በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎች ቁጥር 97 ደረሰ

የጤና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ባለባት ኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው የጤና ተቋም ሰራተኞች ቁጥር 97 ደርሷል።

አብዛኛዎቹም በባለፉት ሁለት ሳምንታት የተያዙ መሆኑንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ ባደረጉት ውይይት ገልፀዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመጋቢት ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ ጭማሬ ያሳየው በባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለይም በባለፉት አምስት ቀናት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ ቫይረሱ የሚገኝባቸው የጤና ሰራተኞችም ቁጥር አሻቅቧል።

በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት 97 የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭዎች መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከነዚህም መካከል 91 በአዲስ አበባ የተለያዩ የጤና ተቋማት ላይ የተያዙ መሆናቸውም ተገልጿል።

አብዛኛዎቹ 86 በመቶ የኮሮናቫይረስ ምልክት ያልታየባቸው ሲሆን በተደረገላቸው ምርመራም የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ መካከለኛ ምልክት ታይቶባቸዋል።

በባለፈው አንድ ወር ውስጥ በጤና ማዕከላት ከኮቪድ-19ም ሆነ ከሌላ ህክምና ጋር በተያያዘ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የጤና ባለሙያዎቹ ተጋላጭነትም መጨመሩንም ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

ከህሙማን ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር 2340 ደርሷል፤ ከነዚህም መካከል 1721 የሚሆኑት ለቫይረሱ የተጋለጡት በመጋቢት ወር ነው ተብሏል።

ለቫይረሱ የተጋለጡት የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን አግልለው የነበሩ እንዲሁም በተለያዩ ማዕከላት ውስጥም በለይቶ ማቆያ ገብተው ክትትል ተደርጎላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health

የጤና ተቋማት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አስፍቶ የመርመር ስራ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደቀጠለ የተናገሩት ሚኒስትሯ በአሁኑ ሰዓትም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተለያዩ መመሪያዎችም እየወጡ ይገኛሉ።

በኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ እየተሰራ ያለውን ስራና ዝግጁነት አስመልክቶ ሚኒስትሯ በሰጡት ምላሽም ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ ውስጥ እንዳይሰራጭ ስራ ይሰራ እንደነበር ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ግን በአንዳንድ አካባቢዎች በማህበረሰቡ በመዛመቱ ሌሎች ዘዴዎች ተቀይሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሃገሪቷ ትኩረት ሰጥታ የምትሰራበት ብለው ሚኒስትሯ የጠቀሷቸው ከፍተኛ የወረርሽኝን ስርጭት መከላከል፣ በኮሮናቫይረስ ለታመሙት የህክምና እርዳታን በማድረግ የሟች ቁጥርን መቀነስ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን መከላከል ይገኙባቸዋል።

በዛሬው እለት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2ሺህ በተሻገረባት ኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እየጨመረ በሚመጣበት ወቅት በለይቶ ማቆያ ብቻ ሳይሆን በቤትም ውስጥ ህክምና መጀመሩ አስገዳጅ እንደሚሆን አመላክተዋል።

በተለይም ምልክቱ የማይታይባቸውና መካከለኛ ምልክት የሚታይባቸው ህሙማን የቤት ውስጥ ህክምና እንደሚጀመር ጠቁመው ነገር ግን እሱን ማድረግ የማይችሉትን ቦታ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ለለይቶ ማቆያ እንዲሁም ለህክምና የሚውሉ ማዕከላትን እየተዘጋጁም እንደሚገኙ ገልፀዋል።