የጆርጅ ፍሎይድን ሞት የቀረጸችው ሴት ምን አለች?

በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የፖሊሶችን ድርጊት በሞባይል ስልክ መቅረጽ አሜሪካ ውስጥ ተለምዷል

ሰዎች ስለ ሟች ጆርጅ ፍሎይድ ያወራሉ። ሰዎች ስለ ጨካኙ ፖሊስ ዴሪክ ያወራሉ። ሰዎች ይህን ሁሉ ጉድ በስልኳ ቀርጻ ለዓለም ስላጋራችው አንዲት ትንሽ ልጅ ግን አያወሩም።

የእርሷ የስልክ ቪዲዮ ባይኖር ዛሬ ስለ ጆርጅ ፍሎይድ የሚያወሩት ቤተሰቦቹ ብቻ በሆኑ ነበር። ማን ያውቃል?

አንዳንድ ወንጀሎች ወንጀል የሚሆኑት ለአደባባይ ሲቀርቡ ነው። ስርቆት ሌብነት ሆኖ የሚያስከስሰው ሲደረስበት ብቻ ነው። በጆርጅ ፍሎይድ የደረሰው ሳይቀረጽ ቀርቶ ቢሆንስ?

በዚህ ዘመን የማኅበራዊ ሚዲያ ጉልበት ኃያል ነው። ሰደድ እሳት ነው። ዓለምን ለማዳረስ ሰከንዶች ይበቁታል። አማዞን ጫካ ላይ የምትጫር ክብሪት…እንደማለት ነው።

ዳርኔላ ፍሬዘር ገና 17 ዓመቷ ነው። ገና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መግባቷ ነው።

የአክስቷን ልጅ ወደ ሰፈራቸው ምግብ ቤት ይዛት እየሄደች ነበር።

የአክስቷ ልጅ ደግሞ ገና 9 ዓመቷ ነው፡። ልክ ምግብ ቤቱ አካባቢ ስትደርስ የሆነ ጥቁር ሰውዬ ፖሊሶች ሲያስጨንቁት አይታ ቆመች፤ ቆመችና እንደ ዋዛ ስልኳን ከኋላ ኪሷ መዘዝ አድርጋ አወጣች።

'ሪከርድ' የሚለውን ቀይ ምልክት ተጫነች።

እርሷ መቅረጽ ስትጀምር ጆርጅ ፍሎይድ አየር አጥሮት ያቃስት ጀምሯል። "እባካችሁ! እባካችሁ" እያለ።

የእርሱ እስትንፋስ እስከወዲያኛው ልትቋረጥ የመጨረሻ ቃሉ "I can't breathe," [መተንፍስ አልቻልኩም] ነበር።

ይቺን "መተንፈስ አልቻልኩም" የምትለዋ ቃል ለመጨረሻ ጊዜ ከእስትንፋሱ ስትወጣ የዳርኔላ ስልክ ባትሪው አላለቀም። እርሷም መቅረጽ አላቆመችም።

ከዚህ በኋላ ጆርጅ ፍሎይድ ምንም አላለም። እስከወዲያኛው አሸልቧል።

የ44 ዓመቱ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ቾቪን ግን እጁን ኪሱ አድርጎ በጉልበቱ የፍሎይድን አንገት እንደተጫነው ነበር። ከዴሪክ ጋር ሦስት ፖሊሶችም ለዚህ ተግባሩ ተባባሪ ነበሩ።

የ17 ዓመቷ ዳርኔላ ስልኳ መቅረጹን እንዲያቆም ያደረገችው ፖሊስ ዴሪክ በእግሩ ወደ ግራ፣ ጆርጅ ፍሎይድ በቃሬዛ ወደ ቀኝ ሲሄዱ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

በጆርጅ ፍⶀይድ ተጠያቂው ዴሪክ ቾቪን

እናውግዛት ወይስ እናድንቃት?

