ደቡብ ኮሪያ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ስልኬን አታነሳም›› ስትል ከሰሰች

ሰሜን ኮሪያዊያን ተማሪዎች ወደ ደቡብ የከዱ ዜጎቻቸውን ያወገዙበት ትናንት የተካሄደ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ሰሜን ኮሪያዊያን ተማሪዎች ወደ ደቡብ የከዱ ዜጎቻቸውን ያወገዙበት ትናንት የተካሄደ ሰልፍ

ሰሜን ኮሪያ ቅር ተሰኝታለች። ከጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ጋር የተጀመሩ ግንኙነቶችን በሙሉ አቆማለሁ ብላ ስትዝት ነበር፤ ይህንንም አድርገዋለች።

ደቡብ ኮሪያ እውነትም ደንበኛ ጠላት አገር ናት ብላታለች።

ሰሜን ኮሪያን ያስኮረፋት ከደቡብ ኮሪያ የሚነሱ "ጠብ አጫሪ" ያለቻቸው ፊኛዎች ናቸው። ፊኛዎቹ የሚላኩት ደግሞ ሰሜን ኮሪያን ከከዱ ከዐዕራሷ ዜጎች መሆኑ አበሳጭቷል።

ከሰኞ ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ድንበር ከተማ ካውሶንግ በኩል ሲደረግ የነበረው ዕለታዊ የስልክ ግንኙነትም አብቅቷል ብለዋል የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት።

ሁለቱ አገራት በመሀላቸው ያለውን ጠላትነት ለመቀነስ በዚህች የድንበር ከተማ ቢሮ ከፍተው ከ2018 ጀምሮ ግንኙነት ለማድረግ ሲጥሩ እንደነበር ይታወሳል።

ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ዛሬም ድረስ በጦርነት ላይ እንዳሉ ነው የሚገመተው፤ ምክንያቱ ደግሞ በፈረንጆቹ 1953 ጦርነት ሲያቆሙ አንዳችም የረባ መደበኛ የሰላም ስምምነት ስላልተፈራረሙ ነው።

የኮሪያ ማዕከላዊ ዜና አገልግሎት (ኬሲኤንኤ) እንዳስተላለፈው መግለጫ ከሆነ ታላቋ ሰሜን ኮሪያ ከጠላት አገር ደቡብ ኮሪያ ጋር ለመቀራረብ ከፍታው የነበረችው ጊዜያዊ ቆንስላ ከማክሰኞ ሰኔ፣ 2020 ማለዳ ጀምሮ ዘግታዋለች።

ወታደራዊ የግንኙነት መስመሮችም ከእንግዲህ አንድ በአንድ ይዘጋሉ።

ይህ ሁለቱን አገራት አገናኝ ቢሮ ባለፈው መስከረም በወረርሽኙ ምክንያት ቢዘጋም ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ የሚያደርጉትን የስልክ ግንኙነት ሲያሳልጥ ቆይቶ ነበር።

ሁለቱ ኮሪያዎች በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ስልክ ይደዋወሉ ነበር። አንዱ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ሌላኛው አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ። ሰኞ ዕለት ግን በ21 ወራት ለመጀመርያ ጊዜ "ስልክ ደውዬላት ሰሜን ኮሪያ ስልኬን አላነሳችውም" ስትል ደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።

ሰሜን ኮሪያ ለዚህ በሰጠችው ምላሽ "ስልክሽን ያላነሳሁት ከዚህ ወዲህ ፊት ለፊት መገናኘትም ሆነ በስልክ ማውራቱ ዋጋ ቢስ በመሆኑና ድርጊትሽ ሁሉ ለብስጭት እየዳረገኝ ስለሆነ ነው" ብላታለች።

