በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ፍርድ የቀረበው የቀድሞ ፖሊስ ባልደረባ 1.25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዋስ ተጠየቀ

በሂውስተን ሃዘናቸውን እየገለፁ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Pool

በሚኒያፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ አጣብቆ አንገቱን በጉልበቱ ለዘጠኝ ደቂቃ የተጫነው ነጭ ፖሊስ የሰው ህይወት በማጥፋት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቧል። በወቅቱም 1.25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ ተጠይቋል።

አቃቤ ሕግ እንደጠቀሰው ወንጀሉ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር እንዲሁም በበርካታ ግዛቶች የተነሳው ተቃውሞና ቁጣን ተከትሎም ነው ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ የተጠየቀው።

ዴሪክ ቾቪን በሁለተኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ የሚቀርብበት ሲሆን ሦስቱ ፖሊሶች ደግሞ በግድያ ወንጀል በመተባባር ይከሰሳሉ።

በሦስት ባልደረቦቹ ታግዞ አንገቱን ከመሬት ላይ አጣብቆ በጉልበቱ ደፍቆ ሲገድል የሚያሳየው ቪዲዮ ዓለም አቀፍ ተቃውሞዎችን እንዲሁም በአሜሪካ ውስጥ ያለውን መዋቅራዊ ዘረኝነት እንዲቆም ጥያቄዎችን አስነስቷል።

ዴሪክ ቾቪንን ጨምሮ ሦስቱ ፖሊሶች ከሥራም ተባረዋል።

በፖሊስነት ለአስራ ዘጠኝ አመታት ያገለገለው ዴሪክ ቾቪን በትናንትናው ዕለት በኢንተርኔት አማካኝነት በተደረገ የፍርድ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቧል።

ለአስራ አምስት ደቂቃ ያህል በነበረውም የፍርድ ሂደት ላይ አንድም ቃል ያልተነፈሰ ሲሆን እጁ በሰንሰለት ታስሮ ብርቱካናማ የመለዮ ልብስ አጥልቆ አነስ ባለች ጠረጴዛ ትይዩ ተቀምጦ ነበር።

ዳኛዋ ጂኒስ ኤም የጆርጅ ፍሎይድን ቤተሰቦች በምንም መንገድ እንዳያገኝ፣ የጦር መሳሪያውን እንዲያስረክብና የፍርድ ሂደቱም እስኪጠናቀቅ ከፀጥታ ኃይል አባልነቱ እንዲሰናበት የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ 1.25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ጠበቃውም የገንዘብ ዋሱን አልተቃወሙም።

ፖሊሱ ሶስት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን እነዚህም ያልታሰበበት ሁለተኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት፣ ሦስተኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት እንዲሁም ለግድያ ማድረስ የሚሉ ሲሆን፤ በእነዚህም ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በያንዳንዳንዳቸው 40፣ 25ና አስር ዓመት የተቀመጠው ከፍተኛ ቅጣት ተፈፃሚ ይሆንበታል።

ፍርድ ቤቱም ለሰኔ 22/2012 ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል። የአርባ አራት ዓመቱ ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በሚኒሶታ በሚገኝ እስር ቤት ያለ ሲሆን ለበርካታ ጊዜያትም ተዘዋውሯል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ክሶች ይቀርቡበታል እየተባለ ሲሆን፤ ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል ላይጠየቅ የሚችልበት እድል በጣም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ለዚህም እንደምክንያትነት የቀረበው አቃቤ ሕጉ ፖሊሱ የግድያውን ወንጀል ለመፈፀም ሆን ብሎ ማቀዱን፣ ነፍስ ለማጥፋት የነበረውን ፍላጎት እንዲሁም ምክንያት ማምጣት ሊኖርባቸው እንደሚችል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የሚኒያፖሊስ ከተማ በበኩሉ የፖሊስ አባላት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርጉትን አንገትን ጠምልሎ መያዝ አንዲሁም ማነቅ ያገደ ሲሆን ዲሞክራቶችም በፖሊስ ተቋም ላይ ለውጥ እንዲመጣ አዲስ የሕግ ረቂቅ አቅርበዋል።

በአሜሪካ ውስጥ የሚደረጉ የፀረ ዘረኝነት ተቃውሞዎች የቀጠሉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ሚኒያፖሊስ ከመምጣቱ በፊት ጆርጅ ፍሎይድ በኖረባት ቴክሳስም አስከሬኑ ለስድስት ሰዓታት ያህል እንዲሰናበቱት በፋውንቴይን ኦፍ ፕሬይዝ ቤተክርስቲያን ቀርቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትናንትናው ዕለት በሂውስተን፣ ህይወቱ ባለፈባት ሚኒያፖሊስና በትውልድ ቦታው ሰሜን ካሮላይና የሐዘን ሥነ ሥርዓትም በትናንትናው ዕለት ተደርጓል። ብዙዎችም ሐዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜም አስከሬኑ ወደ ቴክሳስ ተሸኝቷል።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦች ጋር ተገናኝተው ሐዘናቸውን ገልፀዋል።

"አዳምጠውናል፤ ህመማችንን ሰምተዋል እናም በተቻለ መጠን ተጋርተውናል" በማለት የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ቃለ አቀባይ ቤንጃሚን ክራምፕ ከፎቶ ጋር በትዊተር ገፁ አጋርቷል።