ብራዚል የኮቪድ-19 መረጃዎቿን ከድረ ገጿ ለምን አጠፋች?

በሳኦፖሎ እየተደረገ ያለ ቀብር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ብራዚል ኮቪድ-19ን በተመለከተ ለወራት የተመዘገቡ መረጃዎችን ከመንግሥት ድረ ገጽ ማጥፋቷን ተከትሎ ፕሬዚደንት ጄር ቦልሶናሮ ወረርሽኙን እየተቆጣጠሩበት ባለው መንገድ እየተተቹ ነው፡፡

የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር በ24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙና የሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንደሚያሳውቅ በመግለጽ፤ ከዚህ በኋላ ግን አብዛኞቹ አገራት እንደሚያደርጉት አጠቃላይ ድምር ቁጥር እንደማይናገር ገልጿል፡፡

ፕሬዚደንት ቦልሶናሮ በበኩላቸው አጠቃላይ ቁጥር አሁን ያለውን ሁኔታ አያሳይም ብለዋል፡፡

ብራዚል በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በቅርቡም ከሌሎች አገራት በበለጠ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በላቲን አሜሪካዋ ብራዚል እስካሁን ከ640 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ሰፊ ምርመራ ቢደረግ ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ይነገራል፡፡

ከ35ሺህ በላይ ሰዎችም በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህም ብራዚልን በሟቾች ቁጥር ከዓለም አገራት በሦስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በዓለም ጤና ድርጅት የሚመከረውን አስገዳጅ የቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ ባለመደገፋቸው ትችት ቀርቦባቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚለውን መርህ በመጣስ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተደጋጋሚ ተሳትፈዋል፡፡

የብራዚል ባለሥልጣናት ምን አሉ?

ቅዳሜ እለት የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ-19ን የተመለከቱና በመንግሥትና በማዘጋጃ እስካሁን ሲመዘገቡ የነበሩ መረጃዎችን ከድረ ገጹ ላይ አጥፍቷል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት 24 ሰዓታት 27ሺህ 075 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውንና 904 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ 10 ሺህ 209 ታማሚዎች ደግሞ ማገገማቸውን ገልጿል፡፡

ፕሬዚደንት ቦልሶናሮ በትዊተር ገጻቸው ላይ "አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙና የሞቱ ሰዎችን አሃዝ መግለጽ የወቅቱን ሁኔታ አያመለክትም" ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ መረጃዎቹ ከድረ ገጽ ላይ ለምን እንደጠፉ አላብራሩም፡፡

በአገሪቷ ያለውን የሪፖርት አቀራረብ ለማሻሻልም ተጨማሪ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል፡ ነገር ግን የመረጃ ማጥፋት ውሳኔው በጋዜጠኞችና በኮንግረስ አባላት በስፋት እየተተቸ ነው፡፡

በጤና ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ያለው መረጃ የጠፋውም በአገሪቷ ለአራት ተከታታይ ቀናት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ከተመዘገበ በኋላ ነው ተብሏል፡፡