ለ34 ዓመታት ምስጢር ሆኖ የቆየው የስዊዲኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ግድያ

ኦሉፍ ፓልማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሕዝብ በሚበዛበት ጎዳና ላይ የተገደሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ኦሉፍ ፓልማ

"ተራ ሕዝብ" ብሎ አጉል ቋንቋ አለ፡፡ "ተራ ጠቅላይ ሚኒስትርስ?"

እንዲያ ብሎ ነገር ካለ የስዊድኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማን ማንም አይቀድማቸውም፡፡

ከሕዝብ ጋር እየተጋፉ ጉሊት ወርዶ ቲማቲም መግዛት ተራ ካስባለ፣ ፓልማ ተራ ነበሩ፡፡

ብስክሌት እየጋለቡ ቤተ መንግሥት መሄድ ተራ ካስባለ ፓልማ ተራ ነበሩ፡፡

ሲኒማ መሰለፍ ተራ ካስባለ ፓልማ ተራ ሰውም፣ ተራ ጠቅላይ ሚኒስትርም ነበሩ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ግን፣ በአንድ ተራ ምሽት ‹‹ተራው ጠቅላይ ሚኒስትር›› ሲኒማ ቤት ሄደው አንድ 'ተራ' ኮሜዲ ተመልከተው ሲወጡ በአንድ ጥቁር ኮት በለበሰ "ተራ" ነፍሰ ገዳይ ተገደሉ፡፡

ማን ገደላቸው?

ለዚህ ጥያቄ አጭሩ መልስ "እንጃ!" የሚል ነው፡፡

ፖሊስንም፣ አባዲናንም፣ ወንጀል ምርመራንም፣ አቃቢ ሕግንም ብትጠይቁት ይህንኑ ነው የሚላችሁ፡፡ "እኔንጃ!"…. "እኛንጃ!"

ወደው አይደለም ታዲያ፡፡ ወንጀለኛው ተነነና ነው…ቢፈለግ ቢፈለግ ዱካው ጠፋና ነው…፡፡ ለ34 ዓመታት!

የፓልማ ኑሮ ተራ ቢመስልም ሞታቸው ተራ ሊሆን ያልቻለውም ለዚሁ ነው፡፡ ጉዳዩ ተዳፈነ ሲባል ድንጋይ ፈንቅሎ ይነሳል…፡፡ አበቃለት ሲባል…አንዱ ደውሎ…'እኔ ነኝ የገደልኳቸው፤ እባካችሁ እሰሩኝ' ይላል፡፡

ነገሩ እኛ ለበዓሉ ግርማ ሞት እንደምንብሰለሰለው መሆኑ ነው፡፡ ለስዊድኖች የጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ ሞት እንዲያ ያለ ነው፤ እንቆቅልሽ…ሁልጊዜም የሚከነክን፣ የሚያብከነክን…፡፡

ዶ/ር ጃን ቦንደርሰን በግድያው ዙርያ መጽሐፍ የጻፉ ዝነኛ ደራሲ ናቸው፡፡ "Blood on the Snow, The killing of Olof Palme" የተሰኘ ወፍራም ሥራ አላቸው፡፡

በዚሁ የግድያ እንቆቅልሽ ላይ ለቢቢሲ ሰሞኑን ሲናገሩ፣ "…ምን ማለት መሰለህ፣ እንዴት ብዬ ላስረዳህ? ነገሩ እኮ ማርጋሬታ ታቸር በዝነኛው የሎንዶን አደባባይ (ፒካዲሊ ሰርከስ) በሽጉጥ ተደብድባ ተገድላ፣ ገዳይዋ ተንጎማሎ ያላንዳች ስጋት ባቡር ተሳፍሮ ሲሰወር ማለት ነው…ይህ ነው'ኮ የሆነው፤ የዛሬ 34 ዓመት በስቶክኾልም"፡፡

ይልቅ ጊዜ አናጥፋ! "ማን ገደላቸው?"ን ትተን "እንዴት ተገደሉ"ን እናስቀድም፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማ የተለያዩ አገራት መሪዎችንና ሥርዓታቸውን ይተቹ ነበር

እንዴት ተገደሉ?

ወሩ ጥቅምት ነበር፤ ምሽቱ አርብ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ የሕዝብ ሲኒማ ቤት ሄዶ ፊልም ማየት አማራቸው፡፡ ለነገሩ ሐሳቡ መጀመርያ የባለቤታቸው የወ/ሮ ሊዝቤት ነበር፡፡

‹‹ለምን ሲኒማ አንገባም አሏቸው፡፡ ተስማሙ፡፡ ልጃቸውን ማርቲንን ጠርተው "እስኪ የኔ ልጅ ሮጥ ብለህ ለኔና ላባትህ የሲኒማ ቤት ትኬት ገዝተህ ጠብቀን፤ ጎሽ ተባረክ" አሉት፡፡

ልጃቸው ሄደ፡፡ ሲኒማ ቤት በር ሊገናኙ ተቃጠሩ፡፡

ባልና ሚስት እንደነገሩ ለባብሰው ወጡ፡፡

ሁለቱም አጀብ አይወዱም፤ ሪፐብሊካን ጋርድ የላቸውም፡፡ እስካፍንጫው የታጠቀ ልዩ ኮማንዶ አያሰልፉም፡፡

ያን ምሽትም እንደ ሁልጊዜው ማንንም ሳያስከትሉ ነበር ወደ ሲኒማ ቤት ያመሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማንም መንገድ ላይ ነበር የሚያገኛቸው፤ ብርቅ አልነረም እርሳቸውን ማየት፡፡

‹‹ በቃ አንድ ተራ ዜጋ ነኝ፤ ጠ/ሚኒስትር ስለሆንኩ ልዩ ክብካቤ አይገባኝም›› ይሉ ነበር፡፡ ዜጋውም በፈለገው ሰዓት መንገድ ላይ አስቁሞ ያናግራቸው ነበር፡፡