የሰሜን ኮሪያው ተፈሪ መሪ የኪም እህት የሆነችው ኪም ዮ ጆንግ ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ቴሌቪዥን ባስተላለፈችው መልዕክት "ከአገሬ የከዱ ባንዳዎች ከደቡብ ኮሪያ ሆነው በራሪ ወረቀቶችን የያዙ ፊኛዎችን እየላኩ አበሳጭተውኛል፤ ስለዚህ እርምጃ እወስዳለሁ" ስትል አስፈራታ ነበር።

በዚህ መግለጫዋ ይህ ጠብ አጫሪ መልእክቶችን የያዙ ፊኛዎችን ወደ ሰሜን ኮሪያ መላክ ሁለቱ ጎረቤት አገራት የደረሱበትን የሰላም ስምምነት የሚጥስና እኛንም የሚያበሳጭ ነው ብላለች።

ድርጊቱ በፍጥነት ካልቆመ ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችልም ስትዝት ነበር።

ሁለቱ አገራት በ2018 ፓንሙጆም ላይ ባደረጉት ጉባኤ ሙን እና ኪም ሰላም ለመፍጠር መስማማታቸው ይታወሳል።

ከሰሜን ኮሪያ የከዱ ዜጎች ደቡብ ኮሪያ ከገቡ በኋላ ፖስት ካርዶችና በራሪ ወረቀቶችን የያዙ ፊኛዎችን ወደ ሰማይ በማጎን ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዲገቡ የማድረግ ነገር ለዓመታት የተለመደ ተግባራቸው ሆኖ ቆይቷል።

ፊኛዎቹ አንዳንድ ጊዜ ቼኮሌትና የፍቅር ደብዳቤዎችም ይታጨቁባቸዋል። የፖለቲካ መልእክቶችንም ይይዛሉ። ይህ ነገር ደግሞ ሰሜን ኮሪያን እጅጉኑ ያበሳጫታል።

ደቡብ ኮሪያ ግን ነገሩ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይ አድርጋ ነበር የምትመለከተው።

በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ከሰሜን ኮሪያ የከዱ የሰሜን ኮሪያ አርበኞች ማኅበር አባላት ይህንን በፊኛ መልዕክት በንፋስ ወደ ሰሜን የመላኩን ተግባር በፍጹም እንደማያቆሙት ሲዝቱ ነበር።

ይህ ሐሳብን የመግለጽ መብታችን ካልተከበረማ ምኑን ደቡብ ኮሪያ ኖርነው ሲሉ አስተያየት ይሰጡ ነበር።

ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ደቡብ ኮሪያም ፍላጎት እንዳላት ገልጻ ነበር፤ ምክንያቱም ሰሜን ኮሪያ በዚህ ድርጊት ክፉኛ አየተበሳጨችና ደሟ እየፈላ በመምጣቷ ነበር።

ሰሜን ኮሪያዊያን በአብዛኛው ኢንተርኔት የላቸውም፤ ቢኖራቸውም መረጃን እንደልብ ማሰስ አይችሉም። ብቸኛ የመረጃ ምንጫቸውም የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።

በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል የነበረው ጠላትነት ረገብ ያለው እንደ ፈረንጆቹ በ2018 የሁለቱ አገራት መሪዎች ሦስት ጊዜ ከተገናኙ በኋላ ነበር። እንዲህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ሁለቱ አገራት ከዚያ በፊት ተገናኝተው አያውቁም።

ፒዮንግያንግ ከሴኡል ጋር ያላትን ግንኙነት እየቆረጠች የመጣችው ዛሬ ሳይሆን ኪም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቬትናም ሃኖይ ሊያደርጉት የነበረው ግንኙነት ከተሰረዘ በኋላ ነው።

ሁለቱ ኮሪያዎች ከ1950-53 ያደረጉት ጦርነት ያበቃው በሰላም ስምምነት ሳይሆን በተኩስ አቁም ብቻ ስለነበረ አሁንም ድረስ ሁለቱም አገራት ጦርነት ላይ እንደሆኑ ነው የሚያስቡት።