በራያ ቆቦ በወረዳ አመራሮች ግድያ የሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች እጃቸውን ሰጡ

አቶ ስዩም መስፍን እና አቶ መንገሻ ሞላ

የፎቶው ባለመብት, KOBO COMM

የምስሉ መግለጫ,

አቶ ስዩም መስፍን እና አቶ መንገሻ ሞላ

ከሳምንት በፊት በአማራ ክልል በራያ ቆቦ ወረዳ አመራሮች ላይ የግድያ ወንጀል ፈጽመው ተሰውረው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ እጃቸውን መስጠታቸው አስታወቀ።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍን እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ሞላ ህይወታቸው ያለፈው እሁድ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ህግ ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ መሆኑን ጽህፈት ቤቱን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።

የወረዳው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት የቡድን መሪ የሆኑት አቶ አየነ አማረ ለቢቢሲ እንደገለጹት በግድያ ወንጀሉ ሲፈለጉ የነበሩት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወንድማማቾች ሲሆኑ፤ ተሰውረው ቆይተው ባለፈው እሁድና ትናንት ሰኞ ወልዲያ ማረሚያ ቤት በመሄድ እጃቸውን ሰጥተዋል።

የአካባቢው የጸጥታ አካል ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ እንደነበር ለቢቢሲ የተናገሩት የቡድን መሪው በመጨረሻም ተጠርጣሪዎቹ እራሳቸውን ለሕግ አካል ሰጥተዋል።

"የጸጥታ መዋቅሩ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከፍተኛ ክትትል በማድረግ መውጫ መንገድ እና አማራጭ ሲያጡ ነው እጅ የሰጡት" ብለዋል።

በቀጣይም ተጠርጣሪዎቹን እስካሁን በሕግ ጥላ ስር እንዳይውሉ ያገዙ እና በወንጀሉ ላይ ተባባሪ የነበሩ አካላት ካሉ በሚል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ አየነ ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል ከነዋሪዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ተጠርጣሪዎች ትናናት ሰኞ መያዙን አስታውቆ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል ብሏል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል ከነዋሪዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ተጠርጣሪዎች ትናንት ሰኞ መያዙን አስታውቆ አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል ብሏል።

የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ መንገሻ ሞላ ህይወታቸው ያለፈው በወልዲያ ከተማ የነበራቸውን ሥራ አጠናቀው ወደ ቆቦ ከተማ በመመለስ ላይ እያሉ ነበር።

ሁለቱ አመራሮች በመንገድ ላይ ሳሉ ከወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በሚጻረር እና ለኮሮናቫይረስ ስርጭት በሚያጋልጥ መልኩ አንድ የባጃጅ አሸከርካሪ ስድስት ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ተመልክተው ሕግን ለማስከበር በሞከሩበት ጊዜ ተተኩሶባቸው እንደተገደሉ መነገሩ ይታወሳል።

አመራሩቹን የያዘው አሽከርካሪ እና ሌላ በመኪና ውስጥ የነበሩ ኃላፊ ምን ጉዳት ያልደረሰባቸው ሲሆን የጸጥታ ኃይሎችን ከሮቢት ከተማ ይዘው ሲመለሱ ተጠርጣሪዎቹ ባጃጇን ጢሻ ውስጥ ደብቀው መሰወራቸውን አስታውቀዋል።

የወረዳው አመራሮችን ለመተካት በቀናት ልዩነት በውክልና የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ እና ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ባለሙያ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በመሥራት ላይ መሆናቸው ለማወቅ ተችለወል።

በተፈጸመባቸው ጥቃት የተገደሉት ሁለቱ የወረዳው አመራሮች አቶ ስዩም መስፍን እና አቶ መንገሻ ሞላ ሁለቱም ባለትዳርና የአንድ አንድ ልጅ አባት ነበሩ።