በነገራችሁ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ ሁሌም አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡ በአገራቸው ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር የሚናገሩት አቧራ ያስነሳል፡፡ የሚሰጡት አስተያየት ሚዲያ ያንጫጫል፡፡

እጅግ ተወዳጅ ስነበሩ ሊሆን ይችላል ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው አገራቸው ስዊድንን እያስተዳደሯት የነበረው፡፡

የተቀናጣ ሕይወት ያልነበራቸው ፓልማ፣ ለዓለም ጭቁኖች ድምጽ እሆናለው ያሉት ባለጸጋው ፓልማ ያን ቀፋፊ ምሽት ያለ አንዳች አጀብ ሲኒማ ገብተው ኮሜዲ አይተው ወጡ፡፡ ምን ዋጋ አለው ደጅ ላይ ትራጀዲ ገጠማቸው፡፡

ታሪኩ እንዲህ ነው…

የሚወዷቸውን ባለቤታቸውን ወ/ሮ ሊዝቤትን ከጎናቸው ሸጎጥ አድርገው ከሲኒማ ቤት ወጡና በእግር መጓዝ ጀመሩ፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማን ከባለቤታቸው ሊዝቤት ጋር

መሽቷል'ኮ፡፡ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ21 ደቀቃ ሆኗል፡፡

ኾኖም ዕለቱ አርብ ስለነበር በርካታ ስዊድናዊያን በየመሸታ ቤቱ ሽር ብትን እያሉ ነበር፤ አርብ ለስዊድኖች የአሸሼ ገዳሜ ሌሊት ናት፡፡

ባልና ሚስት ከሲኒማ ቤት ወጥተው ትንሽ እንደተጓዙ አንድ ረዥም ሰውዬ፣ ጥቁር ጃኬት የለበሰ፣ ደንዳና፣ ትከሻው የሚከብድ…በሰፊ መዳፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትከሻ ከኋላ መጥቶ መታ መታ አደረገ፡፡ ፓልማ ዞር ሲሉ ከመቅጽበት በጥይት ደበደባቸው፡፡ አንድ ጥይት በቂ ነበረች፡፡

ጥይቷን ከቅርብ ርቀት በጀርባቸው ነው የለቀቀው፡፡

አንድ ሰው በዚህ ርቀት ሲተኮስበት ሞቱ ቅጽበታዊ ነው የሚሆነው፡፡ እርሳቸውም ተዘልፍልፈው መሬት ከመንካታቸው በፊት ነፍሳቸው ወጣች፡፡ የሞታቸው ፍጥነት የብርሃን ነበር፡፡

ጥቁር ኮት የለበሰው ነፍሰ ገዳይ ቀጥሎ ባለቤታቸው ላይ ተኮሰና…ምንም እንዳልተፈጠረ ነገር ቀብረር ብሎ…ትንሽ ዱብ ዱብ እንደማለትም እየቃጣው መንገዱን ተሻገረና የሆነች የኛን "70 ደረጃ" የምትመስል መወጣጫ ተሻግሮ ሄደ፡፡ እነሱ ‹‹89 ደረጃ›› ይሏታል፡፡

ያኔ ለተመለከተው'ኮ ፍቅረኛውን ተቃጥሮ ያረፈደ ጅንን ቀብራራ ጎረምሳ እንጂ ነብሰ ገዳይ ሊመስል? በጭራሽ፡፡

ደግሞ ገድሎ ሲሄድ በርካታ ሰዎች ዐይተውታል፡፡ በትንሹ 20 ሰዎች ተመልክተውታል፡፡

ቢኾንም አልተከተሉትም፡፡ ለምን አልተከተሉትም ግን?

ብቻ በሶምሶማ ሄደና ተሰወረ፡፡ ይኸው ስንት ዘመን፡፡ እምጥ ይግባ ስምጥ….የሚያውቅ የለም፡፡

34 ዓመታት…ዝም ጭጭ፡፡

ረዥሙ ነፍሰ ገዳይ እንዴት "አጎንብሶ"አመለጠ?

ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚያህል ነገር ገድሎ እየተንጎማለሉ መሄድ አለ አንዴ?

እሺ መሄዱንስ ይሂድ? ግን ወዴት ሄደ? ስዊድናዊያን ይጠይቃሉ፡፡ እስከዛሬ መልስ የለም፡፡

የሚገርመው ይህ ግድያ የተፈጸመው በስቶክሆልም ግርግር በሚበዛበት ቁጥር-1 ጎዳና ላይ መሆኑ ነው፤ በስቪየቫገን፡፡

ደርዘን የሚሆኑ ሰዎች ያን ረዥሙን ነፍሰ ገዳይ ዐይተውታል፤ በስካር መንፈስም ይሁን በሞቅታ…፡፡ውሃ የያዙትም ይሁን ዊስኪ የጨበጡ…፣ የሚሳሳሙትም ይሁን የሚጨቃጨቁት…፡፡ 20 ሰዎች ዐይተውታል፡፡ ኾኖም አልተከተሉትም፡፡ ለምን አልተከተሉትም?

ያ ረዥሙ ነፍሰ ገዳይ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን በጥይት ደብድቦ ሲሄድ እነዚያ ሁሉ ሰዎች ያን ምሽት ተመልክተውታል፤ በሁለት ምክንያት፡-አንደኛ ምሽቱ አርብ ነበር፤ "ፍራይዴይ ናይት!"

ሁለተኛ ሰው የሚርመሰመስበት ጎዳና ነበር ግድያው የተፈጸመው፡፡ግን ለምን አልተከተሉትም?

ምናልባት ትኩረታቸው ሟችን ለማዳን ስለነበረ ይሆን?

