የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በአሜሪካ አዲስ ሕግ እንዲረቀቅ ምክንያት ሆነ

ከፍተኛ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ባለስልጣናት ተንበርክከው ጆርጅ ፍሎይድን ሲያስቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ከፍተኛ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ባለስልጣናት ተንበርክከው ጆርጅ ፍሎይድን ሲያስቡ

በአሜሪካ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት በዲሞክራት ፓርቲ አባላት አመንጪነት አዲስ የሕግ ረቂቅ ቀርቧል። ረቂቁ የአሜሪካንን ፖሊስ የሚመለከት ነው።

ይህ የሕግ ረቂቅ በፍጥነት እንዲቀርብ ያደረገው የጆርጅ ፍሎይድ በሜኔሶታ ግዛት፣ ሚኒያፖሊስ ከተማ ውስጥ በፖሊስ በግፍ መገደሉ ሲሆን ይህን ተከትሎ በመላው አሜሪካ የተቀሰቀው ተቃውሞ ሌላ ምክንያት ሆኗል።

የሕግ ረቂቁ በአሜሪካ እጅግ ከባድ ሆኖ የቆየውን ፖሊስን የመክሰስ ጉዳይ ቀላል ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የተጠርጣሪዎችን አንገት በክንድ ጠምልሎ መያዝ እና ተጠርጣሪ ትንፋሽ እንዲያጥረው ማድረግን ያስቀራል ተብሏል። በተለይም ረቂቁ ዘርን ማዕከል ያደረጉ የፖሊስ እርምጃዎችን ይቀንሳል ተብሎለታል።

ይህ ረቂቅ የሚኒያፖሊስ ሕግ አውጪዎች የከተማዋን ፖሊስ ኃይል ለመበተን መዛታቸውን ተከትሎ ነው የቀረበው።

የጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ በግፍ መግደል ይህ ረቂቅ በቶሎ እንዲረቀቅ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።

ነገር ግን ረቂቁ በሁለቱም ምክር ቤት ዲሞክራቶች ዘንድ ከፍ ያለ ድጋፍ ያግኝ እንጂ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሚገኙ ሪፐብሊካኖች ይደግፉታል ወይ የሚለው አጠያያቂ ሆኗል።

የሟች ጆርጅ ፍሎይድ ወንድም በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሕግ መምሪያው ምክር ቤት ቀርቦ ምስክርነት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ "ጀስቲስ ኢን ፖሊሲንግ አክት-2020" የተሰኘው ሪቂቅ ለሕግ መምሪያ ምክር ቤት የቀረበው ትናንት ሰኞ ሲሆን ረቂቁን ያስተዋወቁት ዝነኛዋ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ፣ እንዲሁም ቸክ ሹመር፣ እና ጥቁሩ የምክር ቤት አባል ካማላ ሀሪስ ናቸው።

አፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፒሎሲ ይህን ረቂቅ የሕግ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ከማስተዋወቃቸው በፊት በቅርብ ጊዜ በፖሊስ ግፍ የተገደሉ ጥቁር ሴትና ወንድ አሜሪካዊያንን ስም ዝርዝር ለሸንጎው አሰምተዋል።

ይህ ረቂቅ የሕግ ሐሳብ ወደፊት ሕግ ሆኖ ከጸደቀ የፌዴራል ፖሊስ ኃይልን ሳይሆን እንደ ረቂቅ ካሜራ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ያስገድደዋል።

ማጅራትን ጠምልሎ መያዝ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ ድንገቴ አሰሳና አፈሳ ማድረግንም ይገድባል።

ከዚህም በላይ ፖሊስ ለሚፈጽማቸው ጥፋቶችና የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሚሆንበትን ዕድል ያመቻቻል። ይህን በማይተገብሩ የፖሊስ ኃይሎች ላይ የፌዴራል ፈንድ እንዳይለቀቅላቸው ያደርጋል።

"የጆርጅ ፍሎይድ በዚያ መንገድ መሰዋት ለበርካታ አሜሪካዊያን በስቃይና በግፍ መሞት ምን እንደሚመስል ለቅጽበት እንዲያስቡት እና ብሔራዊ የጋራ ስሜት እንዲያገኙም ጭምር አድርጓል" ብለዋል ናንሲ ፒሎሲ በንግግራቸው።

"ዛሬ ይህ ብሔራዊ የመጠቃት ስሜት ወደ ብሔራዊ ሕግ የሚሸጋገርበት ዕለት ነው" ሲሉም የሕጉን አስፈላጊነት አስምረውበታል።

ይህ ሕግ ሲጸድቅ ተጠርጣሪዎችን በግፍ መግደልን ይከላከላል፣ ፖሊሶች የሚገዟቸውን የጦር መሣሪያዎች ዓይነት ይወስናል፣ የፍትሕ ሚኒስትር በፌዴራልና በአካባቢ ፖሊስ የሚፈጸሙ ዘር ተኮር በደሎችን እንዲመረምር ስልጣን ይሰጣል።

ከዚህም በተጨማሪ የፖሊስን የሕግ ጥሰቶች የሚመዘገብ ትልቅ ብሔራዊ ቋት እንዲኖር ያስችላል።

አንዳንድ ሪፐብሊክን የራሳቸውን የሕግ ረቂቅ ሐሳብ ለመጻፍ እንደሚያስቡ ፍንጭ የሰጡ ቢሆንም በአመዛኙ የዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ ግን ለናንሲ ፒሎሲ ረቂቅ ድጋፍ ስለመስጠት አለመስጠቱ አልታወቀም።

ከዶናልድ ትራምፕ መስመር አፈንግጠዋል የሚባሉት የሪፐብሊካኑ ሴናተር ሚት ሮምኒ ባለፈው እሑድ በትዊተር ሰሌዳቸው ከሰልፈኞች ጋር ወደ ዋይት ሐውስ ሲያቀኑ የሚያሳይ ፎቶግራፍ የሰቀሉ ሲሆን ከፎቶግራፉ ስር "የጥቁሮች ሕይወት ግድ ይለኛል" (ብላክ ላይቭስ ማተር) የሚል ጽሑፍ አስቀምጠዋል።

በሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውስጥ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ቁጥር ስለሚያይል ይህ ረቂቅ በከፍተኛ ድምጽ የማለፍ ዕድል ቢኖረውም በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ግን እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል የሚል ስጋት አለ።

በተለይም ዶናልድ ትራምፕ ከናንሲ ፒሎሲ ጋር ያላቸው የሻከረ ግንኙነት እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ተሰግቷል።

ረቂቅ ሕጉ በአሜሪካ ሕግና ሥርዓት እንዲሸረሸር ሊያደርግ ይችላል በሚል ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ ሊያቀርቡበት ይችላሉ ተብሎም ተሰግቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ ካቀረቡበት ደግሞ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውድቅ ሊያደርገው የሚችለበት ዕድል ሰፊ ይሆናል።