ኮሮናቫይረስን በተመለከተ አፍሪካን የሞሉት የተሳሳቱ መረጃዎች

በማዳጋስካር የሚገኙ ተማሪዎች የኮቪደ-19 መድሃኒት የተባለውን ሲጠጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ በተለያዩ አፍሪካ ሃገራት እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ድረገፆችም ላይ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲሁ በርክተዋል።

በቅርቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተጋሩ ካሉት የተሳሳቱ መረጃዎች በጥቂቱ

1. አፍሪካ የራሷን የኮሮናቫይረስ መድኃኒት እንዳታገኝ የተወጠነው ሴራ

የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆይሊና አሪቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዕፅዋት የተቀመሙ የኮሮናቫይረስ ፈውስ አግኝቻለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ሴራ የተሞሉ መላ ምቶች እየተንከባለሉ ይገኛሉ።

ከነዚህም ውስጥ አንዱ የአለም የጤና ድርጅት ለማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ ገንዘብ በጉቦነት ሊሰጣቸው ማቅረቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ እየተጋራ ነው። ፕሬዚዳንቱ ይህ ጉቦ የሚሰጣቸው ያመረቱትን መድኃኒት ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ እንደሚመርዙ የሚስማሙ ከሆነ ነው።

ይሄ መሰረት የሌለው ፅንሰ ሃሳብንም እያንሸራሸሩ ያሉት ሰዎች እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት አፍሪካውያን ራሳቸውን ችለው ለኮሮናቫይረስ ፈውስ ማግኘት እንደማይችሉና መቼም ቢሆን በራሳቸው መቆም የማይችሉ መሆናቸውን የአለም ጤና ድርጅት ማሳየት ይፈልጋል እያሉ ነው።

በመጀመሪያ ይሄ ፅሁፍ የወጣው ሚያዝያ አካባቢ መቀመጫውን አንጎላና ኮንጎ ባደረገ የፌስቡክ ገፅ ላይ ሲሆን በፈረንሳይኛ ቋንቋም ነበር። በመቀጠልም በግንቦት ወር ላይ ሁለት የታንዛንያ ጋዜጦች ይህንኑ መረጃ ይዘውት ወጡ።

በአንደኛው ጋዜጣ ላይ በቀረበው ዘገባም የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ከፍራንስ 24 ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ገንዘብ እንስጥዎት ጥያቄ ቀርቦልኛል ማለታቸውን አካቷል።

ይሄ ሪፖርትም በአፍሪካ በሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታም ተጋርቷል። የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት በፍራንስ 24 ቀርበው ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸው እውነት ቢሆንም ከድርጅቱ የጉቦ ጥያቄ ቀርቦልኛል አላሉም።

የአለም ጤና ድርጅትም በበኩሉ ለቢቢሲ እንደገለፀው ይሄ ታሪክ ሃሰተኛ መሆኑን ነው። የማዳጋስካር መንግሥትም ውንጀላውን አጣጥሎታል።

"የኮቪድ- 19 ፈውስ መገኘቱን ተከትሎ ከፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆይሊና ጋር የተያያዙ ሃሰተኛ መረጃዎች ይነዛሉ" በማለት የመንግሥት ቃለ አቀባይ ሎቫ ራኖራሞሮ ተናግረዋል።

ከዕፅዋት የተቀመመው መድኃኒት አሁንም በማዳጋስካር መመረቱ የቀጠለ ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሃገራትም መድሃኒቱን ወደሃገራቸው አስገብተዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ቫይረሱን ስለመፈወሱ የተረጋገጠ መረጃ የለም።

የአለም ጤና ድርጅት ሃገር በቀል የሆኑ መድሃኒቶች ላይ ያሉ ምርምሮች መበረታታት እንደሚገባቸው ጠቅሶ ነገር ግን ያልተፈተሹ መድሃኒቶችን መጠቀም ላይ ያለውን ጉዳት በማስመልከት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

2•የታንዛንያ ጤና ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ አልተያዙም

አንድ የታንዛንያ ድረ ገፅ የሃገሪቱ ጤና ሚኒስትር ኡሙ ምዋሊሙ ባደረጉት ምርመራ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጠቅሶ አንድ ዘገባ አወጣ። ይህም ዘገባ በሃገሪቱ አሉ በሚባሉ ጋዜጠኞችም ዘንድ በትዊተር ገፃቸው አጋሩት።