በአካባቢው ይዝናኑ የነበሩ ሰዎች በ6ደቂቃ ውስጥ የሚወዷቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆስፒታል ወስደዋቸዋል፡፡ ኾኖም ያ ሁሉ ከንቱ ነበር፡፡

ገዳዩ እጅግ አደገኛ መሣሪያ ነበር የተኮሰባቸው፡፡ "ስሚዝ ኤንድ ዌሰን-575 ሪቮልቨር" የሚባል ክፉ መሣሪያ ፡፡ በብዛት ፊልም ላይ ነፍሰ ገዳዮች ይዘውት በምናየው መጥፎ መሣሪያ፡፡

ለዚያም ነው ፓልማ በሰከንዶች ሽርፍራፊ የሞቱት፡፡ በተተኮሱበት ቅጽበት፤ ተዝለፍልፈው መሬት ላይ ከመውደደቃቸው በፊት ነው የሞቱት፡፡ ያን ያህል ኃያል መሣሪያ ነበር የተተኮሰባቸው፡፡ ጥይት መከላከያ ደርበው ቢለብሱ እንኳ አይተርፉም ነበር፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማ ግድያ በአገሪቱ ድንጋጤንና መላምቶችን አስፋፋ

10 ሺህ ሰዎች በፖሊስ ተመርምረዋል

ከዚያች ምሽት ጀምሮ ላለፉት 34 ዓመታት ፖሊስ እንቅልፍ አልተኛም፡፡ ወይም እንቅልፉን ለጥጦታል፡፡ ሁለቱም ዓረፍተ ነገሮች ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ፖሊስ እንቅልፉን ባይለጥጥ እንዴት በአደባባይ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር የገደለ ሰው በቁጥጥር ሥር ማዋል ያቅተዋል?

"አልተኛንም" የሚለውም ትክክል ይመስላል፡፡ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ተመርምረዋል፡፡

እንቅልፍ በዐይኔ ሳይዞር ላለፉት 34 ዓመታት መርምሬ የደረስኩበትን አሳውቃለሁ ብሏል ፖሊስ፡፡ ከነገ በስቲያ ነው ይህ ቀን፡፡ረቡዕ፡፡

የክፍለ ዘመኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ቢባል አያንሰውም፡፡

ዋና አቃቢ ሕግ ክሪስተር ፒተርሰን ባለፈው ጥቅምት ለስዊድን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ‹‹ያን ምሽት ምን እንደተፈጠረና ጠ/ሚኒስትራችንን ማን እንደገደላቸው በቅርቡ የጠራ መረጃ ይን እንቀርባለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል፡፡

መቼስ የሆነ ነገር ባያገኙ እንዲህ የሚያጓጓ ተስፋን አይሰጡም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተገደሉ በኋላ በስዊድን ምን ሆነ?

ስዊድኖች ድምጻቸው ከፍ ብሎ የሚሰማ ሕዝቦች አይደሉም፡፡ አርምሞ ላይ ያሉ ሰዎች ነው የሚመስሉት፡፡ አገራቸውም እንደዚያ ናት፡፡ ኮሽታ ይናፍቃል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድያ እጅጉን ደንግጠው ነበር፤ ያኔ፡፡

ቻርሎታ ዋልስተን ለምሳሌ ያን ጊዜ 12 ዓመቷ ነበር፡፡ ኾኖም ይህ ክስተት ሲከሰት በደንብ ታስታውሳለች፡፡ አባቷ የሆነው ነገር አስደንግጦት ነበር፡፡

‹‹ቤታችን ቲቪ ተከፈተ፡፡ በመላው ስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተገደሉበት ሁኔታ እንጂ ስለሌላ ነገር የሚያወራ ሰው ጠፋ፡፡›› ብላለች ለቢቢሲ፡፡ አሁን 46 ዓመቷ ነው ታርሎታ፡፡

ያን ጊዜ እጅግ ልባቸው በሐዘን ተነክቶ ስለነበር ትምህርት ቤት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ማድረጋቸው ትዝ ይላታል፡፡

‹‹በስዊድን እንደዚህ ዓይነት ነገር ተከስቶ የሚያውቅ አይመስለኝም ነበር፡፡ ሁሉም ፖለቲካ ተረሳ፤ ሁሉም ጉዳይ ተረሳ፤ የርሱ ሞት አገሩን ሁሉ በሐዘን ዋጠው፡፡ ››

ከግድያው በኋላ ተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የስዊድን ፖሊስም ግራ ተጋብቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም መርማሪዎች ወደ ወንጀል ቦታ መጥተው አካባቢውን በፍጥነት መከለል ሲገባቸው የተወሰኑ ቦታዎችን ብቻ ነው ያጠሩት፡፡ ድንበር ቶሎ መዝጋት ሲገባቸው ያ አልተደረገም፡፡

ይባስ ብሎ በክስተቱ የደነገጡ ዜጎች ወደ ቦታው በብዛት ይጎርፉ ነበር፡፡ ይህ ነገር የአሻራ ምርመራ እንዲደረግ ዕድል አልሰጠም፡፡

የጠ/ሚኒስትር ፓልማ ደም የፈሰሰበት ቦታ ሳይደርቅ እንኳ ሰዎች በአጠገቡ ይቆሙም ይመለቱም ነበር፡፡ በነገታው መጥተው አበባ የሚያስቀምጡም ነበሩ፡፡ ነገሩ ሁሉ ትርምስምስ ብሎ ነበር፡፡ ምናልባት ስዊድኖች ለወንጀል አዲስ ስለሆኑ ይሆን? እንዴት ፖሊስ ሥራውን በአግባቡ አይሠራም?

