ጊኒ ቢሳው፡ የገዛ ጄኔራሎቿ አደገኛ እጽ የሚነግዱባት አገር

በጊኒ ቢሳዎ ባንዲራ ቀለም የተሰራ እጽ መያዣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ጥር ወር በአንድ ጀምበር በተደረገ አሰሳ የተገኘው ነገር አስደንጋጭ ነበር።

ሃያ መርሴዲስ ቤንዝ ቅንጡ መኪኖች፣ በባንክ የተደበቀ 3 ሚሊዮን ዶላር፣ 90 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ውስኪና ወይን።

ነገር ግን ከሁሉ የሚያስደነግጠው ይህ አይደለም። 1 ነጥብ 8 ቶን የሚመዝን ኮኬንይን መገኘቱ ነው አነጋጋሪ የሆነው። ይህ ፍርድ ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ ነው።

በጊኒ ቢሳው በኩል ወደ አሜሪካና አውሮፓ የሚሾልከው የአደገኛ እጽ መጠን አስደንጋጭ እየሆነ መጥቷል። ማቆሙም ፈተና ሆኗል።

ባለፈው ወር በተደረገው ልዩ ዘመቻ የተያዙት 12 አደገኛ የእጽ አስተላላፊዎች የጊኒ ዜጎች ብቻ አልነበሩም።

ፖርቹጋሎች፣ የሜክሲኮና ኮሎምቢያ ሰዎችም ነበሩበት። ይህ በዚያች አገር ያለው የእጽ ዝውውር ምን ያህል ዓለም አቀፋዊ ትስስር እንዳለው አመልካች ሆኗል።

ከተከሳሾቹ መካከል ሁለቱ በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል። ጊኒ ቢሳው በወንጀለኞቹ ላይ የወሰደችው እርምጃ ተደንቆላታል። ሆኖም የዚያች አገር እንጀራ፣ የዚያች ትንሽ አገር ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ኮኬንይን እንዳይሆን ስጋት አለ።

'ጄኔራሎቹ ኮኬይን ይነግዳሉ'

አንቶኒ ማዛቶሊ በጊኒ ቢሳዎ የተባበሩት መነግሥታት ድርጅት የአገሪቱን የጸረ አደገኛ እጽ ዘመቻ ይመራሉ።

"ይህ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአደገኛ እጽ መረብን የመበጣጠስ እርምጃ እንደ መጀመሪያ ስኬት ቀላል ግምት የምንሰጠው አይሆንም። ስምንት ዓመት የፈጀ ጉዳይ ነው። ጊኒ ቢሳውን በቀጣይነት ከአደገኛ እጽ የማስተላለፊያ ወደብነት ነጻ ለማድረግ አንድ እርምጃ ነው" ብለዋል።

ጊኒ ቢሳው ለማስተላለፊያነት የተመቸ መለክአ ምድራዊ አቀማመጥ ነው ያላት። ከብራዚል፣ ከኮሎምቢያ፣ ከቬንዝዌላ፣ ከኢኳዶርና ከፔሩ ወደ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን መጠኑ ከፍ ያለ ኮኬይን ለማሸጋገር እንደ ጊኒ የሚመች አገር የለም።

ይህቺ የቀድሞው የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ጊኒ ቢሳው በአሜሪካና በተባበሩት መንግሥታትም ጭምር የአደገኛ እጽ ወደብ በሚል ተሰይማ ነበር።

"ናርኮስቴት" ይሏታል። መዋቅሩ ሁሉ በአደገኛ እጽ ሰንሰለት የተተበተበ አገር እንደማለት ነው።

በአፍሪካ እንዲህ ዓይነት ስም የተሰጣት ብቸኛዋ አገር ጊኒ ቢሳው ናት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የጊኒ ቢሳዎ ደሴቶች የእጽ ማስተላለፊያ አመቺ ቦታዎች ናቸው ይባላል

ይህ ስም የዛሬ 10 ዓመት ነበር ለጊኒ ከአሜሪካና ከተባበሩት መንግሥታት ጭምር የተሰጣት። አሁን ግን ነገሮችን ለመቆጣጠርና ስሟን ለማደስ የተጀመሩ ሙከራዎች አሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚያች አገር ባለፈው የካቲት በተደረገ አጨቃጫቂ ምርጫ ኡማሩ ሲሶኮ አሸንፈዋል። የእርሳቸው ወደ ሥልጣን መምጣት አደገኛ እጽ ዝውውር ላይ የተከፈተውን ጦርነት ቀዝቃዛ ውሃ እንዳይቸልስበት ተፈርቷል።

