ታሪካዊው የፍቅር ፊልም በዘረኝነት ምክንያት ታገደ

የፊልሙ ሁለቱ ገፀ ባህርያት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጎርጎሳውያኑ 1939 የተሰራው ታሪካዊው የፍቅር ፊልም 'ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ' በበርካቶች ዘንድ ዘረኝነት ይንፀባረቅበታል በሚል በአሜሪካ ፊልም ከሚያሳዩ ድረገፆች እንዲወገድ የተነሳውን ጥሪ ተከትሎ ፊልሙ እንዲወርድ ተደርጓል።

ከሰሞኑ ውሳኔውን ያሳወቀው ፊልም በድረገፅ የሚያሳየው ኤችቢኦ ማክስ ፊልሙ ከስምንት አስርት አመታት በፊት የተሰራ ከመሆኑ አንፃር ጊዜውን ቢያሳይም"ዘረኝነት የሚንፀባረቅበት ነው። በወቅቱም ስህተት ነበር አሁንም ስህተት ነው ብሏል።

ድርጅቱ አክሎ እንዳስታወቀው ፊልሙ እንዲሁ ከድረገፁ ላይ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ያለውን ታሪካዊ ዳራ የሚያሳይ ውይይት ተጨምሮበት እንደሚመለስ የገለፀ ሲሆን፤ ጊዜው መቼ እንደሆነ አልተጠቀሰም።

መቼቱን የአሜሪካን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገው ይህ ፊልም ባርነትን የቀረፀበት መልኩ ከፍተኛ ትችቶችንና ውግዘቶችን ሲያስተናግድም ነበር።

በማርጋሬት ሚቸል መፅሃፍ መነሻውን ያደረገው ይህ ፊልም ባርነት ከተወገደ በኋላ ጥቁር አሜሪካውያን በባርነት ዘመናቸው ህይወታቸው ሙሉ እንደነበርና ለቀድሞ ባለቤቶቻቸውም ታማኝ በመሆን በባርነት መቀጠል የሚፈልጉ ጥቁር አሜሪካውያን ህይወት ተንፀባርቆበታል።

ፊልሙ ከፍተኛ ዝናን ከማትረፍ በተጨማሪም በፊልም ሽልማቶች ታላቅ የሚባለውን አስር የኦስካር ሽልማቶችን ማሸነፍ ችሏል።

በፊልሙ ላይ የቤት ሰራተኛነትን ገፀ ባህርይ ተላብሳ የተጫወተችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ሃቲ ማክ ዳንኤል በረዳት ተዋናይነት ያሸነፈች ሲሆን፤ የኦስካር ሽልማትን ለመቀበልም የመጀመሪያዋ ጥቁር ናት።

ከሰሞኑም ታዋቂው ፀሃፊ ጆን ራይድሊ ፊልሙን አስመልክቶ ሎስ አንጀለስ ታይምስ በፃፈው ፅሁፍ " የባርነት ጊዜን ከፍ በማድረግ፤ ጥቁሮች ሲጨቆኑበትና ሲሰቃዩበት የነበረውንም ጊዜ ሌላ መልክ ለመስጠት ይሞክራል" የ'ትዌልቭ ይርስ ኦፍ ኤ ስሌቭ' ፀሃፊ አክሎም " በሆሊውድ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ተዋናዮች የተሰባሰቡበት ፊልም ቢሆንም ባርነት ጥሩ እንደነበርና ለጥቁሮችም ጥሩ ወቅት እንደነበር ለመስበክ ይሞክራል። ይህ ግን ትክክል አይደለም" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤችቢኦ ማክስ ባወጣው መግለጫ "ፊልሙ ዘረኝነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲሁ እንዲታይና ያለ መግለጫና ውግዘት መተው ሃላፊነት የጎደለው ነው" ብሏል።

ድርጅቱ አክሎም ፊልሙ ሲመለስ ብዙ እንደማይቀየር አመላክቷል።

ከኤችቢኦ ማክስ በተጨማሪ ዲዝኒ በበኩሉ በጎርጎሳውያኑ 1941 የተሰራው የአኒሜሽን ፊልም ደምቦን ጨምሮ የቀድሞ ፊልሞቹ "ባህልን ዝቅ የሚያደርጉ ይዘቶች" ሊኖራቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

ከሰሞኑ ከፀረ ዘረኝነትና የፖሊስ ጭካኔ ጋር የተያያዙ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ፊልሙን ለማስወገድ የደረሰው ኤች ቢኦ ማክስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ድረገፆች ፊልሞቻቸውን እየገመገሙ ነው።

'ሊትል ብሪቴይን' የተሰኘው ፊልም ከኔት ፍሊክስ፣ ብሪት ቦክስና ቢቢሲ አይ ፕሌየር እንዲወገድ ተደርጓል። ፊልሙ ዘረኝነት የሚንፀባረቅበትና አንዲት ነጭ ሴት ጥቁር ቀለም ተቀብታ በጥቁር ባህልና ማንነት ላይ ስትዘባበት ያሳያል ተብሏል።