ዳርኔላ በድምሩ 10 ደቂቃ ከ9 ሰከንዶች ቀርጻለች።

ድርጊቱን አጠናቃ ስልኳን ወደ ኪሷ ስትከት ግን በስልኳ ቋት ያኖረችው ተንቀሳቃሽ ምስል ዓለምን ሊንጥ እንደሚችል በፍጹም አልተከሰተላትም።

በወቅቱ ምን እንዳደረገች፣ ምስሉ ከተሰራጨ በኋላ ምን እንደተሰማት ለቢቢሲ ለመናገር ፍቃደኛ አይደለችም።

ለጊዜው ለቢቢሲም ሆነ ለሌላ ሚዲያ አስተያየት መስጠት ትታለች። ዕድሜዋም አንድ ምክንያት ይሆናል።

የእርሷ ጠበቃ ሚስተር ኮቢን ግን ለምን ክስተቱን መቅረጽ እንደፈለገች ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

"የዜግነት ግዴታዋን የመወጣት ስሜት ተሰምቷት ሊሆን ይችላል።"

"ያም ሆነ ይህ በእርሷ ቪዲዮ የመብት ትግል እቅስቃሴ ድጋሚ ተወልዷል ብዬ አምናለሁ" ይላሉ ጠበቃዋ።

የ2ኛ ደረጃ ተማሪዋ ዳርኔላ ከዚህ ክስተት በኋላ መጠነኛ የአእምሮ መታወክ ደርሶባት ሕክምና ጀምራለች።

በሕይወቷ እንዲያ ያለ ሰቅጣጭ ነገር አይታ አታውቅም።

ያን ቪዲዮ በፌስቡክ ሰሌዳዋ ላይ ከሰቀለችው በኋላ የነበረው ምላሽ በእርሷ ዕድሜ ለመቋቋም የሚቻል አልነበረም።

በፖሊስ ድርጊት የተቆጡ እንዳሉ ሁሉ በእርሷ ድርጊት የተቆጡም ቁጥራቸው ትንሽ አልነበረም። ያመሰገኗት እንዳሉ ሁሉ "ጫካኝ፣ አውሬ" ሲሉ የሞለጯትም ጥቂት አይደሉም።

የጆርጅ ፍሎይድ አሰቃቂ ሞት በግንቦት 25 ነበር፤ እርሷ ወደ ፌስቡክ ገጽ ያመራቸው ግን ከ2 ቀናት በኋላ በግንቦት 27 ነው። ወዲያውኑ እሳት ተቀጣጠለ። ነደደ፣ ጨሰ…። የእርሷ ቪዲዮ የእርሷ መሆኑ ቀረ። ሚሊዮኖች ቤት ገባ።

መጀመርያ አካባቢ በፌስቡክ ሰሌዳዋ ስር ለተሰጧት አስተያየቶች ምላሽ ትሰጥ ነበር።

አንዱ አስተያየት ሰጪ እርሷን ዝና ናፋቂ አድርጎ ይከሳታል። እንዲያ ባይሆን ኖሮ ሞባይልሽን አስቀምጠሸ የሚሞተውን ሰው ታድኚው ነበር ብሎ ይከሳታል።

እርሷም ዝም አላለችም። የሚከተለውን መለሰችለት።

"እኔ ያን ክስተት ባልቀርጽ ኖሮ፣ አራቱ ፖሊሶች ዛሬ በሥራ ላይ ነበሩ። ምናልባትም ሌላ ሰው እያነቁ…"

ዳርኔላን 'ያን ያደረግሽው ዝና ፍለጋ ነው' የሚሏት ሰዎች ከምር ያበሳጯት።

"ምን? ለዝና ነው ያደረግሽው ነው የምትሉኝ? ለገንዘብ ነው ያደረግሽ ነው የምትሉኝ? እናንተ ሰዎች ደደብና ደንቆሮዎች ሳትሆኑ አትቀሩም።"

በዳርኔላ ላይ የደረሰው ትችት፤ አደጋ እየደረሰ ቪዲዮ መቅረጽ ጽድቅ ነው ኩነኔ የሚል ሌላ ዙር የክርክር ምዕራፍ ከፍቷል። ለመሆኑ እንዲህ ማድረግ ተገቢ ነው? በሞራል ሕግ እንዴት ይሰፈራል?

ራስ ወደድነታችን ይሆን ሰው እየሞተ እኛ ቪዲዮ እንድንቀርጽ የሚያስችለን? በምንቀርጽበት ቅጽበት እየሞተ ላለው ሰው የምር ሐዘኔታ ይሰማናል? ነው ወይስ የሚያስጨንቀን በእኛ የሚቀረጸው የቪዲዮ ጥራትና ቀጥሎ የሚመጣው እውቅና?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፍሎይድ የተገደለበት ጎዳና ላይ የተቀመጠ መታሰቢያ

የፖሊስን ግፍ የቀረጹ ሰዎች ምን ደረሰባቸው?

