ትራምፕ የሲያትል ሰልፈኞችን "የአገር ውስጥ አሸባሪዎች" አሏቸው

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲያትል ነጻ ቦታ ተሰጥቷቸው ሰላማዊ ተቃውም እያደረጉ ያሉ ተቃዋሚዎችን ዘልፈዋቸዋል።

የተሰጣቸውን የተቃውሞ ስፍራቸውንም መልሰው እንደሚቆጣጠሩትም ዝተዋል።

በሲያትል ከፖሊስ ፍጥጫ ነጻ የሆነ የተቃውሞ ቀጠና የተሰጣቸው ተቃዋሚዎች በተለያየ መንገድ በጥቁሮች ላይ የሚደርሰውን ግፍ በመቃወም ላይ እንደሆነ ይታወቃል።

ፖሊስ በሲያትል ከሰልፈኞች ጋር ሲጋጭ ከሰነበተ በኋላ ከሰኞ ወዲህ ለሰልፈኞቹ አንድ ቀጠናን ለቆላቸው በዚያው የተገደበ ክልል ውስጥ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ግን ይህ የሲያትል ከተማ ውሳኔ ቅር አሰኝቷቸዋል። ሰልፈኞቹንም "እነዚህ የአገር ቤት አሸባሪዎች ወዬላቸው" ሲሉ አስፈራርተዋል።

የዋሺንግተን ግዛት ባለሥልጣናት በበኩላቸው 'እርስዎ ሰውዬ በማያገባዎ አይግቡብን፤ ይህ የእኛ ግዛትና የእኛ ውሳኔ ነው' ብለዋቸዋል።

ፖሊስ ከቀጠናው ከወጣ ጀምሮ የተቃውሞ እንቅስቃሴው በሰላም ቀጥሏል።

ፖሊስ ተቃውሞውን ለማስቆም በሞከረበት ባለፈው ሳምንት ተቃውሞዎቹ ከቁጥጥር ውጪ ወጥተው ነበር።

ሰልፈኞች ተቀጣጣይ ፕላስቲክ ፖሊስ ላይ የወረወሩ ሲሆን ፖሊስ በምላሹ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል። ሆኖም ተቃዋሚዎች በማየላቸው መኪኖች ተቃጥለዋል፣ አንዳንድ መደብሮችም ሲዘረፉ ነበር።

ሰኞ ዕለት የሲያትል ከተማ ከንቲባ ፖሊስ ከሰልፈኞቹ ዘወር እንዲልላቸው ባዘዙት መሰረት ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሏል።

ይህ ነጻ ቀጠና "ቼዝ" በሚል ምሕጻር የሚጠራ ሲሆን "ካፒቶል ሂል ኦቶኖመስ ዞን" የሚለው መጠርያን ይወክላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዚያ ቀጠና በአሁን ሰዓት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተቃውሞ ያሰማሉ፣ የአደባባይ ንግግሮችን ያዳምጣሉ፣ ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን ይታደማሉ።

ምንም እንኳ ሰልፈኞቹ መሪ የለንም ቢሉም ሰልፉን የሚቀላቀሉትን ሰዎች ማንነት የሚያጣሩ የሰልፍ መሪዎች ታይተዋል።

የሲያትል ሚዲያ ተቃውሞው ፌስቲቫል እንጂ ተቃውሞ አይመስልም ሲል ዘግቧል። ተቃዋሚዎቹ ሙዚቃ ይጫወታሉ፣ ይደንሳሉ፣ ምግብና መጠጥ በሽ ነው፣ የግጥም ንባብና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችም በተቃውሞ መሀል ተደግሰዋል።

በተቃውሞው ስብስብ ኮሮናቫይረስ ሾልኮ እንዳይገባ በበጎ ፈቃደኞች ሳኒታይዘር ይታደላል።

በዋሺንግተን ግዛት ትልቋ ሲያትል ከተማ ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ባለፈው ወር በነጭ ፖሊስ በግፍ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ግዛቶች የተነሱ ተቃውሞዎችን ጭጭ እንዲያሰኙ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይባስ ብሎም ለፖሊስ የሚመደበውን በጀት ከፍ ለማድረግና የስልጠና ሂደቶች እንዲከለሱ ለማድረግ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

በአንጻሩ ዲሞክራቶች ለፖሊስ የሚመደበውን በጀት የማቀጨጭ ሐሳብ ያነሱ ሲሆን፤ ይህ በዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል።

የፖሊስ በጀትን ማቀጨጭ የሚለው ሐሳብ ወደ ፖሊስ የሚሄደውን ከፍተኛ ገንዘብ ለወንጀል ተጋላጭ ናቸው በሚባሉ ኅብረተሰቦች ልማት ላይ የማዋል እቅድን የያዘ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በሲያትል የሚካሄደው ነጻ ተቃውሞ በፖሊስ ቀጥጥር ስር እንዲውል የዋሽንግተን ግዛት ባለሥልጣናትን ያሳሰቡ ሲሆን ሐሙስ በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት "እናንተ መቆጣጠር ካቃጣችሁ እኔ አቆጣጠረዋለሁ" ብለዋል።

በሌላ የትዊተር መልዕክት "ሲያትልን አሸባሪዎች አንበርክከዋታል" ሲሉ ጽፈዋል።

የዋሽንግተን ገዢን ደግሞ "ሞኛ ሞኞ" ሲሉ ዘልፈዋቸዋል። ገዢው ጄይ ኢንስሊ በበኩላቸው ለትራምፕ ትንኩሳ ምላሽ ሲሰጡ "አገር ለመምራት ብቁ ያልሆነ ሰው ነህ፤ እጅህን ከግዛታችን ላይ አንሳ" ብለዋል።

የሲያትል ከንቲባ ጄኒ ዱርካን በበኩላቸው "ክቡር ፕሬዝዳንት ሄደው ምድር ቤት ይደበቁ" ብለዋቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ተቃውሞ ባየለ ሰሞን በዋይት ሐውስ ምድር ቤት መደበቃቸው መዘገቡ የሚታወስ ነው። የከንቲባው አግቦም ይህን መሠረት ያደረገ መሆኑ ነው።