ነገር ግን ይህ መረጃ እውነት አይደለም።

ዘገባው እንደ ምንጭ የተጠቀመበት ሚኒስትሩ አጋርተዋል የተባለውን ትዊት በፎቶ አንስቶ እንደሆነ አሳውቋል።

በስዋሂሊ ቋንቋ ተጋርቷል በተባለው መረጃም " ያለመታደል ሆነ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶብኛል። ነገር ግን ራቅ ብዬም ቢሆን ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ሃገሬን ለማገልገል ወስኛለሁ" የሚል ነው።

ነገር ግን ይህ ፅሁፍ በሚኒስትሩ የትዊተር ገፅ ላይ አልተገኘም። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ሚኒስትሩ ሃሰተኛ መረጃ ነው ብለዋል።

3•በደቡብ ሱዳን ቫይረሱን መከላከል የሚችል የደረት አርማ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የኮሮናቫይረስ መከላከል የሚያስችል የደረት አርማ ማድረጋቸው ቢገለፅም አይሰራም ተብሏል።

በፕሬዚዳንቱ ፕሬስ መረጃ ማዕከል ወጣ የተባለ ፎቶ እንደሚያሳየው ፕሬዚዳንቱም እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናት በተለያዩ ድረገፆች ላይ መሸመት የሚችሉ "ኤይር ዶክተር"ና "ቫይረስ ሸት አውት" የሚሉ አርማዎችን አድርገው ታይተዋል።

እነዚህ አርማዎች ቫይረስ እንዲሁም ባክቴሪያዎችን ስለመከላከላቸው ምንም አይነት መረጃ የለም። ቢቢሲ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ቃለ አቀባይን ስለ ጉዳዩ በጠየቃቸው ወቅት በጃፓን መንግሥት ስም አንድ ግለሰብ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

በአለም ጤና ድርጅትም እውቅና ባለማግኘታቸው አርማዎቹን ደረታቸው ላይ ማድረግም ማቆማቸውን ተናግረዋል። በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የጃፓን ኤምባሲ በበኩሉ ከነዚህ አርማዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አሳውቋል።

ተመሳሳይ የደረት ላይ አርማዎች በተለያዩ ሃገራት እየተሸጡ ሲሆን የሩሲያ ፓርላማ አባላትም ከሰሞኑ አድርገዋቸው ታይተዋል።

ከነዚህ የደረት አርማዎች ከሚወጡት ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ ክሎሪንዳይኦክሳይድ ሲሆን የአሜሪካው የመድሃኒት ቁጥጥርም ለሰው ልጅ ጉዳት ከሚያስከትሉ መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቅሷል።

4.የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ማጉፊሊ የፊት ጭምብል ማድረግን አልከለከሉም

የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በህዝባዊ ቦታዎች ላይ የፊት ጭምብል ማድረግን ከልክለዋል የሚሉ አሳሳች መረጃዎች ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥተዋል።

በነዚህ ሃሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያዎች ፅሁፎች መሰረት ፕሬዚዳንቱ ህዝባዊ በሆኑ ቦታዎች ላይ የፊት ጭምብልን ማድረግ ፍራቻን እንደሚነዛና ሃገሪቷን መጎብኘት ለሚፈልጉ የውጭ ቱሪስቶችም የተሳሳተ መልዕክት ያስከትላል በማለት እንዳታደርጉ ብለዋል።

በሳቸው ተፃፈ የተባለም የትዊተር ፅሁፍ መረጃ ቢሰራጭም ሃሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ በተጨማሪም ከሳቸው ቢሮ ወጣ የተባለ መግለጫም ሲዟዟር የነበረ ሲሆን ይህም ትክክለኛ እንዳልሆነ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይም እንዲህ አይነት ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን ችላ እንዲሉ ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል። የታንዛንያ መንግሥት ዜጎቹ የፊት ጭምብል እንዲያደርጉና አካላዊ ርቀታቸውንም እንዲጠብቁ ያበረታታል።

ነገር ግን የታንዛንያ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ያደርጉ የነበረውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ዕለታዊ መረጃዎች ከመስጠት የታቀቡ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ወረርሽኙን ቀለል በማድረግም እየተተቹ ነው።