ዳርኔላ በእርሷ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል ዓለምን ከናጠ በኋላ ሽልማት አልጠበቃትም። እንዲያውም ነገሩ ሕይወቷን ረብሾታል።

አሁን የአእምሮ ሐኪም እየተንከባከባት የሚገኘው ያለምክንያት አይደለም።

ከዚህ ቀደም ቪዲዮ በመቅረጽ ወንጀል ያጋለጡም ቢሆኑ ሽልማት አልጠበቃቸውም። ሕይወታቸው በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተረባብሿል።

1.ዴኒስ ፍሎረስ

ይሄን ቪዲዮ እየቀረጹ የፖሊስን ጭካኔ ማጋለጥ የጀመረው ሰው ዴኒስ ፍሎረስ ሳይሆን አይቀርም። የኒው ዮርክ ሰው ነው።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስን እንደሱ የቀረጸ የለም። ፖሊስ 70 ጊዜ አስሮታል። ከ90ዎቹ ጀምሮ እንደቀረጻቸው ነው ያለው።

ዛሬ 'ፖሊስ አደብ ይግዛ፣ ዘረኝነቱን ይተው' የሚሉ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ምክንያት የሆነው እርሱ ነው። ሞባይል ሳይጀመር እርሱ የፖሊስ ግፍ መቅረጽ ጀምሯል።

ይህ ድርጊቱ ሕይወቱን እንዴት እንዳከበደው ወደኋላ ላይ ይነግረናል።

ፍሎረስ የጀመረውን ተግባር ግን በብዙዎች ይተገበር ጀመር።

የፎቶው ባለመብት, Dennis Flores

የምስሉ መግለጫ,

ፍሎሪስ የኒው ዮርክ ፖሊሶችን በቪዲዮ ሲቀርጽ ከ70 ጊዜ በላእ ታስሯል

2.ቧንቧ ሠራተኛው ጆርጅ ሆሊዴይ

ከፍሎረስ በኋላ በ1991 አካባቢ አንድ ጆርጅ ሆሊዴይ የሚባል የቧንቧ ሠራተኛ ከአፓርትመንቱ በርንዳ ላይ ሆኖ የቀረጸው ነገር ምናልባትም እንደ ወረርሽኝ የተዛመተ የመጀርመያ ቪዲዮ ሳይሆን አይቀርም።

ያን ጊዜ እንደዛሬው ፌስቡክ የለ፣ ቅንጡ ሞባይል የለ! ምን የለ፣ ምን የለ!

እርሱ ቀረጻ ያደረገውም በተለምዶ የልደት ካሜራ መቅረጫ በምንላት ትንሽ ሶኒ ቪዲዮ ካሜራ ነበር።

ከበረንዳው ቀርጾ ያስቀረው ምስል ከባድ ውጤትን አስከተለ።

በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ሮድኒ ኪንግ የሚባልን አንድ ጥቁር ወጣት በርከት ያሉ ነጭ ፖሊሶች ከበውት እየተቀባበሉ ሲያዳፉት የሚያሳይ አሰቃቂ ቪዲዮ ነበር።

ጆርጅ ሆሊዴይ ያን ጊዜ ይህን ክስተት ሲቀርጽ ሞባይል አልነበረም ብለናል። 5ጂ ኢንተርኔትም አልተፈጠረም፤ ፌስቡክ የለም። ታዲያ እንዴት ተዛመተ?

ይህንን የቀረጸውን አሰቃቂ የቪዲዮ ቴፕ ወስዶ እዚያ ሰፈሩ ለሚገኝ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰጠ። ጣቢያው ተንቀሳቃሽ ምስሉን በዜና እወጃ ሰዓት ላይ አስተላለፈው፤ አገሪቱም በተቃውሞ ተናጠች።

ከዓመት በኋላ ያንን ድርጊት የፈጸሙ ፖሊሶች ፍርድ ቤት ነጻ ናችሁ ሲላቸው ደግሞ ደም አፋሳሽ ተቃወሞ በመላው አሜሪካ ዳግም ተከሰተ።

"ይሄ ሰው የቀረጸው ምስል ነው በአሜሪካ ምድር የፖሊስን ግፍ መቅረጽ እንዲለመድ ምክንያት የሆነው" ይላል በዚህ ተግባር ጥርሱን የነቀለው የኒው ዮርኩ ፍሎርስ፣ ለቢቢሲ።

በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ዜጎች በፖሊስ የሚፈጸምን ተግባር ቆመው የመቅረጽ መብት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Free VT