ፍርሃቱ ያለ ምክንያት አልመጣም።

ምንም እንኳ አዲሱ ፕሬዝዳንት በአደገኛ እጽ የዝውውር ሰንሰለት እጃቸው እንዳለበት የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም ዋና ዋና የጦር ጄኔራሎች ለእርሳቸው ድጋፍ መስጠታቸው ምናልባት በእጽ ዝውውር የሚታሙት እነዚያው የጦር መሪዎች ንግዱን በአዲስ መልክ እንዳያጧጡፉት ተሰግቷል።

በተለይ ባለፈው በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ይዘው የነበሩት ኢታማዡር ሹሙ አንቶኒዮ ኢንጃይ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ድጋፍ መስጠታቸው አዲስ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

ኢታማዡር ሹሙ የእጽ ዝውውሩ ላይ እስከ አንገታቸው ተዘፍቀዋል ተብለው ይታማሉ።

ጄኔራል ኢንጃይ ግን ክሱን ያስተባብላሉ።

ጊኒና ኮኬይን

ጊኒ ቢሳዎ ከፖርቱጋል የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጸ የወጣቸው በ1970ዎቹ መጀመርያ ነበር። ከዚያ በኋላ 9 መፈንቅለ መንግሥት አስተናግዳለች።

ይህም በመሆኑ የዚያች አገር ተቋማት ልፍስፍስ ሆነው ቆይተዋል።

የተቋማቱ መልፈስፈስ ደግሞ የእጽ ዝውውሩ እንዲሳለጥ የተመቻቸ ሁኔታን ፈጥሯል።

ጊኒ ቢሳዎ የምዕራብ አፍሪካ አገር ናት። የሕዝብ ብዛቷ አንድ ሚሊዮን ተኩል ሲሆን ፖርቹጊዝ እና ክሪዮሎ የሚባል ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው።

አደገኛ እጽ ሲራራ ነጋዴዎች ጊኒን በጣም ይወዷታል፤ ከደቡብ አሜሪካ ተጭኖ ወደ አውሮፓ ለማድረስ ምቹ ወደብ ሆና ትታያቸዋለችና።

ከሕዝቧ 70 ከመቶ የሚሆነው የቀን ገቢው ከ2 ዶላር ያነሰ ነው።

"በዚያች አገር ተቋማት ባለመገንባታቸው እጽ አስተላላፊዎች ማንኛውንም ባለሥልጣን በሙስና እንዲያባብሉ አግዟቸዋል" ይላሉ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢው ጸረ እጽ ግብረ ኃይል መሪ ማዜቴሊ።

"በዚህ ሂደት ጥቂት ጄኔራሎች ይበለጽጋሉ። የሚደማው ግን ሰፊው የአገሬው ሕዝብ ነው።"

የቀድሞው የባሕር ኃይል አዛዥ ቡቦ ና ቹቶ በአስተላላፊነት ከተጠረጠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው።

ሰውየው በርካታ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ተሳክቶላቸው ግን አያውቅም። አሜሪካ እኚህን ጄኔራል "የእጽ ጌታ" የሚል ቅጽል ሰጥታቸዋለች።

2013 ላይ በወታደሮቻቸው እገዛ በልዩ ጥበብ ነበር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የተደረጉት።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የቀድሞው ኢታማዡር ሹሙ ጄኔራል ኢንጃይን 'የኮኬይን መፈንቅለ መንግሥት' በሚባለው ስልጣን ላይ ወጥተው ነበር

ጄኔራሉ ወደ አሜሪካ ለሚዘዋወር እጽ ድጋፍ በመስጠት ክስ ተመስርቶባቸው 4 ዓመት እስር ተበይኖባቸዋል። ለመርማሪዎች ተባባሪ ስለነበሩና መልካም ባህሪን ስላሳዩ በሚል የእስር ዘመናቸው አጭር እንዲሆን ተደርጓል። አሁን ወደ ኑሯቸው ተመልሰው ድምጽ አጥፍተው እዚያው ጊኒ ውስጥ ናቸው።

ሰውየው የተያዙበት መንገድ ፊልም የሚመስል ነበር።

በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተፈለገው ኢታማዡር ሹሙ ጄኔራል ኢንጃይን ነበር።

