ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው ሶሪያው አሳድ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን አባረሩ

SUWAYDA24/AFP

የፎቶው ባለመብት, SUWAYDA24/AFP

በከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና በሕዝባዊ ተቃውሞ እየታመሰች በምትገኘው ሶሪያ ጫናው የበረታባቸው ፕሬዝደንት ባሻር አል አሳድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢማድ ካሚስን ከስልጣናቸው አባረሩ።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለምን ፕሬዝዳንቱ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ በኃላፊነት የቆዩትን ጠቅላይ ሚንስትር በሌላ ሰው ለመተካት እንደወሰኑ ያሉት ነገር የለም።

ነገር ግን መንግሥትን የሚቃወሙ ዜጎች በጎዳናዎች ወጥተው ባሻር አል አሳድ ከስልጣን ይነሱ ብለው ከጠየቁ ከቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን ማነሳታቸው ጥያቄን ፈጥሯል።

በሱዌይዳ በተካሄ የመንግሥት ደጋፊዎች ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ደግሞ ምዕራባውያን በጣሉት ማዕቀብ አገሪቱ ችግር ውስጥ ገብታለች፤ የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅምም እንዲዳከም ተደርጓል ብለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት አሜሪካ የባሻር አል አሳድን መንግሥት የሚደግፉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ሥራ እንደምትጀመር አስታውቃለች። ለዘጠኝ ዓመታት በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት 380 ሺህ ሶሪያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የሶሪያ ጦርነት ጅማሮ ዜጎች ''ዲሞክራሲ ይስፈን ሙስናም ይብቃ'' በሚል አደባባይ የወጡት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2011 ነበር።

ወዲያውኑም ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ላይ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ በፍጥነት ወደ ለየለት ጦርነት ተቀየረ። እስካሁንም መቋጫ ያለተገኘለት የእርስ በርስ ግጭት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

የዓለም ኃያላን አገራትም ጎራ ይዘው የጦርነቱ አካል መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ በጦርነቱ ቁልፍ ተዋናይ በመሆን በመካከለኛው ምሥራቅና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሟንም ማሳደግ ትፈልጋለች።

ኢራን ከአረብ አገራት ሶሪያን እንደዋነኛ አጋሯ የምታያት ሲሆን፤ ወደ ሂዝቦላህና እና ወደ ሊባኖስ የምትልካቸው መሳሪያዎችም የሚያልፉት በሶሪያ በኩል ነው።

ሳዑዲ አረቢያ ኢራን ከሕዝብ ቁጥሯ አብዛኛቹ ሱኒዎች በሆኑባት ሶሪያ የምትፈጥረውን ተጽእኖ ትቃወማለች።

አሜሪካ ተቃዋሚዎችን መደገፍ የጀመረችው የአሳድን ጨካኔ የተሞላበት ተግባር ከዚህ በላይ መታገስ አልችልም በሚል ነው።

በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት እነማን እየተዋጉ ነው?

ለፕሬዝዳንት አሳድ ድጋፍ የሚሰጡት

  • ሩሲያ - በአየር ጥቃትና በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የፖለቲካ እገዛ በማድረግ
  • ኢራን - በጦር መሳሪያ፣ በጦር አማካሪዎች እና በተዋጊ ጦር አቅርቦት
  • ሄዝቦላህ - በሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን በማቅረብ
  • የሺአ ሙስሊም ታጣቂዎች - በኢራን በኩል ከኢራቅ፣ ከአፍጋኒስታንና ከየመን በመመልመል

በተቃዋሚዎች በኩል

  • ቱርክ - በጦር መሳሪያ አቅርቦት፤ በወታደራዊና ፖሊቲካዊ ድጋፍ
  • የባህረ ሰላጤው የአረብ አገራት - በገንዘብና በጦር መሳሪያ አቅርቦት
  • አሜሪካ- በጦር መሳሪያ፣ በስልጠናና ለለዘብተኛ ቡድኖች ወታደራዊ ድጋፍ
  • ዮርዳኖስ - በቁሳዊ ድጋፍና በስልጠና

የአካባቢው ፖለቲካዊ ተንታኞች እንደሚሉት በጎረቤት አገር ሊባኖስ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሶሪያ ላይ ለወራት ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

ከሊባኖስ ባንኮች ሰዎችና ድርጅቶች የሚያወጡት የገንዘብ መጠን መገደብ የአሜሪካ ዶላር ወደ ሶሪያ እንደልብ እንዳይገባ አድርጎታል።

በዚህም ምክንያት በሶሪያ ሁሉም ነገር እጅግ ውድ እየሆነ መጥቷል።

በተጨማሪም አሜሪካ ሶሪያ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ እጥለዋለው ያለችው ተጨማሪ ማዕቀብ ይበልጥ ኢኮኖሚውን እንደሚያንኮታሉተው ተሰግቷል።