የምስሉ መግለጫ,

ጆርጅ ሆሊዴይ ሮድኒ ኪንግ በፖሊሶች ሲደበደብ የቀረጸው ምስል

3.ራምሴ ኦርታ

ከዚህ ክስተት በኋላ የመጣው የኤሪክ ጋርነር ጉዳይ ነው።

ሚስተር ጋርነር የ43 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ ነበር። በኒው ዮርክ ከተማ በ2014 ልክ እንደ ጆርጅ ፍሎይድ ሁሉ በነጭ ፖሊሶች አንገቱን ታንቆ ነበር የሞተው።

ፖሊሶቹ አንገቱን አንቀው የያዙት የምትሸጣቸው ሲጃራዎች ሕጋዊ አይደሉም በሚል ምክንያት ነበር።

ልክ እንደ ጆርጅ ፍሎይድ ሁሉ ሚስተር ጋርነርም ፖሊሶቹ አንገቱን ጠምልለው ሲያስጨንቁት፤ 'እባካችሁ መተንፈስ አቃተኝ፣ እባካችሁ!' እያለ ይጮኽ ነበር።

"I can't breath" የሚለው ንግግርም የትግል መፈክር መሆን የጀመረው ከእርሱ በኋላ ነበር።

በእርሱ የደረሰው የሞት አደጋ ፍርድ ቤት የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ነው ቢልም ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊስ ግን ነጻ ሆኗል። ያ ፖሊስ ስሙ ዳንኤል ፓንታሊዮ ይባል ነበር።

ሟችና ገዳይን ለጊዜው ትተን ያን ድርጊት በቪዲዮ ስላስቀረው ሰው ትንሽ እናውራ።

ራምሴ ኦርታ ይባላል። የእርሱ ጉዳይም እንደ ሌሎቹ ቀራጮች ሁሉ ሲያወዛግብ ነው የኖረው።

"ይህን ክስተት ከቀረጽኩ በኋላ ፖሊሶች ሲከታተሉኝ ነው የኖርኩት" ብሏል ከዚህ በፊት በሰጠው አንድ ቃለ ምልልስ።

በ2016 ራምሴ ኦርታ በአደገኛ እጽና በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ክስ ተመሰረተበት። አራት ዓመትም ዘብጥያ ወረደ።

እርግጥ ነው የተመሰረተበት ክስ የፖሊስን ድርጊት በቪዲዮ ከመቅረጽ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር ባይኖርም ጓደኛው ሚስተር ፍሎረስ እንደሚያምነው ግን ፖሊስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲከታተለውና የሚታሰርበትን ሰበብ ሲፈልግለት፣ እንዲሁም ቀን ሲጠብቅለት ነበር።

"ፖሊስን ማጋለጥ ለአደጋ መጋለጥ እንደሆነ ሊያስረዳ የሚችለው የራምሴ ኦርታ ጉዳይ ነው" ይላል ፍሎረስ።

የሚገርመው ራምሴ ኦርታ ከእስሩ በኋላ ምነው ያን ጊዜ ፖሊስን ባልቀረጽኩ ኖሮ ሲል ተጸጽቷል።

ያም ሆኖ ግፍ ሲፈጸም ዝም ብሎ ማለፍም ከባድ የሕሊና ጸጸት እንደሚተርፍ የፈይዲን ሳንታናን ታሪክ ማየት በቂ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ራምሴ ኦርታ ጓደኛው ኤሪክ ጋርነር በፖሊሶች ሲገደል በቪዲዮ በመቅረጹ ፖሊሶች እንደሚያሳድዱት ይከሳል

4.ፈይዲን ሳንታና

ፈይዲን ሳንታና በ2015 በሳውዝ ካሮላይና ግዛት፣ ቻርልስተን ከተማ ወደ ሥራ እየሄደ ነበር። አንድ ነጭ ፖሊስ ዋልተር ስኮት የሚባል አንድ ጥቁርን መኪናው ውስጥ ሳለ ሲያስቆመው ያያል።

ነገሩ እንዲሁ ስላላማረው ወይም ልማድ ሆኖበት ይሆናል ስልኩን አውጥቶ መቅረጽ ይጀምራል።

ፖሊሱ ትንሽ ዘወር ባለበት ቅጽበት ጥቁሩ ዋልተር ስኮት ድንገት ከመኪናው ወርዶ እግሬ አውጪኝ ይላል።

ሳንታና ይህ ሁሉ ሲሆን በግማሽ ልብም ቢሆንም እየቀረጸው ነበር። በዚህ ቅጽበት ፖሊሱ ያደረገው ነገር ግን ፍጹም ያልጠበቀው ነበር።

