የ75 አመቱን ግለሰብ ገፍትረው የጣሉት ፖሊሶች ክስ ተመሰረተባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ የ75 አመት የእድሜ ባለፀጋን ገፍተው መሬት ላይ የጣሉ ሁለት ፖሊሶች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ግለሰቡ ቦታው ላይ የተገኙት የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ለመቃወም ነበር ተብሏል።
የዕድሜ ባለፀጋውን መሬት ላይ በጣሉት ወቅትም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውንም ከተቀረፀው ቪዲዮ መረዳት ይቻላል።
የ39 አመቱ አሮን ቶርጋልስኪና የ32 አመቱ ሮበርት ማካቤ ወንጀሉን አልፈፀምንም ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ለጊዜው ያለ ዋስ ቢለቀቁም ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሰባት አመት እስር ይጠብቃቸዋል።
በዚህ ሳምንት ሐሙስ እለት ማርቲን ጉጊኖ የተባሉትን ግለሰብ በገፈተሯቸው ወቅት ግለሰቡ ወደኋላ በጀርባቸው አስፓልቱ ላይ ወድቀዋል። ወዲያውም ነው ከጭንቅላታቸው ደም መፍሰስ የጀመረው።
በአሁኑ ሰዓት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በጥሩ ጤንነትም ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በነጭ ፖሊስ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ተከትሎ የተቀጣጠለውን የፀረ ዘረኝነት ተቃውሞም ለማብረድ ግዛቶች የሰዓት እላፊ አዋጅን አሳልፈዋል።
በኒውዮርክም የሰዓት እላፊ አዋጅ የተጣለ ሲሆን ይህንንም ለማስከበር ፖሊሶቹ በቦታው ነበሩ ተብሏል።
የአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚሰጠው ቡድን አባላት የሆኑት ሁለቱ ፖሊሶች የዕድሜ ባለፀጋውን የገፈተሩበት ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ያለ ደመወዝ ከስራቸው እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፏል።
የነሱ ከስራ መታገድንም ተከትሎ የቡድኑ አምሳ ሰባት አባላትም ከስራቸው ለቀዋል።
በትናንትናው ዕለትም 100 የሚሆኑ ደጋፊዎች፣ ፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ክሱን በመቃወም በቡፋሎ ፍርድ ቤት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።