በህዳሴው ግድብ ድርድር በታዛቢዎች ሚና ላይ ስምምነት አለመደረሱ ተነገረ

ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF WATER AND IRRIGATION

ለወራት ተቋርጦ የነበረው በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረትና በአሜሪካ ታዛቢነት ተጀመረ።

ይሁን እንጂ በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉት አገራት ሚናን በተመለከተ ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ሃሳብ ላይ በተደራዳሪ አገራቱ መካከል መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለውና ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የተራዘመ ድርድርና ውይይት ሲደረግበት የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተው ድርድር መጀመሩን የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አክሎም ይህ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ተመልክቷል።

ድርድሩ ማክሰኞ ሰኔ 2/2012 ዓ.ም በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ቀደም ሲል ተሳታፊ ከነበረችው አሜሪካ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካናና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በታዛቢነት በተገኙበት በአገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ነው የተካሄደው።

በዚህ ከወራት በኋላ በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ተሳታፊ አገራቱ ስለድርድሩ የአካሄድ ሥነ ሥርዓት፣ ስለታዛቢዎችና ሌሎች ዋና ዋና ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ተደራዳሪ አገራቱ ቁልፍ የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበው በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል ተብሏል።

ስምምነት ባልተደረሰበት የድርድሩ ታዛቢዎች ሚናን በሚመለከት ያለውን ልዩነት ላይ መፍትሄ ለማግኘትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስብሰባው በዛሬው ዕለት [ረቡዕ]ም የሚቀጥል ይሆናል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ ናት" ብሏል።