ለምሳሌ የዓይን እማኞች ወዲያው ቃላቸው እንዲሰጡ እንኳ ሳይደረግ ወደ ቤታቸው ሄደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ባለቤታቸው ላይ ከተኮሱት አንደኛዋ ጥይት በወቅቱ ሳትገኘት ቀርታ ከቀናት በኋላ ነው አንድ መንገደኛ መሬት ላይ አግኝቷት ለፖሊስ የሰጠው፡፡

ይህ ሁሉ መዝረክረክ የሚናገረው ፖሊስ ያን ጊዜ ሥራውን በአግባቡ አለማከናወኑን ነው፡፡

ለማንኛውም ቀናት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን እየተኩ ሄዱ፡፡ ገዳይ የለም! በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጥቆማ ይሰጣሉ፡፡ ገዳይ ግን የለም፡፡

ነፍሰ ገዳዩ ለዘመናት አለመታወቁ ስዊድናዊያኑን ይበልጥ ግራ አጋባቸው፡፡ ነገሩ ከትኩስ ደረቅ የግድያ ወንጀል አልፎ ተረትና ፊልም ወደ መሆኑ ያመዘነውም ለዚሁ ይሆናል፡፡

በጊዜ ሂደት ይህ ነገር እንደ ቅዠት እያደረገ የሚያባንናቸው ዜጎች ተፈጠሩ፡፡ ግድያውን መርምረን ደረስንበት የሚሉ አማተር ጀብደኛ መርማሪዎች ተወለዱ፡፡ privatspanarna ይሏቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጤነኞች ናቸው፤ ሌሎች ግን ዘብረቅ ያደርጋሉ፡፡

ግድያውን ተከትሎ ባለፉት 30 ዓመታት ራሱን የቻለ በሽታ ተፈጥሯል፤ በስዊድን፡፡ ፓልማኒያ የሚባል፤ እንዲሁም ፓልማሲክ የሚባል፡፡

የዚህ በሽታ ምልክቶች በሰውየው አሟሟት መብሰልሰል ነው፤ ያለማቋረጥ፡፡ በራስ ተነሳሽነት ምርመራ መጀመርንም ያካትታል፣ አንዳንዴም ገዳዩ እኔ ነኝ ብሎ ለፖሊስ እጅ መስጠትን ይጨምራል፡፡

በዚህ መንገድ 130 ሰዎች እኛ ነን ገዳዮቹ ብለው ለፖሊስ እጅ ሰጥተዋል ቢባል አሁን ማን ያምናል? አነርሱ ገዳይ እንደሆኑ ይመኑ እንጂ አንዳቸውም ግን ወንጀለኛ ኾነው አልተገኙም፡፡ የ"ፓልማሲክ" ተጠቂዎች ናቸው፡፡

ይህ ግድያ እንደ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ እንደ ወንድማቸው እንደ ሮበርት ኬነዲ፣ እንደ በዓሉ ግርማ፣ እንደ ቱፓክ ሻኩር ምስጢር ነው፡፡ኾኖም ምስጢሩ አልተፈታም፡፡

በ34 ዓመት ምርመራ ከ10ሺ ሰዎች በቅጡ ተመርምረዋል፡፡ በስዊድን ዋና ቢሮ የሚገኘው የምርመራ ዶሴ ፋይል 250 ሜትር ሼልፍ ቢሰራ አይበቃውም፡፡

በምድር ላይ እስከዛሬ ካልተፈቱ የግድያ እንቆቅልሾች አንዱና ትልቁ የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡

ይህን ግድያ ተንተርሶ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፊልሞች፣ መጽሐፎች፣ የመድረክ ተውኔቶች፣ የጋዜጣ መጣጥፎት ተጽፈዋል፣ ተደርሰዋል፣ታትመዋል፣ ተሰራጭተዋል፡፡

በፓልማ ግድያ ብቻ ላይ ያተኮረ ፖድካስት ሥርጭትም በስዊድን ውስጥ አለ፡፡ ፓልሜሞርዴት ይባላል፡፡ 173 ክፍል ድረስ ተሰራጭቷል፡፡ የቀን ቅኝት በሉት፡፡

ሌላ ቡድን ደግሞ አለ፡፡ ሟቹን ለመዘከር ሲል ሲኒማ ገብቶ ፊልም አይቶ፣ በዚያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሄዱበት ጎዳና በሌሊት ሄዶ ልክ በተገደሉባት ሰዓት 05፡21 የተገደሉባት ቦታ የመቆም ሥነ ሥርዓት የሚያካሄድ ቡድን፡፡

ሌላ ማኅበርም ተፈጥሯል፡፡ እውነት አፈላላጊ የሚባል፡፡ Sanningskommission የሚባል፡፡ የዚህ ማኅበር ዓላማ ደግሞ በሰውየው ዙርያ የራሱን ምርመራ እያደረገ መረጃን ለጋዜጠኞና መርማሪዎች ማቀበል ነው፡፡ የተቋቋመበት ዓላማ ገዳዩ ወይም ምስክሮች ፖሊስ ጋር መሄድ ከፈሩ እኛ ጋ ሊመጡ ይችላሉ በሚል ነው፡፡

በአጭሩ አገሩ በዚህ ግድያ የስዊድን ሕዝቦ አብዶ ነው የኖረው ማለት ይቻላል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሉፍ ፓልማ የተገደሉበት ስፍራ

የሴራ ትብታቦ በእርሳቸው ዙርያ

ዝም ተብሎ ወደ ሴራ ትብታቦ (conspiracy theory) አልተገባም፡፡ ፖሊስ ተጨባጭ ነገር ሲያጣ ነው ነገሩ ሁሉ የአሉባልታና ሴራ መፈንጫ የኾነው፡፡

የመጀመርያው መርማሪ ሀንስ ሆልሜር ይባል ነበር፡፡ እንዲህ ውስብስብ ጉዳይ እንኳ ይዞ አያውቅም፣ ከዚያ በፊት፡፡ ኾኖም ምስጢሩን ፈትቼ የስዊድን ጀግና እኾናለው ብሎ የተነሳ ሰው ነበር ይሉታል፡፡

ቢለው ቢለው አልሆነለትም፡፡

መርማሪ ሆልሜር የመጀመርያ ተጠርጣሪ ያደረጋቸው ከቱርክ መንግሥት ጋር ለነጻነት የሚዋጉትን ፒኬኬዎችን ነበር፡፡ ያን ዘመን ፒኬኬ ጽንፈኛ ነው በሚል በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ተወግዞ ነበር፡፡