ፖሊሱ ሽጉጡን አውጥቶ እየሮጠ የነበረውን ጥቁሩን ዋልተር ስኮትን 8 ጥይቶችን ከጀርባ ለቀቀበት። አከታትሎ።

ዋልተር ስኮት መሬት ላይ ወደቀ።

ሳንታና እንደቀልድ የቀረጸው ነገር በኋላ ላይ ለከፍተኛ የአእምሮ መረበሽ ዳረገው።

"ድንጋጤ ውስጥ የከተተኝ ምንም ያልታጠቀ አንድ ጥቁር ሰውዬ እንዲሁ ለማምለጥ ሲል ብቻ ስለሮጠ 8 ጥይት ከጀርባው ይዘንብበታል ብዬ አላሰብኩም ነበር" ብሏል ለቢቢሲ።

ሳንታና ከዚህ ክስተት በኋላ ለሦሰት ቀናት ያህል ከቤት መውጣት አስጠላው። እርሱ ራሱ ስደተኛ ነው፣ በዚያ ላይ ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ መጥቶ በፀጉር አስተካካይነት ነበር የሚተዳደረው።

በስልኩ ያስቀረውን ነገር ለማንም አላሳየም። ለማንም አላጋራም። እንዲያ ቢያደርግ በኋላ ጣጣው ብዙ ነው ብሎ አሰበ።

እንዲያውም ያስቀረውን ተንቀሳቃሽ ምስል እስከ ወዲያኛው ሊሰርዘውና ቻርለስተን ከተማን ጥሎ ለመሄድም አስቦ ነበር።

በዚህ መወዛገብ ውስጥ ሳለ ታዲያ አንድ ቀን የፖሊስን ሪፖርት ተመለከተ። ያየውን ማመን አቅቶት ደርቆ ቀረ።

በዚህ ሪፖርት 8 ጥይት በጥቁሩ ሰው ላይ ከጀርባው የለቀቀበት ራሱን ለማዳን ነው ይላል።

"ፖሊስ ያን ያደረኩት ሰውየው መሳሪያ ይዞ ስለነበረ ሕይወቴ ላይ አደጋ እንዳያደርስ ፈርቼ ነው" የሚል ነገር ሳነብ ደነገጥኩ፤ "በዚህ ጊዜ ውሳኔዬን ቀለበስኩ" ይላል ሳንታና።

"በዚያ ጊዜ ይህን ጭልጥ ያለ ውሸት ለማጋለጥ በምድር ላይ ያለሁት ብቸኛው ሰው እኔ እንደሆንኩ አውቃለሁ፤ ፍርሃቴን ለመጋፈጥ ወሰንኩ" ይላል ለቢቢሲ።

ሳንታና ጨክኖ ያን ቪዲዮ ወስዶ ለሟች ቤተሰብ አስረከበ። ቪዲዮው ፖሊስ መዋሸቱን አጋለጠ።

"እኔ የቀረጽኩት ቪዲዮ በቅጽበት እንደ ሰደድ እሳት ይዛመታል አላልኩም ነበር" ይላል ሳንታና።

ከዚያ ቪዲዮ በኋላ የሳንታና ሕይወት እስከ ወዲያኛው ተቀየረ።

"የእንገድልሀለን ዛቻ፣ ዘረኛ ስድቦች ሁሉ ይዘንቡብኝ ጀመር። ፍርሃቴን ለመጋፈጥ እኔም ነገሩን መጋፈጥ ፈለኩ…"

ዕድሜ ለሳንታናና ለዚያ ቪዲዮ የፖሊስ መኮንንኑ ሚስተር ስላገር ክስ ተመሰረተበት። ፍርድም አገኘ።

"አንዳንድ ጊዜ ዝም ማለት የወንጀል ተባባሪነት ነው። ላመንኩበት ነገር መታገል ጀመርኩ። ፍርሃቴንም እያሸነፍኩ መምጣት ጀመርኩ" ይላል ሳንታና፤ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ፌይዲን ሳንታና ዋልተር ስኮት በጥይት ሲመታ የሚያሳየውን ቪዲዮ ለመዘረዝ አስቦ ነበር

