ስንገናኝ የምናደርጋቸው። ከእነዚያ መካከል አንዱ ዕለታዊ ሥራ ነው።

ሌስ ባክ (የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር)

አዲስ ነገር ልንጀምር ጫፍ ላይ ያለን ይመስለኛል። የሰው፣ የቦታና የጊዜ መስተጋብር ሌላ መልክ በመያዝ እየመጡ ይመስለኛል። ከዚህ ወዲያ አንዳንድ ነገሮች በነበሩበት ይቀጥላሉ ለማለት እቸገራለሁ።

ኦዲ ቢኮሌት (የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ)

አንዳንድ ግዙፍ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ እያበረታቱ መሆኑ ግልጽ ነው። ትዊተር ይህን ወስኗል። ፌስቡክም እንዲሁ። የባርክሌይ ባንክ ሥራ አስፈጻሚም "7 ሺህ ሠራተኛ ቢሮ ጠርቶ ማርመስመስ ከዚህ በኋላ ያረጀ ያፈጀ ጉዳይ" እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ቢሮ ሄዶ የመስራቱ ነገር ጨርሶውኑ ይጠፋል ባይባልም የቢሮ መሄድ ልማድ እየከሰመ ሲሄድ አነስተኛ፣ መካከለኛና ዋነኛ የከተማ አካባቢዎች እንደየደረጃው መልካቸው መለወጡ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ሌስ ባክ (የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር)

አንዳንድ ኩባንያዎች "ለምንድነው ሚሊዮን ዶላር ለቢሮ የምንከሰክሰው" ማለታቸው አይቀርም።፡ ከወዲሁ እንደዚያ ማሰብ የጀመሩ አሉ። ይሄ ማለት በትንሹ ሦስት ነገሮችን ጨርሶውኑ ይቀይራል።

አንዱ የከተሞችን ማዕከላት፣ ሁለተኛው የልጅ አስተዳደግ፣ ሦስተኛው ደግሞ የትዳር ግንኙነት ናቸው። ይህ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።

ኦዲ ቢኮሌት (የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ)

እኔ እንደሚመስለኝ በየሰፈራችን፣ ወደ ቢሮ ርቀን ሳንሄድ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛዎች እና ሌሎች የምንፈልጋቸው ነገሮች ወደኛ እየቀረቡ ይሄዱ ይሆናል። ሰዎች በአቅራቢያቸው መገናኘት መጀመር ይፈልጉ ይሆናል። ሌላው ደግሞ ከቤታችሁ ስሩ ስንባል ቦታ ስንሻ በዚያው በሰፈራችን የተሸለ ስፍራ መፈለጋችን አይቀርም።

ይህ ሀቅ ሰፈሮች እንዲያብቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ቢሮዎች በስፋት በሚገኙባቸው የከተማ ማዕከላትም ለውጦች መኖራቸው አይቀርም። እነዚያ ሰፋፊ የቢሮ ሕንጻዎች ቆመው አይቀሩም መቼስ። የዲዛይን ለውጥ እየተደረገባቸው ወደ መኖርያ አፓርትመን ይቀየሩ ይሆናል።

ፖል ቼሽየር (በለንደን ስኩል ኦፍ የኢኮኖሚክስ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር)

ከቤት ሥሩ ከተባልን ሁሉም የቤተሰብ አባል ቤት መዋሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቤታችን ውስጥ ሰፋፊ ቦታ መሻትን ያስከትላል። ካልሆነም በአቅራቢያችን የተመቻቸ ቦታ እንፈልግ ይሆናል።

ለስብሰባ በሳምንት አንድ ሁለት ጊዜ ወደ ዋና ጽሕፈት ቤት መሄድ ሊኖር ይችላል። በሳምንት አንድ ጊዜ መሄድ ብቻ ግዴታ ሲሆን ደግሞ ሰዎች ከዋና ከተማ አቅራቢያ መስፈራቸው ጥቅሙ እየቀነሰ ይመጣል። ሰዎች ከከተማ ማዕከል ወደ ገጠር እየሄዱ መስፈር ይጀምሩ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

በርሚንግሃም ውስጥ የሚገኝ ጭር ያለ የባቡር ጣቢያ

ትራንስፖርትና የሰዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ ምን ይፈጠራል?

ማርገሬት ቤል በኒውካስል ዩኒቨርስቲ የትራንስፖርትና ኢንቫይሮንመንት ፕሮፌሰር

ሰዎች መኪና መግዛት ይጀምራሉ። ይህም የሚሆነው ሰፋፊ ቦታ ፍለጋ ወደ ገጠር ስለሚያቀኑ ነው። በራቁ ቁጥር መኪና የግድ ይላቸዋል። ይህ ደግሞ የካርቦን ልቀትን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። ማድረግ የሚኖርብን ሰዎች ምንም ይሁን ምን ከሥራ ቦታቸው አቅራቢያ እንዲሰፈሩ ማድረግና ብስክሌት እንዲነዱ ማበረታት ነው።

ፖል ቼሽየር (በለንደን ስኩል የኢኮኖሚክስ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር)

ብዙ ሰዎች ቤት ሲቀመጡ ቤት ማብሰል ግድ እየሆነ ይመጣል። ይህ የኢነርጂ [ኃይል] አጠቃቀማችን ላይ ለውጥ ያመጣል። ከቤት ባለመውጣት ከምናድነው ኢነርጂ የበለጠ ቤት ውስጥ እንጠቀማለን። ጥናቶች ይህንን ነው የሚመሰክሩት።

በከተሞቻችን ዙርያ ስለሚኖር ለውጥ

ሌስ ባክ (የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር)

ብዙ ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ ስናወራ ከፍ ያለ የቢሮ ሥራ ስለሚሰሩ ሰዎች እያሰብን ነው፤ ለምሳሌ በፋይናንስ፣ በአይቲ ወዘተ። ከተሞች የተሞሉት ግን በእነዚህ ሠራተኞች አይደለም። ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና አገልግሎች ሰጪ ተቋማት ይቀጥላሉ።

ደግሞም ከተሞች የመገናኛ ማዕከል መሆናችውን አንርሳ። አገልግሎት ብቻ አይደለም የምንፈልገው። ሰዎች ሌሎችን ማግኘት መተዋወቅ ወዳጅነት መመስረት ይፈልጋሉ። ይህ እነሱን ከማይመስሉ ሰዎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ይጨምራል። በባህል እኛን የማይመስሉ ሰዎችን በሰፈራችን ስለማናገኛቸው ርቀን ወደ ከተማ ማዕከላት መሄዳችን አይርም።

ፖል ቼሽየር (በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር)

ሌላው ጉዳይ መጠየቅ ያለብን ሰዎች ወደ ከተማ ወጥተው ለመቀላቀል ከዚህ በኋላ የኮሮናቫይረስ ፍርሃታቸው ብን ብሎ ይጠፋል ወይ? ሰዎች ወደ ድሮ ባህሪያቸው ለመመለስ ቢያንስ በሽታው በቁጥጥር ሥር ስለመዋሉን እርግጠኞች መሆን ይፈልጋሉ። ቢያንስ ክትባት ሊገኝ ይገባል።

ይህ እስኪሆን ደግሞ ረዥም ጊዜ መፈለጉ አይርም። ረዥም ጊዜ!