የሆነ ቀን እንዲያውም ተጠርጣሪውን ለመያዝ ተቃርቢያለሁ አለና፤ የፒኬኬ አባላት ይሰበሰቡበታል የሚባል ቤተ መጻሕፍትን ድንገቴ ወረራ በማድረግ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ አንዳች ነገር ጠብ አላለትም፡፡ የስዊድን ሕዝብ በዚህ መርማሪ ተናደደበት፡፡

የሆልሜር ምርመራ ፍሬ ሳያፈራ ሲቀር የሴራ መላምት ቦታውን ያዘ፡፡

የገዛ ሚስቱ ናት ያስገደለችው የሚል አለ፡፡ ለምን ቢባል እየማጋጠ አስቸግሯት፡፡

ጆን ኤፍ ኬኔዲን የገደለው ምስጢራዊ የሰይጣን አምላኪዎች ቡድን ነው ያስገደለው የሚሉም አሉ፡፡ ለምን ቢባል መልስ የለም፡፡

የገዛ ወንድ ልጁ ማርተን ነው የስገደለው ተባለ፡፡ ለምን ቢባል…አባቱ ላይ ቂያሜ ነበረው፡፡

ጨርሶውኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ አልሞቱም፣ ሁሉም ነገር ድራማ ነው ተባለ፤ ለምን ቢባል ጀግና አይሞትም፡፡

በእርግጥም በስዊድን ‹‹የፓልማ ደዌ›› የሚባል ነገር ተፈጥሮ ነበር፤ ብዙ ሰዎች በዚህ ደዌ ታመዋል፡፡

ታማሚዎች ይዘባርቃሉ፤ ሴራ ይጎነጉናሉ፡፡ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ በአንድ ወቅት ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገረው ‹‹በሽታው የእውነት ነው፤ ሰዎች ከዚህ አባዜ ከተሰቃዩ በኋላ ድነው እየደወሉ ይቅርታ ይጠይቁኛል›› ብሏል፡፡

ለማንኛውም መርማሪ ሆልሜር ውግዘት ደርሶበት ሥራውን ለቀቀ፡፡

በኋላ ላይ ነገሩን ዳር ሳላደርስ አልሞትም ብሎ በግሉ እንደ ተራ ዜጋ ምርመራውን ገፋበት፡፡ አንድ ቀን በድብቅ ሕገ ወጥ የስልክ ግንኙነት መጥለፊያ መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ ተያዘ፡፡ ሌላ ቅሌት!

አወዛጋቢው ፓልማ ማን ነበሩ?

ፓልማ ለ16 ዓመታት ግራ ዘመሙን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ መርተዋል፡፡

ይህ ፓርቲ ስዊድንን በ20ኛው ክፍለ ዘመን በአመዛኙ የመራ አውራ ፓርቲ ነበር፡፡ ስዊድንን ስዊድን ያደረጋት ይህ ፓርቲ ነው፡፡

የናጠጠ ሀብታም ግብር እየተጫነበት ድሀን እንዲደጉም፤ የሀብት ክፍፍል ሚዛናዊ እንዲሆን ያስቻለ ፓርቲ ይህ ፓርቲ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ ይህን ፓርቲ ነው የመሩት፡፡

የተወለዱት እንደነርሱ አቆጣጠር በ1927 ሲሆን ከመሳፍንት ቤተሰብ ነበር የተገኙት፡፡

በ1949 የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አባል ሆኑ፡፡ በ1969 የፓርቲውን መሪነት ከመልማያቸው ከታግ ኤርላንደር ተረከቡ፡፡

ታግ ኤርላንደር የስዊድን የ"ዌልፌር ሲስተም" አባት ይባላሉ፡፡ ስዊድን ዓለም የሚቀናባት አገር ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡ ዌልፌር ሲስተም ሀብታምን በግብር ተጭኖ ድሀን ከፍ የማድረግ፣ የማመጣጠን ምጣኔ ሀብታዊ-ወ-ፖለቲካዊ የአስተዳር ስልት ነው፡፡

ኦሉፍ ፓልማ ታዲያ ፖለቲካን የተማሩት ይህን ዘዴ በስዊድን ከዘረጉት ከኚህ ጎምቱ ፖለቲከኛ ነበር፡፡ ወደበኋላም ፓልማ የታግ ኤርላንድን ፖሊሲና ሌጋሲ ያስቀጠሉ ሁነኛ ሰው ነበሩ፡፡

ጠ/ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የሠራተኛ ማኅበራትን አቅምና ጉልበት እንዲጠነክር አድገዋል፡፡ የጤና መድኅን እንዲስፋፋ ተግተዋል፤ ከንጉሣዊ አስተዳደር ጋር የተሳሰሩ የፖለቲካ ሥልጣኖችን መንግለዋል፤ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ እንዲፈስ አስችለዋል፡፡

በርሳቸው ጊዜ መዋዕለ ሕጻናት እንደ አሸን ፈሉ፡፡ የትምህርት ጥራት ጨመረ፡፡ ሴቶች የቢሮ ሥራ ተሳትፏቸው ተመነደገ፡፡ የጾታ እኩልነት በሚደንቅ ፍጥነት በመላው ስዊድን ባሕል እየሆነ መጣ፡፡

ኦሎፍ ፓልማ የአገር ውስጥ አንበሳ ብቻ አልነበሩም ታዲያ፡፡ በዓለም አቀፍ ጉዳዮችም ድምጻቸው ኃያል ነበር፡፡

ጭቆናን ይጠላሉ፤ ጨቋኝ ያወግዛሉ፤ ተጨቋኝ ይረዳሉ፡፡

በስፔን የጄኔራል ፍራንኮን ፋሽስታዊ አገዛዝ ክፉኛ ያወግዙ ነበር፡፡ "እነዚህ እርኩስ ገዳዮች" ይሏቸው ነበር፣ የጄኔራል ፍራንኮን ሰዎች፡፡

ለአሜሪካም ሆነ ለታላቋ ሶቪየት ኅብረት አይመለሱም፡፡ በ1968 ሶቪየት ኅብረት ቼኮዝላቫኪያን ስትወር ፓልሜ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡

በ1972 አሜሪካ ሰሜን ቬትናምን በቦምብ ስትደበድብ ፓልማ ‹‹ይሄማ በ2ኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ ናዚዎች አይሁዶች ላይ ከፈጸሙት ጥፋት በምን ተለየ?" ብለው ሂስ ሂሰዋል፡፡ በዚህን ጊዜ አሜሪካ ክፉኛ ተቀየመቻቸው፡፡

በስቶክሆልምና በዋሺንግተን መሀል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ተቋረጠ፤ ለአጭር ጊዜም ቢሆን፡፡

‹‹በተናገርኩት ነገር አልጸጸትም፤ ምክንያቱም ፍትህ ሲጓደል ስታይ ዝም ማለት የለብህም፤ የትም ቢሆን፣ መቼም ቢሆን፡፡›› ብለው ነበር ድሮ ያኔ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፡፡

ፓልማ ተናጋሪ ብቻም ሳይሆን አስታራቂም ነበሩ፡፡ የ1980ዎቹን የኢራቅና ኢራን ጦርነትን የሸመገሉ ሰው ናቸው፡፡

ሰንድስቶርም የተባሉ ሰው ስለ ፓልማ አስተያየት ሲሰጡ፤ ‹‹ሰውየው ወይ በጣም የምትወደው፣ ወይ በጣም የምትጠላው ዓይነት ሰው ነበር›› ብለዋል፡፡

‹‹እጅግ እጅግ የሚወዱት ሰዎች ነበሩ፡፡ እጅግ እጅግ የተቆጡበት መንግሥታትም ነበሩ፡፡››

ለማንኛውም ፓልማ በጣም ተወዳጁ የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚባሉት ውስጥ ይመደባሉ፡፡

ከ34 ዓመታት በኋላ ዛሬም የተገደሉበት ጎዳና ላይ የአበባ ጉንጉን የሚያስቀምጡ ሰዎች ያሉትም ለዚህ ይሆናል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ክሪስ ፒተርሰን

ደቡብ አፍሪካ ትሆን ያስገደለቻቸው?

ፓልማ ዝም አልልም ባይነታቸው በርካታ ወዳጅ እንዳፈራላቸው ሁሉ ጠላትም ገዝቶላቸው ነበር፡፡

የስዊድን የቢዝነስ ሰዎችና ሊበራሎች እንደርሳቸው የተመቿቸው ባይኖርም የዓለም ኃያላን መንግሥታት ግን ጥርስ ነክሰውባቸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒሰትር ፓልማ ግድያ ከፍተኛው ተጠርጣሪ የዚያ ዘመኑ የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግሥት ነው፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፓልማ ከመገደላቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለጸረ አፓርታይድ ታጋዮች ንግግር አድርገው ነበር፡፡

‹‹የአፓርታይድ ሥርዓት ድምጥማጡ ሊጠፋ እንጂ ሊሻሻል አይገባም፡፡ አስቀያሚና መጥፎ ሥርዓት ነው›› ብለው በግልጽ አውግዛውታል፡፡

ግራ ዘመሙ ፓልማ ይህን ወሬ አውርተው ብቻ አልሄዱም፡፡ በአፓርታይድ ሥርዓት ላይ ማዕቀብ የሚጣልበትን መንገድ ያሰላስሉ ጀመር፡፡ ለነ ማንዴላ፣ ለኤኤንሲ የገንዘብ እርዳታም ማድረግ ጀመሩ፡፡ሚሊዮኖችን ለገሱ፡፡

ለአፓርታድ አፍቃሪ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ፓልማ መወገድ ያለባቸው ሰው ነበሩ፡፡አውሮጳዊ ሆነው የነጭን የበላይነት እንዴት ይቃወማሉ ሲሉ ጥርስ የነከሱባቸው የአፓርታይድ አፍቃሪ ነጮች ጥቂት አልነበሩም፡፡

ይህ በቅ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያስገደለቻቸው ደቡብ አፍሪካ ትሆን የሚል ጥያቄን አጫረ፡፡ ከፍተኛ ምርመራም ተጀመረ፡፡

ስዊድን ነገሩ ከአቅሟ በላይ ሲሆንባት እንግሊዝን እርጂኝ አለቻት፡፡ ኤምአይ-16 የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ተቋም በጉዳዩ ገባበት፡፡ የሚያውቀውን ለስዊድን አቀበለ፡፡

በእርግጥም ጠ/ሚኒስትሩ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጥርስ ተነክሶባቸው ነበር አለ፡፡ እንዲገደሉም ፍላጎት ነበር ሲል አጋለጠ፡፡

እንግሊዝ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ ከነበረ አንድ ታማኝ ምንጭ ሰውየውን ለመግደል እቅድ ተይዞ እንደነበር መረጃ አግኝታ ይህንኑ ለስዊድን አቀብላለች፡፡

ክሬግ ዊሊየምሰን የሚባል የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ የነበረ ሰው ደግሞ ግድያውን እንዲያቀነባበር ተነግሮት ነበር፡፡ ይህ ሰው ደግሞ በርቲል ዌዲን ከሚባል ስዊድናዊው የቀኝ አክራሪ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፡፡

ዌዲን ዛሬም ድረስ በሕይወት አለ፡፡ ዋዲን ተይዞ ተመረመረ፡፡ አላመነም፡፡

ዌዲን በወቅቱ ቀኝ አክራሪ ብቻም ሳይሆን የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ደጋፊና በስለላ መረብ ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበር፡፡ ግድያውን እሱ ባይፈጽምም አቀነባብሮት ይሆን?

ማን ገድሏቸው ይሆን?

ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የገደላቸውን ሰው ያን ምሽት ጣጣውን ጨርሶ መንገድ ተሻግሮ ሲሄድ ብዙዎች ቢያዩትም ፖሊስ ግን ሰውየው ያለበትን ፍንጭ ማግኘት ተቸግሮ ነበር፡፡

ኋላ ላይ የተገኘችው ጥይት እንዳሳበቀችው ገዳዩ የተጠቀመው እጅግ አደገኛ የሆነውን "357 ማግነም" የእጅ ጦር መሣሪያ ነው፡፡

ዶ/ር ቦንደርሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዚህ መሣሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥይት መከላከያ እንኳ ደራርበው ቢለብሱ ከመሞት አይድኑም ነበር፡፡

ይህ የሚያሳየው ግድያው በጣም አስተማማኝና የማያዳግም እንዲሆን ታቅዶና ተወጥኖ የተገባበት ስለመሆኑ ነው፡፡

የመጀመርያው መርማሪ ሆልሜር በ1987 በቅሌት ሥራውን መልቀቁን ጠቅሰናል፡፡ በኋላ እሱ ራሱ ልቦለድ ጸሐፊ ኾነ፡፡ ከልቦለዱ በኋላ ግን አንድ ያልጨረሰው መጽሐፍ ነበር፡፡ በግድያው ዙርያ መሆኑ ይታወቃል፤ በዚያው ሳይጨርሰው ሞተ፡፡

ከርሱ በኋላ የመጣው መርማሪ ክሪስተር ፒተርሰን የሚባል ወንጀለኛን አሰረ፡፡ ሰውየው በ1970ዎቹ በስቶክሆለም ጎዳና አንድን መንገደኛ በጩቤ ወግቶ መግደሉ ይታወቃል፡፡ ሰውየውን የገደለበት ምንም በቂ ምክንያት አልነበረውም፡፡ፍርዱን ጨርሶ የወጣ ሰው ነበር፡፡

የሚደደንቀው የዚህ ወንጀለኛ የሰውነት ቁመና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ገድሏል ከተባለው ቀውላላው ሰውዬ ጋር ምስስሎሽ ያለው ነው፡፡

ፖሊሶችና ወንጀለኛው በአንድ እንዲሰለፉ ተደርጎ የጠቅላይ ሚኒስትር ፓልማ ሚስት ተጠርጣሪውን በቲቪ እንድታየው ተደርጎ ‹‹ገዳዩ የትኛው ይመስልሻል?›› ተባለች፡፡

ፒተርሰንን ነጥላ አወጣችው፡፡ ተከሰሰና በ1989 ዕድሜ ልክ ተፈረደበት፡፡

ነገር ግን ጠበቃው ወዲያው ይግባኝ አለ፡፡ የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው ከሦስት ቀን በኋላ ፍርድ ቤት በነጻ ለቀቀው፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ላይ በቂ መረጃ ሊገኝ ቀርቶ አንዳችም አሳማኝ ነገር አልተገኘበትም፡፡

በዚያ ላይ ፖሊስ ለሴትዮዋ ለይታ እንድታወጣው ከመጠየቁ በፊት ስለ ሰካራምነቱ ነግሯት ነበር፡፡ ሰካራም መለየት ደግሞ ቀላል ነው፡፡

ለካንስ ያ የሰካራም ፊቱ ነው ተጽእኖ አድርጎባት ‹‹እሱ ነው ገዳዩ›› ያስባላት፡፡

ሰካራሙ ሰውዬ ሲፈታ ለተንገላታበት 50ሺ ዶላር ካሳ ተከፍሎት ነው፡፡

ወደቤቱ ቀብረር ብሎ ሲሄድ ታዲያ በአንድ እጁ ቮድካ በሌላ እጁ ቤይሌይ የአይሪሽ መጠጥ ይዞ ነበር፡፡ ያ ክስተት በጋዜጠኞች ካሜራ ተቀርጾ ቀርቶ ስለነበር እርሱ ያን ጊዜ ይዞት የነበረውን መጠጥ ቅልቅል ዛሬም ድረስ ስዊድናዊን ‹‹ዘ ኪለር›› እያሉ ይጠሩታል፡፡

ፒተርሰን ቮድካውን እየጠጣ ኖረ፡፡ ኖሮ ኖሮ በ2004 ሞተ፡፡

ከመሞቱ በፊት ግን ጋዜጠኞች ጋር ይደውልና ገዳዩ እርሱ ስለመሆኑ መጠነኛ ፍንጭ ይሰጣቸውና በጉጉት ልባቸውን ያንጠለጥላል፡፡ ሞቅ ብሏቸው ሲጽፉ ደግሞ በስም ማጥፋት ይከሰቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ብዙ ብር ካሳ ይፈረድለታል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ኖሮ ኖሮ አንድም ፍንጭ ሳይተው የሞተው፡፡

ከዚህ ሰውዬ ሞት በኋላ ስዊድን በተወዳጁ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሞት ምላሽ በማጣቷ የሴራ ትብታቦ ውስጥ ተዘፍቃ ኖራለች፡፡ በግድያው ዙርያ ብዙ ሴራ ነዳፊዎች ያልፈተፈቱት አሉባልታ የለም፡፡ አንዲያውም ይህ ነገር በስዊድን የሥነ ልቦና ሞያዊ ስም ሁሉ ተሰጥቶታል፡፡ Palmes sjukdom ይሉታል፡፡ የፓልማ ደዌ እንደማት ነው፡፡

በ1996 አንድ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ጠቅላይ ሚኒስትራችሁ የተገደሉት አፓርታይድን በመቃወማቸውና ለኤኤንሲ ፓርቲ ድጋፍ በመስጠታቸው ነው የሚል መረጃ አወጣ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ ሰውየው ይህን ባለ በስንተኛው ቀን ሞተ፡፡

የስዊድን ፖሊስ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሄዶ ምርመራ ጀምሮ ነበር፡፡ ምንም ያገኘው ነገር አልነበረም፡፡

ስቴግ ላርሰን ደራሲ ነው፡፡ "Girl with the Dragon Tattoo" መጽሐፍ የጻፈው እርሱ ነው፡፡ ይህን ግድያ በተመለከተ እስከ ሞቱ ድረስ ሲመራመር ነው የኖረው፡፡ እርሱ የሚምነው የአፓርታይድ ሰዎች ናቸው ፓልማን ያስገደሉት፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገደሉበት ቦታ ላይ የተቀመጠ ማስታወሻ

የጦር መሣሪያ ደላሎች ይሆኑ?

