ከቀብር በኋላ በደረሰ የምርመራ ውጤት ሰበብ 53 ሰዎች በሰሜን ሸዋ ወደ ለይቶ ማቆያ ገቡ

ሰሜን ሸዋ

ጉዳዩ የሚጀምረው አዲስ አበባ ነው። ትውልዳቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪ በሥራ ቦታ በገጠማቸው አደጋ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ይወሰዳሉ።

በሆስፒታሉ ከሚደረግላቸው ህክምና በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ይደረግላቸዋል።

ነገር ግን የግለሰቡ የምርመራ ውጤት ሳይታወቅ ህይወታቸው ያልፋል። ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች አስከሬኑን ግንቦት 29/2012 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው እንሳሮ በመውሰድ በዚያው ዕለት ካራምባ ቀበሌ ጥቁር ዱር ሚካኤል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ይፈጸማል።

በቀጣዩ ቀን ከግለሰቡ የተወሰደው ናሙና ቫይረሱ እንዳለባቸው የሚገልጽ መሆኑን የወረዳው ጤና ጥቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር በቀለች ሞገስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሽታው ወደ ሌሎች የማኅበረሰብ አባላት እንዳይዛመት የወረዳው የኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ኮሚቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ ተፈፀመበት ካራምባ ቀበሌ በመሄድ የቅርብ ንክኪ አላቸው የተባሉትን ሰዎችን በመለየት ጊዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓልም ብለዋል።

እንደ ሲስተር በቀለች ከሆነ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ወደለይቶ ማቆያ ከማስገባት በተጨማሪ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይተው እስከ 14 ቀናት ድረስ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በጎጥ ደረጃ እንደተነገረም ገልጸዋል።

ውጤቱ እሑዱ 10 ሰዓት አካባቢ የደረሳቸው መሆኑን ያስታወቁት የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጸዳለ ሰሙንጉሥ 53 ሰዎችን በመለየት ምሽቱን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ የቅርብ ንክኪ ይኖራቸዋል የሚባሉ 20 ሰዎች ተለይተው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ በመውሰድ ወረዳውን ለማገዝ እንደተሞከረም ምክትል ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ንክኪ አላቸው የተባሉ ሰዎችን ናሙና መወሰዱን እና ውጤታቸው እየተጠበቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

እስካሁን ወደለይቶ ማቆያ ከገቡት መካከል ምልክት የታየባቸው ሰዎች እንደሌሉም ጨምረው ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ናሙና ውጤት በፍጥነት ካለመታወቁ ጋር በተያያዘ ናሙና የሰጡ ሰዎች በአንድ ቦታ ካልተቀመጡ ቫይረሱ ካለባቸው በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ የመከላከል ሥራውን ያከብዱታል ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም አዲስ አበባ ውስጥ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው እና ናመና የሰጡ ሁለት ግለሰቦች ውጤት ሳይነገራቸው በፊት ወደ ዞኑ ካቀኑ በኋላ ቫይረሱ እንዳለባቸው መነገሩንም ያስታውሳሉ።

"በአዲስ አበባ ያለው የስርጭት መጠን እና ጫናው ይህን ክፍተት ፈጥሮ ሊሆን ይችላል" የሚሉት ወይዘሮ ጸዳለ "ቢቻል የሚመረመረውን ማቆየት፤ አስከሬን ምርመራም ናሙና ወስዶ ወዲያው ከሚመለስ እንዲቆይ ቢደረግ" እንዲህ አይነቱን ክስተት ሊያስቀር እንደሚችል ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ አስከሬን ለቤተስብ ከመሰጠቱና ከቀብር በፊት ውጤቱ ቢደርስ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ ዕድል ስለሚሰጥ አመልክተው፤ በዚህ በኩል ሊኖር የሚችለውን የስታውን ስርጭት ለመግታት የላብራቶሪ ውጤት በቶሎ መታወቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡም የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረገ በኋላ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ውጤቱ እስኪታወቅ ከሰዎች ጋር ያለውን ንክኪ በማስወገድ እራስን ለይቶ ማቆየት እንደሚያስፈልግ የጤና መምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጸዳለ ሰሙንጉሥ ተናግረዋል።