ለኚሁ ኢታማዦር ሹም የእጽ ነጋዴዎች ሊያነጋግሯቸው እንደሚፈልጉና ወደ ወደብ በአስቸኳይ እንዲመጡ መልዕክት ይደረግላቸዋል።

ኢታማዦር ሹሙ ነገሩ ጥርጣሬ ይፈጥርባቸውና የባሕር ኃይል አዛዡን ይልኳቸዋል። እኚህ አዛዥ ወደ ድንበር ሄደው የተባሉትን የእጽ ነጋዴዎች ሲጠብቁ የአሜሪካ ሰላዮች ያጠመዱላቸው ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ። በቁጥጥር ሥር የዋሉትም ያን ጊዜ ነበር።

የጊኒ 'እስር ቤቶች'

ጊኒ ቢሳው 10 እስር ቤቶች አሏት። ነገር ግን እስር ቤቶቿ እጅግ የተጎሳቆሉ ናቸው። ፖሊሶችም አንድ እስረኛ ሊያመልጥ ቢል ለማስቆም የሚያስችል የጥበቃ መሳሪያ እንኳ በበቂ ሁኔታ የሌላቸው ናቸው።

ይህን ያሉት የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስትር ሩት ሞንቴሪዮ ናቸው።

ለምሳሌ መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ወንጀል የተጠርጣሪዎቹ ክስ ሊታይ የነበረው በጊኒ ቢሳዎ ዋና ከተማ ቢሳዎ አልነረበረም። በዚያው በተያዙበት ከተማ ቢሶሮ ውስጥ ነበር። ነገር ግን በቢሶሮ ከተማ ተጠርጣሪን ወደ እስር ቤት የሚወስድ መኪና እንኳ ባለመኖሩ ወደ ዋና ከተማው እንዲመጡ ተደረገዋል።

"እስር ቤት የለንም፤ እስረኛ ማጓጓዠ የለንም፣ ተቋማት የሉንም፣ እስረኛ ላምልጥ ቢል እንኳ ማስቆም አንችልም። ይህ ሁሉ ተደማምሮ እኛ ለአደገኛ እጽ ማስተላለፊያነት የተመቸን አድርጎናል" ይላሉ የቀድሞው የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስትር ሩት ሞንቴሪዮ።

ከዚህም በተጨማሪ በዚያች አገር ከአደገኛ እጽ ዝውውር የሚገኘው ገንዘብ የአልቃይዳ ርዝራዦችን መደጎሚያነት እየዋለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, @UNODC_WCAfrica

የምስሉ መግለጫ,

መስከረም ላይ ከዋና ከተማዋ አቅራቢያ የተያዘው ኮኬይን

ለምሳሌ ባለፈው ወር የተየዘ 900 ኪሎ ግራም የሚመዝን የጭነት መኪና የጫነው ዓሳ እንደሆነ ነበር የሚታወቀው። ሆኖም ውስጡ ኮኬይን ተሞልቶ ነበር። የጭነት መኪናው ሊያመራ የነበረው ሰሜን መግረብ በረሃ ለሚነስቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖች ነበር።

በጊኒ የአደገኛ እጽ ገንዘብ የምርጫ ቅስቀሳ ይደረግበታል።

ለምሳሌ ብራይማ ሳይድ ባ አደገኛ እጽ አዘዋዋሪ ነው። እስከዛሬም አልተያዘውም። ሁለት ዜግነት አለው። ፖርቱጋላዊና ጊኒያዊ ነው። በጋምቢያ በጊኒና በማሊ እንደሚዘዋወር ይገመታል። ይህ የሚያሳየው ንግዱ የአካባቢውን አገራት እንደሚያዳርስ ነው።

ሌላው ተጠርጣሪ ሪካርዶ ነው። ሪካርዶ የኮሎምቢያም የሜክሲኮም ዜግነት አለው። አልተያዘም። ምናልባት በደቡብ አሜሪካ እንደሚዘዋወር ይገመታል።

ተጠርጣሪዎቹ ፖለቲካዉን ጭምር ይዘውሩታል። ከእጽ ዝውውር የሚገኘው ገንዘብ መልሶ ለምርጫ ቅስቀሳ ይውላል። ለፓርላማ ምርጫ የየድርሻቸውን ይቀራመቱታል። በዚያው ሌላ በእጽ የናወዘ፣ በእጽ የሚዘወር ሥርዓት ይመሰረታል። ጊኒን "ናርኮስቴት" ያሰኛትም ሌላ ሳይሆን ይኸው ነው"