በአሜሪካ ፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞዎች የቀጠሉ ሲሆን ታላቅ የተባለውም ሰልፍ ተካሄደ

በአሜሪካ እየተደረጉ ያሉ የተቃውሞ ሰልፎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ለዘጠኝ ደቂቃ ተጭኖት ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ በበርካታ ግዛቶች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞ 12ኛ ቀኑን ይዟል፡

ዘረኝነትንና የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም እየተደረገ ያለው ህዝባዊ አመፅ ቀጥሎም በመላው አሜሪካም ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ ትልቅ በተባለው ተቃውሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ በመውጣት ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን ፖሊስ ተቃዋሚዎች ወደ ዋይት ሃውስ እንዳይቀርቡ ከልክሏል፡፡

በኒውዮርክ፣ ችካጎ ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሳን ፍራንሲስኮም በርካታ ሰዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጆርጅ ፍሎይድ በተወለደባት ሰሜን ካሮሊና ግዛት ከመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ በፊት ሰዎች ለፍሎይድ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም ምንም እንኳን መንግሥት በወረርሽኙ ሳቢያ ሰዎች እንዳይሰባሰቡ ቢያሳስብም የለንደን ፓርላማ አደባባይ በሰዎች ተሞልቶ ነበር፡፡

በአውስትራሊያ በሲድኒ፣ ሜል ቦርን እና ብሪስቤን የአውስትራሊያ ቀደምት ህዝቦች (አቦርጂኖች) አያያዝ ላይ ትኩረት ያደረጉ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ስፔንም የተቃውሞ ሰልፎች ነበሩ፡፡

መሳሪያ ያልታጠቀው ፍሎይድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በአሰቃቂ ሁኔታ በሚኒያፖሊስ ከተማ የተገደለው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር፡፡

አሟሟቱን የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልም አንድ ነጭ ፖሊስ ለዘጠኝ ደቂቃዎች የፍሎይድን አንገት በጉልበቱ ተጭኖ ፍሎይድም መተንፈስ እንዳልቻለ እየተናገረ ሕይወቱ ሲያልፍ ያሳያል፡፡

የጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ በጉልበቱ ቆሞ የነበረው ዴሪክ ቾቪን የተባለ ነጭ ፖሊስ በዚህ ድርጊቱ ከሥራ የተባረረ ሲሆን ክስም ተመስርቶበታል፡፡

ድርጊቱ ሲፈጸም በሥፍራው የነበሩ ሦስት ፖሊሶችም በተመሳሳይ ከሥራ የተባረሩ ሲሆን በግድያው ተባብረዋል በሚል ተከሰዋል፡፡