ፍትህን በእጃችን ይዞ መዞር

ሞባይል ስልክና ኢንተርኔት በሌለበት ዘመን የተወለደው የፖሊስን ግፍ የማጋለጥ ተግባር ዛሬ ቀላል ሆኗል።

በርካታ ሰዎች ግፍ የመሰላቸውን ተግባር በስልካቸው እየቀረጹ በማኅበራዊ ድረ አምባው ያጋራሉ።

ይህም ወንጀሎች ቸል እንዳይባሉ፣ ማኅበረሰቡ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ነገሮች ዐይኑን እንዲገልጥ ምክንያት ሆነዋል። ወንጀል ፈጻሚዎችም ግፍ ሲፈጽሙ ዓለም እየተመለከታቸው እንደሆነ ማገናዘብ ጀምረዋል።

ለሀቀኛ መርማሪዎችም ነገሩ ሥራ አቅልሎላቸዋል።

ለምሳሌ የጆርጅ ፍሎይድን ክስተት ከወጣቷ ዳርኔላ ስልክ ወስደው አስቀምጠውታል። "ወደፊት ደግሞ ዳርኔላ ፍርድ ቤት ቀርባ እንድትመሰክር መደረጉ አይቀርም" ይላሉ ጠበቃዋ ሚስተር ኮቢን።

ምንም እንኳ ገና የ2ኛ ደረጃ ጀማሪ ተማሪ ብትሆንም ድርጊቱን በመቅረጽዋ ለአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ቃሏን ሰጥታለች። ቃሏን በምትሰጥበት ወቅት የነበራት ስሜት በዚህ ድርጊት ውስጥ መሳተፍ ተራ ተግባር እንዳልሆነ ማሳያ ነው።

ጠበቃዋ ዳርኔላ ቃሏን ስትሰጥ የነበረውን ሁኔታ በዚህ መልኩ ገልጸውታል።

"ያለማቋረጥ ታለቅስ ነበር። የደረሰባት ነገር ከባድ ነው። ለመርማሪዎች እንደገለጸቸው በማንኛው ሰዓት ዐይኗን ስትጨፍን የሚመጣባት ምስል ፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድን አንቆ ሲገድለው ነው። የሚሰማት ድምጽ 'እርዱኝ መተንፈስ አልቻልኩም' የሚለው ነው። ጆርጅ ፍሎይድ እየሞተ ሳለ የነበረው ፊቱ ይመጣባታል። ዐይኗን ስትገልጥ ግን ምስሉ የለም። ዐይኗን ስትጨፍን ጆርጅ ፍሎይድ ነው የሚታያት።"

ወጣቷ ዳርኔላ በዚህ ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርባ ባትመሰክር ምርጫዋ ነው።

ይህን ቪዲዮ በፌስቡክ ሰሌዳዋ ላይ ባትሰቅለው ትመርጥ ነበር። ምንም የመታወቅ ፍላጎት አልነበራትም። በዚህ ረገድ ጠበቃዋ ሚስተር ኮቢን ለቢቢሲ ያቀረበው የታሪክ ምስስሎሽ መጠቀስ የሚገባው ነው።

"ዳርኔላ ልክ እንደ ሮዛ ፓርክስ ነው የሆነችው፤ ሮዛ ፓርክስ በ1955 ዓ.ም በአላባማ ባቡር ተሳፍራ ሳለ ወንበር ለነጭ እንድትለቅ ስትጠየቅ እምቢ አለች፡፡…

ይህ ድርጊቷ በጥቁር መብት ትግል ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ነገር ግን እርሷ ያን ስታደርግ ወደፊት ማን እንደምትሆን አላሰበችውም። ማርቲን ሉተር ኪንግን ወይም ማልኮም ኤክስን ለመሆን አልነበረም እምቢ አልነሳም ያለችው። በቃ በዚያ ሰዓትና ሁኔታ ለነጭ ወንበሯን መልቀቅ ትክክል እንዳልሆነ ተሰማት አደረገችውም፡፡ የእኔ ደንበኛ ዳርኔላም እንዲያ ናት። መጥፎ ተግባር አየች፤ ስልኳን አውጥታ ቀረጸች።"

ዳርኔላስ ልጅ ናት፤ አንድ አዋቂ ሰው እየሞተ ያለን ሰው መርዳት ሲገባው ካሜራውን አውጥቶ ቢቀርጽ ድርጊቱ ጽድቅ ነው ኩነኔ?