በብራዚል የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች በ'መቃብር' ላይ የተተከለ መስቀል ነቃቀሉ

የቀብር ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ብራዚል የሞቱባት ሰዎች 40 ሺህ አልፈዋል። የተያዙባት ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን እየገሰገሰ ነው፤ ለጊዜው ትክክለኛ ቁጥራቸው 802 ሺህ 828 ቢሆንም ቅሉ።

ይህ አሐዝ ታዲያ መንግሥት ያመነው ነው።

የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች ቁጥሩ ከዚህ የትና የት ይበልጣል ይላሉ።

ምክንያቱም በብራዚል በቀን የሚመረመረው ሰው ቁጥር እንደ አሜሪካ ግማሽ ሚሊዮን ሳይሆን ጥቂት ሺህዎች ብቻ ናቸውና ነው።

የመብት ተሟጋቾች በቀኝ አክራሪው ፕሬዝዳንት ጄይር ቦልሶናሮ ተግባር ተቆጥተዋል።

እርሳቸውን ለመቃወም በሚል በዝነኛው ኮፓካባና የባሕር ዳርቻ 100 የሚሆኑ መቃብሮችን ቆፍረው ተምሳሌታዊ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህን እያደረጉ ያሉት አንድም በወረርሽኙ የሞቱትን ብራዚላዊያንን ለማሰብ ነው፣ አንድም የብራዚል መንግሥት ዜጎቹ እያለቁ እጁን አጣጥፎ መቀመጡን ለማሳበቅ ነው።

ያም ሆኖ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች በእነዚህ የመብት ተቆርቋሪዎች ላይ እያፌዙባቸው ይገኛሉ።በተምሳሌትነት በተቆፈሩ መቃብሮች ላይ የተተከሉ መስቀሎችን እየነቃቀሉባቸው ነው።

የጄይር ቦልሶናሮ እንቅስቃሴን ለመገደብ ፍቃደኛ አለመሆን የደቡብ አሜሪካንን ትልቋን አገር ለሁለት ከፍሏታል።

ብራዚል ከዓለም በሟቾች ቁጥም ሆነ በተሕዋሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ከሚባሉ አገራት ተርታ የምትመደብ ሆናለች።

የሟቾች ቁጥር 41ሺህ ሆኖ ከዓለም ሦስተኛ ብትሆንም በቅርቡ ዩናይትድ ኪንግደምን አልፋ እንደምትሄድ ጥርጥር የለውም ይላሉ የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች።

በተጠቂዎች ቁጥር ደግሞ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ አገር ናት።

ይህ በኮፓካባና ሆቴል ማዶ በባሕር ዳርቻ ተቆፍሮ እላዩ ላይ ጥቁር መስቀል የተሰካበት ተምሳሌታዊ መቃብር መብት ተቆርቋሪዎች ያዘጋጁት በሌሊት ተነስተው ነው።

የዚህ የመብት ተሟጋቾች ቡድን ስም ሪዮ ዴ ፓዝ ይባላል።

የዚህ ተቃውሞ አስተባባሪ አንቶኒዮ ካርሎስ ኮስታ ለሮይተርስ እንደተናገረው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በብራዚል ታሪክ ደርሶ የማያውቅ ጥፋት በአገራችን እየደረሰ እንደሆነ አልተገነዘቡም።

"ሰዎች በአያሌው እየሞቱ ነው። ሥራ አጥ ቁጥሩ ጣሪያ ነክቷል፣ ረሀብ እያንዣበበ ነው። የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ግን እያሾፉ ነው" ብሏል።

በተምሳሌነት የተተከሉትን መስቀሎች እየነቃቀሉ ያስቸገሯቸው የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ናቸው። ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በዚያች አገር ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች ያሏቸው ሲሆን በዚህ ከባድ ወቅት ዜጎቻቸው ምንም ስጋት ሳይገባቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ይፈልጋሉ።

በብራዚል ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 1ሺህ 239 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። 30 ሺህ ሰዎች ደግሞ ባለፉት ጥቂት ቀናት በቫይረሱ መያዛቸው ተደርሶበታል።