ዶ/ር ቦንድሰን በበኩላቸው ግድያው ከሕንድ የጦር መሣሪያ ንግድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

እንዴት ሲባሉ፣ ቦፎርስ የተባለ የስዊድን ኩባንያ ለሕንድ የጦር መሣሪያ ለመሸጥ በ80ዎቹ እና 90ዎቹ ስምምነት አድርጎ ነበር፡፡ ኩባንያው ይህንን ለመሳካት በርካታ ክፍያዎችን ለሚሊየነር ደላሎች ፈጽሟል፡፡ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትረ ራጂቭ ጋንዲ ሳይቀሩ በነገሩ ተነክረውበት ነበር፡፡

ጠ/ሚኒስትር ፓልማ ይህን የጦር መሣሪያ ሻጭ ኩባንያ ጋር የተያያዘውን ሙስና ደርሰውበት ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ ኩባንያ ትርፍ ለማጋበስ ያሰፈሰፉ ሚሊየነር ደላሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነፍሰ ገዳይ ቀጥረው አስገድለዋቸዋል፡፡

ይህ የዶ/ር ሐሳብ ግን ፖሊስ ችላ ብለውታል፡፡ የማይመስል ነገር ሆኖባቸው፡፡

ከዐይን እማኞቹ አንዱ ለምን ራሱን አጠፋ?

ሌላው ጥርጣሬ ስካንዲያ ከተባለ ኡንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ከሚሰራ ሰውዬ ጋር ይያያዛል፡፡

ይህ ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያች ምሽት ከተገደሉበት ጎዳና አጠገብ ነው የሚገኘው፡፡

በዚህ ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚሠራ ስካንዲያ ማን የሚባል ሰው ነበር፡፡ ግድያውን ከተመለከቱ 20 ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ በ2000 ዓ. ም ራሱን አጠፋ፡፡

ለምን ራሱን ሊያጠፋ ቻለ? የሚያውቀው ነገር ይኖር ይሆን?

በዚህ ሰው ላይ ትኩረት አድርጎ ለ12 ዓመታት ምርመራ ሲያደርግ የነበረ ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ቶማ ፒተርሰን ይባላል፡፡ እርሱ ነው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ገዳዩ ይህ ሰው ሲል ጥርጣሬ የጀመረው፡፡

መነሻ ምክንያት ነበረው፡፡

ይህ ራሱን ያጠፋው ሰው አንደኛ የጦር መሣሪያ ስልጠና ወስዷል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የጦር መሣሪያ መሰብሰብ ሆቢው ያደረገ አንድ ወዳጅ ነበረው፡፡ ይህ ወዳጁ ሰውየው የተገደሉበት ዓይነት መሣሪያ ነበረው፡፡ በዚያ ላይ ተጠርጣሪው ማግነም ከሚባለው ተሸከርካሪ ጦር መሣሪያ ትልቅ ፍቅር ነበረው፡፡

በዚያ ላይ ሰውየው ቃል ሲሰጥ ‹‹እዛ ቦታ የተገኘሁት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነፍሳቸው አልወጣች እንደሆን ለማትረፍ ነበር›› ብሎ ዋሽቷል፡፡

ብዙ ሰዊድናዊያን ይህ ሰው አንድ ቡድን ነገሩን ለማዘናጋት እየተጠቀመበት እንደሆነ ያምናሉ እንጂ ገዳይ ነው አይሉም፡፡

ምክንያቱም ገዳዩ እጅግ ግዙፍና ረዥም መሆኑ እየታወቀ ይህ ተጠርጣሪ ግን አጭርና ደቃቃ ሰው ነበር፡፡ በዚያ ላይ ይህ ሰው ከዚያ ክስተት ወዲህም ይሁን ወዲያ ሰው ገድሎ አያውቅም፡፡ እንዲሁ ነው ራሱን ያጠፋው፡፡

ማርቴን ፓልማ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድ ልጅ ነው፡፡ አባቱ ከመገደላቸው ቀደም ብሎ እርሳቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ካገኟቸው ሰዎችም አንዱ ነው፡፡

‹‹ፖሊስ ገዳዩ ማን እንደሆነ ያውቃል፤ መግለጽ ነው ያልደረፈው›› ብሏል፡፡

ፖሊስ ምን ያስፈራዋል? ልጁ ምን ማለቱ ይሆን?

ፖሊስ ገዳዩን የሚያውቅ ከነበረ ታዲያ ይህን ሁሉ ሰዎች ለምን መረመረ? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ገዳይ ከልሆኑ ደግሞ ማን ነው ገዳዩ? ምናለበት ቢናዘዝ…

ረቡዕ በጉጉት እየተጠበቀች ያለችው ያለምክንያት አይደለም፡፡

ዶ/ር ቦንደሰን ግን ጨለምተኛ ሆነዋል፡፡

‹‹ እሮብ አዲስ ነገር ከፖሊስ አልጠብቅም፤ አዲስ መረጃም አይኖራቸውም፡፡ ያም ሆኖ ጉዳዩን መዝጋት ፈልገዋል፡፡ ደግሞም መዘጋት አለበት፤ መልስ የለኝም ማለትም አንድ መልስ ነው እኮ፡፡"

ሌላ ያልነገርናችሁ ምስጢርም አለ፡፡ ባለፈው ሚያዚያ ፖሊስ አንድ ዎኪቶኪ ስልክ አገኘ፡፡ ስልኩን የሆነ ሰውዬ ነው ለፖሊስ የሰጠው፡፡ ይሄ ዎኪ ቶኪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገደሉ ማግስት ነበር አንድ ሰውዬ አግኝቶት የደበቀው? ለምን ደበቀው?

ለስዊድናዊያን ረቡዕ የሩቅ ቅርብ የሆነችው ያለምክንያት አይደለም፡፡

በስዊድን አቆጣጠር ነገ መቼ ነው?