"ኮሮናቫይረስ ስጋት ሆኖ ከቀጠለ ሁሉም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን ይቀጥሉ"

ፌዴሬሽን ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, House of Federation

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኮሮናቫይረስ ስርጭት በኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ማጽደቁ ተነገረ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን ባከናወነበት ወቅት መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዘሃን ዘግበዋል።

የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን ከማራዘም ጋር በተያያዘ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ከመረመረ በኋላ፤ የቫይረሱ ስርጭት በአገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ወስኗል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ ኮሚቴው የሚመለከታቸው አካላት የቫይረሱን ስርጭትና ጉዳት ገምግመው፤ ቫይረሱ የሚያስከትለው ጉዳት መቀነሱን ወይንም ጉዳት ማድረስ ማቆሙን ማረጋገጥ ሲችሉ አገራዊው ምርጫ ከ9 ወር እስከ 1 ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ማካሄድ እንደሚቻል የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ለመስጠት በመወያየት ላይ ይገኛል።