"የምር በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ታዝናላችሁ እንዴ?" የክሮስፊት ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ

በቴክሳስ የሚገኝ የጆርጅ ፍሎይድ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, MARK FELIX

ክሮስፊት ዓለም አቀፍ የስፖርት ትጥቆችና ቁሶችን አምራችና ቸርቻሪ ኩባንያ ነው፡፡ ከሰውነት ማጎልመሻ ጋር የተያያዙ ንግዶች ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡

የዚህ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ሰው በጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ሞት ላይ ተሳልቀዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው ሚስተር ግሬግ ግላስማን ይባላሉ፡፡ በዚህ መረን በለቀቀ ድርጊታቸው ውግዘት ከደረሰባቸው በኋላ ነው ሥራቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት፡፡

እኚህ ሰው በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ላይ ከተዘባባቱ ወዲህ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል የሚባልለት ኩባንያቸው ጋር የሥራ ግንኙነት ያቋረጡ በርካታ ዓለም አቀፍ መደብሮች ናቸው፡፡

ሰውየው ሥራቸውን የለቀቁት በቴክሳስ የፍሎይድ ቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡

እኚህ ሰው መልቀቂያ ባስገቡበት ደብዳቤያቸው "ሳት ብሎኝ በተናገርኩት ነገር ብዙ ሰዎችን አስቀይሚያለሁ፤ የኔ ንግግር ቢዝነሱን እንዲጎዳ ስለማልሻ ጡረታ ለመውጣት ወስኛለሁ "ብለዋል፡፡

እርሳቸውን የተካው ዴቭ ካስትሮ፣ ድርጅታችን ክሮስፊት "ራሱን አንድ ጥላ ሥር የተሰባሰበ ቤተሰብ የሚመለከት፣ ብዝኃነኃነትን የሚቀበል የብዙኃን ድርጅት ነው፤ አባሎቻችንን አስቀይመናል›› ብሏል፡፡

ሚስተር ግላስማን ይህን እጅግ ሀብታም ኩባንያቸውን የመሰረቱት በካሊፎርኒያ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በወላጆቻቸው መኪና ማቆምያ ውስጥ ምርት በመጀመር ነበር፡፡ አሁን ኩባንያቸው ሰፈርቶና ጎምርቶ 13ሺህ ከሚሆኑ አለማቀፍ መደብሮች ጋር ይሰራል፡፡

ሚስተር ግላስማን ቅዳሜ ለታ በትዊተር ሰሌዳቸው የጻፉት ነገር ነው ቁጣን የቀሰቀሰባቸው፡፤

አሜሪካ ዘረኝነት የኅብረተሰብ ጤና ቀውስ ነው የሚባለውን አባባል ተንተርስው በትዊተር ሰሌዳቸው "ኮቪድ-19" የሚለውን "ፍሎይድ-19" ብለው በሟቹ ጥቁር አሜሪካዊ ላይ ለማሾፍ መሞከራቸው ነው መጀመርያ ችግር የፈጠረው፡፡

ከዚያም አልፈው ከርሳቸው ጋር በሽርክና የሚሰሩ ኩባንያዎች ስለምን ክሮስፊት በዚህ ግድያ ላይ ዝምታን መረጠ ብለው ሲጠይቋቸው " ለዚህ ለጆርጅ ፍሎይድ ሞት የምር ታዝናላችሁ እንዴ? እኔም ሆንኩ የኔ ባልደረቦች ግን በጭራሽ ግድ አልሰጠንም" ብለው ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከርሳቸው ድርጅት ጋር የሚሰሩ ኩባንያዎች የሥራ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል፡፡

ይህን እርምጃ ከወሰዱት ውስጥ ዝነኛውን የስፖርት ትጥቅ፣ ሪቡክን (Reebok) የሚያመርተው አዲዳስ (Adidas) ይገኝበታል፡፡